የጀርመን እና የኢጣልያ እግር ኳስ ግጥሚያ
ሐሙስ፣ ሰኔ 21 2004
ይህ በጉጉት የሚጠበቀው ጨዋታ ጠንካራ ፉክክር የሚታይበት እንደሚሆን ተገልጾዋል።
ፖርቱጋልን፡ ኔዘርላንድስን፡ ዴንማርክን እና ግሪክን አንፎ አሁን ለግማሽ ፍፃሜ የደረሰው የጀርመን ቡድን ካለፉት አሥራ ሰባት ዓመታት ወዲህ ዋንጫ በሚያሰጥ የአውሮጳም ሆነ ዓለም አቀፍ ጨዋታ ላይ አሸንፎት ከማያውቀው የኢጣልያን ቡድን ጋ በዛሬው ዕለት የሚጋጠም ሲሆን፡ ብዙ ጀርመናውያን የ«እርግማን» ያህል የሚቆጥሩትን ሁኔታ ቀይሮ ለፍፃሜ ጨዋታ መብቃት ይጠበቅበታል።
ኢጣልያ ጀርመንን ሦስት ጊዜ፡ ማለትም፡ እአአ በ 1970 ዓም በዓለም እግር ኳስ ዋንጫ ግማሽ ፍፃሜ ጨዋታ ላይ አራት ለሦስት፡ እአአ በ1982 ዓም በፍፃሜ ግጥሚያ ሦስት ለአንድ ፡ እአአ በ 2006 ዓም በዓለም እግር ኳስ ዋንጫ ግማሽ ፍፃሜ ጨዋታ ላይ ሁለት ለአንድ ማሸንፍዋ የሚታወስ ነው። በተለይ ከስድስት ዓመታት በፊት በዶርትሙንድ የተሸነፉበት ግጥሚያ ትዝታ አሁንም ትኩስ ነው።
በዚህም የተነሳ፡ ያለፈውን ወደኋላ በመተው፡ ዛሬ ይህን የሽንፈት ሠንሠለት በመበጠስ ድል አድራጊ ለመሆን ቆርጦ መነሳቱን የጀርመን አልጣኝ ዮአኺም ለቭ አስታውቀዋል።
« ጥንካሬአችን የት ላይ መሆኑን በሚገባ እናውቃለን። በጣም በጣም ጠንካራ ቡድን አለን። ኢጣልያንም ጭምር ለማሸነፍና ወደ ፍፃሜ ጨዋታ ለማለፍ በሚያስችል አቋም ላይ እንገኛለን። »
የቡድኑ ዋና ሥራ አስኪያጅ ኦሊቨር ቢርሆፍ ግጥሚያው ቀላል ባይሆንም ቡድኑ ለዛሬ ግጥሚያ በሚገባ መዘጋጀቱን ገልፀዋል።።
« ለኢጣልያን ቡድን ከፍተኛ አክብሮት አለን። እንደሚመስለኝ፡ ጀርመን ባላፉት ጊዚያት በየትኞቹ ጨዋታዎች መሸነፏን በሚመለከት የሚወጡ መዘርዝሮች በተጫዋቾች ዘንድ ሚና አይጫወትም። እርግጥ ይህ ገሀድ ሁሌ ያለ ቢሆንም፡ ይህ ብቻውን ተጫዋቾቹን የሚያስጨንቅ አይመስለኝም። »
ጀርመን ለፍፃሜ ግጥሚያ ማለፍ ከፈለገች የፈጣኖቹን ኢጣልያ ቡድን አከፋፋይ አንድሬ ፒሮልንና የመሀል ተጫዋቹን ማርእዮ ባሎቴሊንና የeብ ጠባቂ ጂያንሉጂ ቡፎንን ጨዋታና እንቅስቃሴ ማደናቀፍ ይኖርባታል።
« ወሳኙ እነዚህ ተጫዋቾች የሚንቀሳቀሱበትንና ኳስ ወደሌላ ለማሳለፍ የሚያደርጉትን ትረት እና እንቅስቃሴ ማሰናከሉ ነው። ከዚህ በተጨማሪም የኢጣልያውያኑን የጨዋታ ሥልት አሰናክለን የራሳችንን ጨዋታ መምራት በምንችልበት ሁኔታ ላይ መገኘታችን በጨዋታው ሂደት ላይ ወሳኝ ሚና ይኖረዋል። »
በጀርመና በኢጣልያ መካከል የሚደረገውና በጉጉት የሚጠበቀውን ጨዋታ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ የእግር ካኳስ አፍቃሪዎች፡ በጀርመን የሚኖሩ ብዙዎቹ ኢጣልያውያንም በርሊን አደባባይ በተዘጋጀ ትላልቅ ቴሌቪዤን ፣ እንዲሁም፡ በየቡና በየምግብ ቤቶች በህብረት ይመለከታሉ።
አርያም ተክሌ
ተክሌ የኋላ