1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የጀርመን የማሊ ተልዕኮ

ቅዳሜ፣ ኅዳር 18 2008

የጀርመን መንግሥት ምዕራብ አፍሪቃዊቱን ሃገር ማሊ ለማረጋጋት በተጀመረው ጥረት ላይ የሃገሩ ብሔራዊ መከላከያ ሰራዊት የሚያደርገውን ትብብር ለማስፋፋት ባለፈው ጎርጎሪዮሳዊው ህዳር 25 ቀን 2015 ዓም ወሰነ።

https://p.dw.com/p/1HDnU
Symbolbild Bundeswehr in Mali
ምስል picture-alliance/dpa/B. von Jutrczenka

[No title]

200 የጀርመን ወታደሮች ባንድ በኩል የአውሮጳ ህብረት በደቡባዊ ማሊ በሚያካሂደው የማሊ ፀጥታ ኃይላትን የማሰልጠን ተግባር ላይ፣ በሌላ ወገን የተመድ በሰሜን ማሊ በጀመረው የሰላም ማስከበሪያ ተልዕኮ ደግሞ በምህፃሩ የ «ሚኑስማ» ተሳታፊዎች ናቸው።

ሁለቱ ማሊን የማረጋጋት ተልዕኮዎች የተጀመሩት በጎርጎሪዮሳዊው 2013 ዓም በሰሜናዊ ማሊ በመንግሥቱ አንፃር በተንቀሳቀሱት የቱዋሬግ ዓማፅያን እና በፅንፈኞቹ የሙስሊም ቡድኖች አንፃር የጥቃት ዘመቻ የጀመሩትን የፈረንሳይ ጸጥታ ኃይላት ለመርዳት እና ከፈረንሳይ ጋር ለመተባበር ነበር። እንደሚታወሰው በዚሁ ጊዜ በተካሄደ የመንግሥት ግልበጣ ሙከራ እና ሰሜናዊ ማሊን ተቆጣጥረው በነበሩት ዓማፅያንኑ ግስጋሴ ማሊ ትልቅ ቀውስ ውስጥ ወድቃ ነበር።

Bundeswehr in Mali EU-Ausbildungsmission
ምስል picture-alliance/dpa/M. Gambarini

ጀርመን ሰሞኑን በደረሰችው ውሳኔ መሰረት፣ በማሊ በተሰማራው የ«ሚኑስማ» ተልዕኮ ውስጥ ለምታደርገው ትብብር ተጨማሪ 650 ወታደሮችን ትልካለች፣ ይሁንና፣ ጀርመን የፀጥታ ሁኔታው አስጊ በሆነው በደቡባዊ ማሊ በተሰማራው በ«ሚኑስማ» ያሰለፈቻቸው የብሔራዊ መከላከያ ሰራዊት ወታደሮችዋ ቁጥር 10 ብቻ ነው። አሁን ተጨማሪ ወታደሮችን ወደ ማሊ ለመላክ የወሰነችው ፈረንሳይ ራሱን «አይ ኤስ» ወይም እስላማዊ መንግሥት ብሎ ከሚጠራው ፅንፈኛ ቡድን አንፃር በምታካሂደዉ ትግል ላይ ጥቂት ፋታ እንድታገኝ መሆኑን ጀርመናዊትዋ የመከላከያ ሚንስትር ኡርዙላ ፎን ዴር ላየን በማስታወቅ፣ ይኸው የመንግሥታቸው ውሳኔ የሃገራቸውን ፌዴራዊ ምክር ቤት፣ «ቡንድስታኽ»ን ፅድቂያ እንዳገኘ ተግባራዊ እንደሚሆን አስረድተዋል። እንደሚታወሰው «አይ ኤስ» ከሁለት ሳምንት በፊት በመዲናዋ ፓሪስ ላይ ጥቃት ጥሎ የ130 ሰዎችን ሕይወት ካጠፋ በኋላ ፈረንሳይ በዚሁ ፅንፈኛ ቡድን አንፃር ለተጀመረው ትግል የዓለም አቀፉን ማህበረሰብ ትብብር ጠይቃለች።

በማሊ የ«ሚኑስማ»ኃላፊ እና የተመድ ዋና ጸሐፊ ልዩ ልዑክ ሞንጊ ሀምዲ የጀርመን ተጨማሪ ወታደሮችን የመላክ ውሳኔ አወድሰዋል።

Symbolbild - Minusma Mali
ምስል Getty Images/AFP/H. Kouyate

« የጀርመን ጦር ኃይል ቡድኖችን በደስታ ነው የምንቀበላቸው። «ሚኑስማን» ለማጠናከር ወደ ማሊ መምጣት የሚችሉበት ሁኔታ በመኖሩ ደስ ብሎናል። ምክንያቱም የጀርመን ጦር በተለይ ዝና ያተረፈው በተሞክሮው፣ በቴክኖሎጂ ችሎታው እና በአስተማማኝነቱ ነው። እና ጀርመን በ «ሚኑስማ»ን የማሊ ፀጥታ ኃይላትን በማሰልጠኑ ተግባር ላይ ቢረዳ በጣም ጠቃሚ ነው። »

የጀርመን የመከላከያ ሰራዊት ወታደሮች በማሊ በ«ሚኑስማ» ስር ያደርጉታል ተብሎ የሚጠበቀው ተልዕኮ በውጊያ ተግባር የሚሳተፉበትንም ሂደት ማካተት ይገባው ይሆን በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄ የ«ሚኑስማ» ኃላፊ ሞንጊ ሀምዲ ሲመልሱ እንዲህ ነበር ያሉት።

« እውነት ለመናገር በጀርመን ፖለቲካ ውስጥ ጣልቃ መግባት አልፈልግም። ይሁን እንጂ፣ የጀርመን ጦር ኃይል ቡድኖች ርዳታ እና ተሞክሮ ሁሌም በደስታ የምንቀበለው ነው። »

አሪክ ቶፖና/አርያም ተክሌ

እሸቴ በቀለ