1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የጀርመን የባህር ሃይል የባህር ወንበዴዎችን ጥቃት አከሸፈ

እሑድ፣ ጥቅምት 11 2005

በምስራቅ አፍሪቃ የባህር ጠረፍ ላይ ተሰማርቶ የሚገኘዉ የጀርመን የባህር ሃይል፤ የባህር ላይ ወንበዴዎች በአንድ የኢራን መርከብ ላይ የሚያደረሱትን ጥቃት ማከሸፉ ተዘገበ።

https://p.dw.com/p/16U9F
ምስል picture-alliance/dpa

በምስራቅ አፍሪቃ በሶማልያ የባህር ጠረፍ ላይ ተሰማርቶ የሚገኘዉ የጀርመን የባህር ሃይል፤ የባህር ላይ ወንበዴዎች በአንድ የኢራን መርከብ ላይ የሚያደረሱትን ጥቃት ማስቆሙ ተዘገበ። « ዛክሰን » የሚል መጠርያ የያዘዉ የጀርመኑ የባህር ሃይል፤ አካባቢዉ ላይ ከሚገኘዉ ከአዉሮጳ ህብረት ጸረ- ባህር ላይ ወንበዴዎች ተልዕኮ፤ የባህር ወንበዴዎቹ መርከቡን መያዛቸዉን የሚያሳይ መረጃ በማግኘቱ መሆኑም ታዉቆአል። የጀርመን ጦር በድረ -ገጹ ላይ ባወጣዉ ዘገባ ፤ ወታደሮቹ በመርከቡ ሰባት ተጠርጣሪ ሶማልያዉያን እና መሣርያዎቻቸዉን በቁጥጥር ስር አዉለዋል። ወንበዴዎቹን ለመያዝ በተደረገዉ ወታደራዊ እንቅስቃሴ ከጀርመን ወታደር ወገን የቆሰለ እንደሌለ ዘገባዉ ያሳያል። «ዛክሰን» በሚል መጠርያ የሚታወቀዉ የጀርመን የባህር ሃይል፤ በምስራቅ አፍሪቃ የባህር ጠረፍ በባህር ላይ ወንበዴዎች እንዲዘምት በተሰማራዉ በአታላንታ ተልዕኮ ስር እንደሚንቀሳቀስ ይታወቃል።
በተያያዘ የሶማልያ ዜና፤ አንድ ሃሰን አብዲ የተባሉ የሶማሌ የባህር ላይ ወንበዴዎች አዛዥ ሁለት አመት ግድም ታግቶ የቆየ አንድ የእቃ ማጓጓዣ መርከብ መለቀቁን ትናንት ማስታወቃቸዉን የፈረንሳዩ የዜና አገልግሎች አዣንስ ፍራንስ ፕሪስ ዘገበ። ሃሰን አብዲ መርከቡን ለማስለቀቅ 600 ሺ ዶላር መከፈሉን፤ ነገር ግን ስድስት ግለሰቦች አሁንም ታግተዉ እንደሚገኙ መናገራቸዉ ተገልጾአል። በያዝነዉ አመት በህንድ ዉቅያኖስ ላይ በሚገኙ መርከቦች ላይ የሚደርሰዉ አደጋ በሚታየዉ ቁጥጥር እጅግ ቢቀንስም ቅሉ፤ አሁንም ስድስት መርከቦች እና ወደ 170 ያህል የመርከብ ሰራተኞች በባህር ላይ ወንበዴዎች ታግተዉ እንደሚገኙ ተነግሮአል።

አዜብ ታደሰ

ልደት አበበ