1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የጀርመን የልማትና ትብብር ሚኒስትር ጉብኝትና የኢትዮዽያ የሰብዓዊ መብት ሁኔታ

ረቡዕ፣ ጥር 4 2003

የጀርመን የልማትና ትብብር ሚኒስትር ዴሪክ ኒብል ዛሬ የአራት ቀናት ጉብኝት በኢትዮዽያ ጀምሯዋል። ሚኒስትሩ የኢትዮዽያን የሰባዓዊ መብት ሁኔታ ትኩረት እንዲያደርጉ ተጠይቋል።

https://p.dw.com/p/Qq0I
ሚኒስትር ዴሪክ ኒብልምስል dpa

ሚኒስትሩ ከአዲስ አበባ ሌላ መቀሌንና ድሬዳዋን ይጎበኛሉ ተብሎ ይጠበቃል። በዚህም ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊን ጨምሮ የኢትዮዽያ መንግስት ባላስልጣናትን ያነጋግራሉ። ሚኒስትር ዴሪክ ኔብል ወደ ኢትዮዽያ ከማምራታቸው በፊት እዚህ ጀርመን ጋዜጣዊ መግለጪያ ሰጥተው ነበር። በመግለጪያቸውም በኢትዮዽያ ያለውን የሰብዓዊ መብት አያያዝ ሁኔታ በተመለከተ ከኢትዮዽያ መንግስት ጋር ውይይት ማድረግ የጉብኝታቸው ተቀዳሚ ዓላማ እንደሆነ ገልጸው ነበር። የዛሬው አውሮፓና ጀርመን ዝግጅታችን የሚኒስትር ኔብል ጉብኝት በኢትዮዽያ ያለው የሰብዓዊ መብት ሁኔታ ላይ እንዲያተኩር አንድ ዓለም አቀፍ የኢትዮዽያ የሰብዓዊ መብት ኮሚቴ ያደረገውን ጥሪ መነሻ በማድረግ በእግድ ላይ ያሉ ጋዜጠኖችና የሰብዓዊ መብት ጉባዔ ከሚኒስትሩ ጉብኝት ምን እንደሚጠብቁ ያነጋገርንበት መሰናዶ ይሆናል የሚቀርበው። ለዝግጅቱ መሳይ መኮንን ነኝ።

ጀርመን ለኢትዮዽያ የልማት እርዳታ ከሚሰጡ ምዕራባውያን መንግስታት ግንባር ቀደም እንደሆነች ይታወቃል። በተለያዩ የልማት መስኮች በኩል የሚደረገውን እንቅስቃሴ ለመደገፍ የጀርመን መንግስት ከፍተኛ የሆነ የገንዘብ ዕርዳታ በማድረግ ሲሆን በቅርቡም በወታደራዊ ዘርፍ የኢትዮዽያን መከላከያ ኃይል የማጠናከር ድጋፍ ማድረግ ጀምራለች-ጀርመን። ዓለም ዓቀፉ የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋች ድርጅት ሂውማን ራይትስ ዎች የዕርዳታ ገንዘብን ለፖለቲካ መጨቆኛ ይጠቀማል ሲል የኢትዮዽያን መንግስት በተደጋጋሚ ሲወቅስ ሰንብቷል። ጀርመን በዚህ አንጻር የምትሰጠው የገንዘብ ዕርዳታ ለታለመለት ዓለማ ስለመዋሉ ቁጥጥር እንድታደርግ ከተለያዩ ወገኖች ግፊት ይደረግባታል። በዚህ ሁኔታ ውስጥ ነው እንግዲህ የጀርመን የልማትና ትብብር ሚኒስትር ዴሪክ ኒብል በኢትዮዽያ የአራት ቀናት ጉብኝት ዛሬ የጀመሩት። በጀርመን የሚገኘው የኢትዮዽያ ዓለም ዓቀፍ የሰብዓዊ መብት ኮሚቴ በእርግጥ ሚኒስትሩ ወደ ኢትዮዽያ ከማምራታቸው በፊት የሰጡት ቃል ኃላ ላይ በፕሮግራማቸው ውስጥ አለመካተቱ ቅር አሰኝቶታል። የኮሚቴው ሰብሳቢ አቶ ስዩም ሀብተማርያም

