1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የጀርመን ዉሕደት 27ኛ ዓመት እና ዉጤቱ

እሑድ፣ መስከረም 28 2010

ጀርመን ዳግም በተዋሐደኝ በ27ኛ ዓመቱ ዘንድሮ አማራጭ ለጀርመን (AFD) በጀርመንኛ ምሕፃሩ የተባለዉ ቀኝ ፅንፈኛዉ የፖለቲካ ፓርቲ ሰፊ የሕዝብ ድጋፍ አግኝቶ የትልቂቱ አዉሮጳዊት ሐገር ሦስተኛ ትልቅ የፖለቲካ ፓርቲ መሆኑ የአዲስ ስጋት እና ጥያቄ መንስኤ ሆኗል

https://p.dw.com/p/2lOqh
Tag der Deutschen Einheit
ምስል picture-alliance/dpa/T. Frey

ውይይት፤ የጀርመን ውህደት

የጀርመንን ዳግም ዉሕደት በግንባር ቀደምትነት ከቀየሱት አንዱ፤ የያኔዉ የፌደራል (ምዕራብ) ጀርመን ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ሐንስ ዲትሪሽ ጌንሼር በ1990 (ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎርጎሪያኑ አቆጣጠር ነዉ) በጡረት ጋዜጣዊ ጉባኤ ላይ ከተካፈሉ ጋዜጠኞች አንዱ «ለጀርመን ዳግም ዉሕደት----» ብሎ ጥያቄዉን ሳያጋምስ ሚንስትሩ «ለጀርመን አንድነት» ብለዉ አቋረጡት።አረሙትም።ዘንድሮ 27 ዓመቱ።

ከሑለተኛዉ የዓለም ጦርነት ፍፃሜ ጀምሮ ምሥራቅና ምዕራብ ለሁለት የተገመሱት ጀርመኖች ዳግም መዋሐዳቸዉን ብሪታንያዎች በግልፅ ተቃዉመዉት ነበር።እንዲያዉም የያኔዋ የብሪታንያ ጠቅላይ ሚንስትር ወይዘሮ ማርጋሬት ታቸር ታሕሳስ 1989 ሽትራስቡርግ-ፈረንሳይ ለተሰየመዉ የአዉሮጳ ማሕበረሰብ የመሪዎች ጉባኤ ባደረጉት ንግግር «ጀርመኖችን ሁለቴ አሸንፈናቸዋል።አሁን ግን ዳግም መጡ።» እስከማለት ደርሰዉ ነበር።

Mainz Bürgerfest vor Tag der Deutschen Einheit
ምስል picture-alliance/dpa/T. Frey

ፈረንሳዮችም የጀርመንን ዳግም ዉሕደት  አልፈለጉትም።የሐገሪቱ ፕሬዝደንት ፍራንሷ ሚቴሯን ለሶቬት ሕብረቱ አቻቸዉ ለሚኻኤል ጎርቫቾቭ «ጀርመኖች ዳግም መዋሐዳቸዉ የማይቀር ቢሆንም፤ ፈረንሳይ ጨርሶ አትደግፈዉም» ብለዉ ነበር።አሜሪካኖች ዉሕደቱን በመቃወምና በመደገፍ መሐል ነበሩ።ሶቬየት ሕብረቶች ግን ከቦኖች ጎን የቆሙ መስለዋል።እዉቁ የጀርመን ዲፕሎማት ጌንሸር «ዉሐድት» እና «አንድነት» በሚሉ ቃላት መካከል ልዩነት ፈጥረዉ ከጋዜጠኞች ጋር የመነታረካቸዉ ምክንያትም ተቃዉሞ፤ ሥጋት፤ ፍርሐቱን እንደ ዲፕሎማሲዉ ወግ ለማለሳለስ ነበር።

BdT Tag der Deutschen Einheit
ምስል picture-alliance/dpa/N. Armer

ሚኒስቴሯ እንዳሉት የማይቀረዉ የጀርመኖች ዉሕደት ግን ብዙዎች ባልጠበቁት ፍጥነት ገቢር ሆኗል።ጀርመኖች ዳግም ቢዋሐዱ ሌላ ጠብ ይጭራሉ፤ በጦርነት ያጡዋቸዉን ግዛቶች ለመያዝ ይሞክራሉ፤ ዘረኛ ሥርዓትን ይመሠርታሉ የሚለዉ ሥጋት ግን ከሥጋት አላለፈም።

ጀርመን ዳግም በተዋሐደኝ በ27ኛ ዓመቱ ዘንድሮ አማራጭ ለጀርመን (AFD) በጀርመንኛ ምሕፃሩ የተባለዉ ቀኝ ፅንፈኛዉ የፖለቲካ ፓርቲ ሰፊ የሕዝብ ድጋፍ አግኝቶ የትልቂቱ አዉሮጳዊት ሐገር ሰወስተኛ ትልቅ የፖለቲካ ፓርቲ መሆኑ የአዲስ ስጋት እና ጥያቄ መንስኤ ሆኗል።የጀርመን ዉሕደት፤ በአዉሮጳ እና በዓለም ያሳደረዉ ተፅዕኖ  ሥፍራ እና የወደፊት ጉዞዋ ያጭር ዉይይታችን ትኩረት ነዉ።

ነጋሽ መሐመድ

ማንተጋፍቶት ስለሺ