1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የጀርመን ዊንግስ አደጋ ተጎጂዎች ክስ

እሑድ፣ ነሐሴ 3 2007

ጀርመን ዊንግስ ካሁን ቀደም ለተጎጂ ቤተሰቦች 50 ሺህ ዩሮ ከፍሏል። የተጎጂ ቤተሰቦች ክሱን በዩናይትድ ስቴትስ ለማቅረብ አቅደዋል። በጀርመን ዊንግስ የአውሮፕላን አደጋ ቤተሰቦቻቸውን ያጡ የቀረበላቸው የካሳ ክፍያ በቂ ባለመሆኑ በሉፍታንዛ አየር መንገድ ላይ በዩናይትድ ስቴትስ ክስ ሊመሰርቱ ነው።

https://p.dw.com/p/1GCSr
Gedenkstein an Germanwings-Absturzstelle
ምስል picture-alliance/dpa/P. Kneffel

ንብረትነቱ የሉፍታንዛ አየር መንገድ የሆነው ጀርመን ዊንግስ በመጋቢቱ አደጋ ለሞቱ 150 ሰዎች በግለሰብ 25,000 ዩሮ ለተጎጂ ቤተሰቦች ለመክፈል ሃሳብ ያቀረበው ባለፈው ሰኔ ወር ነበር። ይህ ክፍያ አደጋው እንደተከሰተ አየር መንገዱ ለእያንዳንዱ ተጎጂ ቤተሰብ ከከፈለው 50,000 ዩሮ ተጨማሪ ነው።

አሁን የሚቀርበው ክስ ከዚህ ቀደም የጭንቀት ህመም የነበረበት የጀርመን ዊንግስ ረዳት አብራሪ አንድሪያስ ሉቢትዝ ለምን ማብረር እንደተፈቀደለት ይሞግታል ተብሏል።

የዩናይትድ ስቴትስ ህግ ከጀርመኑ በተሻለ ለስሜት ጉዳት ክፍያ እንዲደረግ እንደሚያስገድድና እስከ አንድ ሚሊዮን ዩሮ የሚደርስ የካሳ ክፍያ ሊከፍል እንደሚገባ የተጎጂ ቤተሰቦች ጠበቃ የሆኑት ኤልማር ጊይሙላ ተናግረዋል።ጀርመን ዊንግስ አስተያየት ከመስጠት ቢቆጠብም በአደጋው ህይወታቸውን ላጡ መንገደኞች የሚከፈለው አነስተኛ የካሳ ክፍያ ለእያንዳንዳቸው 100 ሺህ ዩሮ እንደሚሆንና እንደ ቤተሰቦቻቸው ሁኔታ እስከ አንድ ሚሊዮን ዩሮ እንደሚያድግ አስታውቋል።

የጀርመን ዊንግስ ረዳት አብራሪ አንድሪያስ ሉቢትዝ ዋና አብራሪው ከማብረሪያ ክፍሉ ሲወጣ ሆን ብሎ በመቆለፍ ከባርሴሎና ወደ ዱሴልዶርፍ ይበር የነበረውን አውሮፕላን አልፕስ ተራራ ላይ እንዲከሰከስ ማድረጉን የሚጠቁሙ መረጃዎች መገኘታቸው ይታወሳል።

እሸቴ በቀለ

ልደት አበበ