1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የጀርመን የመከላከያ ሚኒስትር የኮንጎ ጉብኝት

ማክሰኞ፣ ሰኔ 27 1998

የጀርመን የመከላከያ ሚኒስትር ፍራንዝ ዮሴፍ ዩንግ በዲሞክራቲክ ኮንጎ የሚያደርጉትን የሶስት ቀናት ጉብኝት ጀምረዋል።

https://p.dw.com/p/E0iT
ዮሴፍ ዩንግ በኮንጎ
ዮሴፍ ዩንግ በኮንጎምስል picture-alliance/ dpa

ከኮንጎ መንግስት ተወካዮችና ከፕሬዝደንት ጆሴፍ ካቢላ ጋርም ተገናኝተዉ ተወያይተዋል። ኪንሻሳ የሚገኙትን የጀርመን የሰላም አስከባሪ ወታደሮችንም አይተዋል። በኪንሻሳ ሁኔታዉ አሁን ፀጥ ያለ ነዉ። ሆኖም አፍን ሞልቶ ተረጋግቷል ማለት ግን አይቻልም።

በዲምክራቲክ ኮንጎ ሁኔታ ላይ ነገሮች ተረጋግተዋል ብሎ እርግጠኛ መሆን አይቻልም። የጀርመን የመከላከያ ሚኒስትር ፍራንዝ ዮሴፍ ዩንግ ሃምሌ 23 1998ዓ.ም በኮንጎ የሚካሄደዉ ምርጫ በሰላማዊ መንገድ እንዲከናወን የኪንሻሳ የሚገኙት የጀርመን ወታደሮች የበኩላቸዉን እንደሚያደርጉ ተናግረዋል።

ፕሬዝደንት ጆሴፍ ካቢላና የምርጫ ኮሚሽኑ ሊቀመንበር ማሉ ማሉም በትናንትናዉ ዕለት ከሚኒስትሩ ጋር ተነጋግረዋል።

ከኮንጎ የመከላከያ ሚኒስትር አዶልፍ ዖኑሲምባ ጋር በተገናኙበት ወቅት ዩንግ እንዲህ ነዉ ያሉት

«እኛ ገለልተኛ ሃላፊነት ነዉ ያለን፤ ምርጫዉ ዲሞክራሲያዊና ነፃ እንዲሆን ነዉ የምንፈልገዉ።»

ሆኖም በኮንጎ የሚገኙት የፖለቲካ ተቃዋሚ ኃይሎች የአዉሮፓ ህብረት ወታደሮች እዚያ መገኘት በስልጣን ላይ ያሉት ጆሴፍ ካቢላ ይዞታቸዉን እንዲያጠናክሩ ያደርጋሉ የሚል ስጋት ነዉ ያላቸዉ።

የመከላከያ ሚኒስትር ዩንግ ትናንት ከሰዓት በኋላ ደግሞ በቀድሞዉ የኪንሻሳ አዉሮፕላን ማረፊያ ዶሎ የሰፈረዉን የጀርመን ቃኚ ጦር ጎብኝተዋል።

በዚህ ስፍራ ነዉ ከአዉሮፓ ህብረት ሀገራት ተዉጣጥተዉ ወደኮንጎ የሚዘምቱት ወደ1000 ገደማ የሚሆኑት ወታደሮች የሚቆዩት።

በዚህ ቦታ 780 የጀርመን ወዛታደሮች ይገኛሉ። ከእነዚህ መካከል ሲሶዉ ኪንሻሳ የሚቆይ ሲሆን ቀሪዉ ደግሞ በተጠንቀቅ ጋቦን የሚጠባበቅ ይሆናል።

ዩንግ ስፍራዉ ሲደርሱ ባዩት በ54 የጀርመን መከላከያ ሰራዊት አባላት ተሳትፎ በፈጣን ሁኔታ የተደራጀዉ ወታደራዊ ካምፕ ይዞታም መደነቃቸዉን ገልፀዋል።

በአሁኑ ሰዓት በየቀኑ ወደስፍራዉ የሚሄደዉ ሰላም አስከባሪ ኃይል ኪንሻሳ በመግባት ላይ ነዉ። የመከላከያ ሚኒስትር ዩንግ በእርግጠኝነት እንደተናገሩትም እስከ ሃምሌ 11 ድረስ ሁሉም ተጠናቀዉ እዛ ይገኛሉ።

የጦሩ አዉሮፕላን አብራሪዎች ከሶስት ሄሊኮፕተሮች ጋር እዚያዉ ዶሎ ይቆያሉ። በስፍራዉ የመከላከያ ሰራዊቱ ሃኪም ቤት የገነባ ሲሆን ዘመናዊ የመገናኛ ዘዴዎቹና መሳሪያዎቹ በጀርመኖች ስር ይሆናሉ።

ስለሰራዊቱ አቀማመጥና ስለኪኒሻሳ ሁኔታ ዩንግ ሲገልፁም

«አሁን ስለሁኔታዎች ከወዲሁ ብዙ መተንበይ አልፈልግም። ለጊዜዉ ነገሮች ሰላማዊ ቢመስሉም ተረጋግቷል ማለት ግን አይደለም።»

ከአዉሮፓ ህብረት ሀገራት የተዉጣጡት ወታደሮች ከኪንሻሳ ኗሪዎች የተደረገላቸዉ አቀባለል መልካም እንደሆነ ለመከላከያ ሚኒስትሩ ገልፀዋል።

ሆኖም የምርጫዉ ዉጤት ይፋ ከሚሆንበት ከነሃሴ ወር ማለቂያ በኋላ አለመረጋጋት ሊከሰት ይችላል የሚል ስጋት ከወዲሁ አለ።

በአካባቢዉ የሚሰማሩት እነዚህ የሰላም አስከባሪ ኃይሎች የሚቆዩት ለአራት ወራት ብቻም እንደሚሆን ተገምቷል።

በርካታ የዉጪና ኮንጓዉያን ታዛቢዎች የሚከታተሉት ይህ የተወሳሰበ የምርጫ ሂደት በተገመተዉ የጊዜ ገደብ ተረጋግቶ ማለቁ እያነጋገረ ነዉ።