1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የጀርመን የልማት ርዳታ ሲቃኝ

ሰኞ፣ ሰኔ 25 2004

የጀርመኑ ዓለም ዓቀፍ የተራድኦ ድርጅት በጀርመንኛ ምህፃሩ GIZ በርሊን ላይ የአንድ ዓመት የሥራ ክንዉኑን አቀረበ። በተለያዩ ሀገሮች የሚንቀሳቀሰዉ GIZ ባለፈዉ የጎርጎሮሳዊዉ የዘመን ቀመር ከሁለት ቢሊዮን ዩሮ በላይ በጀት መመደቡ

https://p.dw.com/p/15Q9K
ምስል picture-alliance/dpa

ከፍተኛ ደረጃን አስይዞታል። የጀርመን የልማት ትብብር ትኩረት ለህዝቦች ነፃነት መስጠትን በማስቀደም፤ አፅናፋዊዉ የዓለም ትስስር ማለትም ግሎባላይዜሽን፤ ለሁሉም የተሻለ እድል እንዲከፍት ማድረግ እንደሆነ የሀገሪቱ የልማት ተራድኦ ሚኒስቴር ያመለክታል። መልካም አስተዳደርና የሰብዓዊ መብቶች ይዞታም ትልቅ ስፍራ ይሰጠዋል።

የልማት ትብብር ማለት ለአንድ ህዝብ ከቁሳቁስ ይልቅ ለራሱ ህይወት የሚበጀዉን ለመወሰን ኃላፊነት እንዲሰማዉ ነፃነት መስጠት ማለት ነዉ ይላል የፌደራል ጀርመን የልማት ተራድኦ ሚኒስቴር ስለልማት መርሁ ሲገልፅ። የልማት ትብብሩ ላይ የተሰማሩ ድርጅቶቹም አፅናፋዊዉ የዓለም ትስስር ለህዝቦች የተሻለ እድልን እንዲያስገኝ በልማት መርሆዉ የበኩላቸዉን አስተዋፅኦ ያደርጋሉም ይላል። ለዚህም በተለያየ ስያሜ ተግባር ተሰማርተዉ የቆዩትን የጀርመን የልማት ድርጅቶች በአንድ ጥላ ስር አሰባስቧል።

ካለፈዉ የጎርጎሮሳዊ ቀመር 2011ዓ,ም አንስቶ ነዉ በጀርመን የልማት ሚኒስትር ድሪክ ኒብል የበላይነት የጀርመን የቴክኒክ ትብብር GTZ፣ የጀርመን የልማት አገልግሎትDED፤ እንዲሁም ትምህርትና ስልጠና ላይ የሚያተኩረዉ Invent የተሰኘዉ የድርጅት በጋራ ተጣምረዉ፤ የጀርመን ዓለም ዓቀፍ የተራድኦ ድርጅት ማለትም GIZ የተፈጠረዉ። የልማት ድርጅቶቹ ጥምረት ስኬታማ እንደሆነ ነዉ የGIZ ቃል አቀባይ በርንት አይዘንብሌተር የሚገልፁት፤

«አዎ፤ የፌደራል መንግስት አገልግሎት ይበልጥ የተሻለ አድርገናል። አዎ፤ እዉቀታችንም በኢንዱስትሪ በበለፀጉት ሀገሮችም ሆነ እዚሁ ጀርመን፤ እንዲሁም በመዉጣትና በማደግ ላይ ባሉ ሀገሮች ሁሉ ይበልጥ እየተፈለገ ነዉ። አሁን የበለጠ ዉጤታማ ሆነናል። በዚህ የእድገት መንገድም ከሠራተኞቻችን ጋ ወደፊት መቀጠል እንፈልጋለን።»

Bangladesch Borguna GIZ Wiederaufbau nach Zyklon Sidr
ምስል RDF

GIZ እዚህ ጀርመንም ሆነ በሌሎች ሀገሮች ከ17 ሺህ በላይ ሠራተኞች አሉት። ከዚህ መሃል በአዳጊ ሀገሮች በጀርመንኛ ግርድፍ ትርጉሙ «ዓለም ወደፊት» በተሰኘዉ መርሃግብር ተካተዉ የሚሠሩ 3,700ዉ ወጣቶች ናቸዉ። ከዚህም ሌላ በካበተ ሙያዊ እዉቀታቸዉ ደግሞ GIZ ዉስጥ የሚያገለግሉ 9,700 በጡረታ ላይ የሚገኙ ባለሙያዎች ይገኛሉ። ድርጅቱ ባለፈዉ የአዉሮጳዉያን ዓመት 2011ዓ,ም በጀቱ ከሁለት ቢሊዮን ዩሮ በላይ መሆኑ ተጠቅሷል። ከሃያ ዓመታት አገልግሎት በኋላ በጡረታ ለመሰናበት የተቃረቡት አይዘንብሌተር በፋይናንስ ረገድ ድርጅቱ ለሌሎች ምሳሌ እንደሚሆን ነዉ የገለፁት።