በጀርመን የኢትዮዽያ ዓለም ዓቀፍ የሰብዓዊ መብት ኮሚቴ አዲስ አበባ ዛሬ ጉብኝት ለጀመሩት የልማትና ትብብር ሚኒስትሩ በጻፈው ደብዳቤ ሚኒስትሩ ተቃሚዎችን፤ የሰብዓዊ መብት ጉባዔን፤ የታገዱ ጋዜጠኞችን ጨምሮ ሌሎች በመንግስት በደል ይደርስባቸዋል ያላቸውን ተቋማትንና ግለሰቦችን እንዲያነጋግሩ ጠይቋል። አቶ ስዩም ሀብተማሪያም የጀርመንም ሆነ የሌሎች ለጋሽ ሀገራት ዕርዳታ ኢትዮዽያ ውስጥ መንግስትን ለሚቃወሙ መጨቆኛ ስለመዋሉ እንዲህ ይገልጻሉ።

የኢትዮዽያ ዓለም ዓቀፍ የሰብዓዊ መብት ኮሚቴ በኢትዮዽያ የሚደረገውን የመሬት መቀራመት በተመለከተ ሚኒስትሩ ትኩረት ሰጥተው እንዲከታተሉ በደብዳቤው ጠይቋል።

የጀርመን የልማትና ትብብር ሚኒስትር ዴሪክ ኒብል በኢትዮዽያ የሚደርጉትን ጉብኝት በተመለከተ ሌሎች ድርጅቶችም ለሚኒስትሩ ደብዳቤ ልከዋል። ለተጨቆኑ ህዝቦች የሚm4ገተው የጀርመን መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት በድህረ ገጹ የበተነውና ለሚኒስትሩ የተላከው ደብዳቤ በተለይ የመሬት መቀራመት በኢትዮዽያ አሳሳቢ ደረጃ ላይ እንደሚገኝና የጀርመን መንግስት ሁኔታውን በቸልታ እንዳያየው ጠይቋል። በኪዚህ ሌላ ዴር ደፌም የተባለ ለሴቶች መብት የሚሟገት ዓለም ዓቀፍ ድርጅትም በኢትዮዽያ በሴቶች ላይ የሚደርሰውን የሰብዓዊ መብት ጥሰት በሚቆምበት ሁኔታ ላይ ሚኒስትሩ የኢትዮዽያን መንግስት እንዲያነጋግሩ በደብዳቤ ገልጿል። ሚኒስትር ኔብል በጉብኝታቸው እንዲያነጋግሩዋቸው በእነዚህ ዓለም ዓቀፍ ተቋማት ከተገለጹት መኃል የሰብዓዊ መብት ጉባዔ ይገኝበታል። የጉባዔው ሰብሳቢ ወይዘሮ እልፍነሽ ደምሴ ድርጅታቸው ሲቋቋም ጀምሮ ጀርመን ከጎናቸው እንደነበረች በመግለጽ ይጀምራሉ።

የሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ ሰብሳቢ ወይዘሮ እልፍነሽ ደምሴ የጀርመን የልማትና ትብብር ሚኒስትር ጉብኝት ለድርጅታቸው ያለውን ጠቀሜታ ሲገልጹ

ሌላው በሚኒስትሩ ጉብኝት ዕድል ተሰጥቶአቸው እንዲያናግሩዋቸው በዓለም ዓቀፉ የኢትዮዽያውያን የሰብዓዊ መብት ኮሚቴ የተጠየቀው በመንግስት እገዳ የተጣለባቸው የግሉ ፕሬስ አባላትን ነው። ጋዜጠኛ ሰርካለም ፋሲል ከባሌቤታቸው ከጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ ጋር በአንድ ሙያ ውስጥ የሚገኙ ብቻ አይደሉም። የ1997ቱን ምርጫ ተከትሎ ወደወህኒ ባልና ሚስት አብረው ወርደዋል። አብረውም ከእስር ተለቀዋል። በመንግስት ዳግም ወደ ስራ እንዳይገቡ ተከልክለዋል።

በጀርመን የኢትዮዽያ ዓለም ዓቀፍ የሰብዓዊ መብት ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ስዩም ሀብተማርያም ዛሬ በአዲስ አበባ ጉብኝታቸውን ለጀመሩት የጀርመን የልማትና ትብብር ሚኒስትር በድጋሚ የሚሉት አላቸው።

መሳይ መኮንን

ተክሌ የኋላ