«እኔ ላለፉት በርካታ ዓመታት በጉዞ ላይ ነበርኩ፤ በተለይ ወደብዙ ተጓዳኝ ሀገሮች በተደጋጋሚ ሄጃለሁ። ጀርመን እዚያ በGIZ ምክንያት ብቻም ሳይሆን ጥሩ ስም ያተረፈዉና በሌሎችም ለጋሾች ዘንድ በመንፈሳዊ ቅናት የምትታየዉ፤ በተናጠል በእያንዳንዱ ሀገር በምናከናዉነዉ ከሙያ ብቃት ጋ የተያያዘ አሠራር ነዉ፤ እንደሚመስለኝ በዚህ ልንኮራ ይገባል፤ ምክንያቱም የድርጅቶቹ የሥራ አመራር ማለፊያ ዉጤት በማሳየቱና በጣሙን ስኬታማ በሆነ መልኩ በመቀጠሉ ነዉ።»

የጀርመን የልማት ተራድኦ ትብብር በመሥራት ላይ የሚገኘዉ በአዲስ እና ዉጤታማ መዋቅር ብቻ ሳይሆን፤ ከተጓዳኝ ሀገሮች ጋም ለመተባበርም እንዲሁ መስፈርትና ደረጃ አዉጥቷል። የፌደራል ጀርመን የልማት ተራድኦ ሚኒስቴር ለወደፊቱ ሀገሪቱ በልማት ርዳታዉ ዘርፍ የምታተኩረዉ በትምህርት፤ በጤና፤ በገጠር ልማት፤ በመልካም አስተዳደር እንዲሁም ዘበዘላቂ የኤኮኖሚ ልማት ላይ እንደሚሆንም አመልክቷል። ከምንም በላይ የልማት ትብብሩን የሚመራዉ ለሰብዓዊ መብቶች የሚደረገዉ ጥበቃ እንደሚሆንም ያስረዳል። ከዚህም ሌላ ከመቼዉም ጊዜ በላቀ ሁኔታም የሚሰጠዉ ድጋፍ ፍላጎትን መሠረት ያደረገ እና ሚዛናዊ እንዲሆን ይጠበቃል ይላሉ ሃንስ ዩርገን ቤርፊልትስ የጀርመን የኤኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር /BMZ/ ዋና ፀሐፊ፤

Bangladesch Borguna GIZ Wiederaufbau nach Zyklon Sidr
ምስል RDF

«በዚህ ላይ በግልፅ መናገር የምንችለዉ ምንጊዜም ተፈላጊዉ ትልቅ ዋጋ የሚሰጠዉ ጉዳይ ቢሆንም ፍላጎትን መሠረት ያደረገ ነዉ። ይህንን ስንልም የምንፈልገዉ ይህ መሆኑን ሃቅን ተመርኩዘን እንናገራለን። የልማት ትብብር ተግባር ስኬታማ እንዲሆን ከተፈለገ እንደሶሻሊዝም ስርዓት የተዘጋጀ ምግብ በሳህን ለመመገብ ማቅረብ ሳይሆን፤ ስለወደፊቱም የጋራ ጥቅማቸዉ ከልማት ተጓዳኞች ጋ በጋራ መርህ መቀየስ ያስፈልጋል። አለበለዚያ የተሳካ ዉጤት ማስመዝገብ አንችልም።»

በጀርመኑ የነፃ ዴሞክራት የሚመራዉ የልማት ትብብር ይበልጥ የሚያተኩረዉ ከመድህን ዋስትና ጋ በተያያዘዉ ዘርፍ ነዉ። ለምሳሌ የእስያ ገበሬዎች ሰብላቸዉ ደርሶ ለተለያየ የተፈጥሮ አደጋ የመጋለጥ እድሉ ስለሚያመዝን ለዚህ የመድህን ዋስትና የገቡበት ስልት ይጠቀሳል። ከዚሁ ጋ በተያያዘም GIZ ባለፈዉ ዓመት በአረብ ሀገሮች፤ በሰሜን አፍሪቃና መካከለኛዉ ምስራቅ ለሰብል ዘርፍ ቅድሚያ መስጠቱም ተገልጿል። በተለይ በግብፅና ቱኒዚያ ጀርመን የልማት ትብብሯን እያሳደገች እንደሆነም ተመልክቷል።

ቤቲና ማርክስ

ሸዋዬ ለገሠ

ተክሌ የኋላ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