የጀርመን ኤኮኖሚና ኢንዱስትሪዎቿ
ማክሰኞ፣ ጳጉሜን 5 2005በዚህ የገንዘብ ቀውስ ዘመን ጀርመን በተሻለ አቋም መገኘት እንድትችል የጀርመን ኢንዱስትሪ ከፊል ድርሻ ማበርከቱ አይካድም ። ይህን የጀርመን አቋም በሥልጣን ላይ ያለው መንግሥትም ሆነ ተቃዋሚዎች በምርጫ ዘመቻ ወቅት መጠቀማቸው አይቀርም ።
«ለሃገራችን ላከናወናችሁት ተግባር አመሰግናለሁ ። ለአውሮፓ ላደረጋችሁትም እንደዚሁ አመሰግናለሁ »
የጀርመን መራሂተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል በዚህ ዓመት በሰኔ ወር በጀርመን የኢንዱስትሪ መታሰቢያ እለት ላይ ለመካከለኛ ኢንዱስትሪ ባለቤቶች ያቀረቡት ምሥጋና ። ከጀርመን አጠቃላይ የምጣኔ ሃብት ሩቡን ድርሻ የሚይዘው ኢንዱስትሪው ነው ። በጀርመን ኢንዱስትሪዎች ፌደሬሽን በምህፃሩ BDI ፣ ስር የተቃፉ ኢንዱስትሪዎች ጀርመን ውስጥ ከ8 ሚሊዮን የሚበልጥ ሠራተኛ አላቸው ። የፌደሬሽኑ ፕሬዝዳንት ኡልሪሽ ግሪሎ አንዳንዴ የጀርመን ኢንዱስትሪን የሥራ ማሽን ይሉታል ። በኢንዱስትሪ ከበለጸጉት አገሮች መካከል እንደ ጀርመን ፍፁምን የተሳካላቸው በቤተሰብ የሚመሩ በዛ ያሉ መካከለኛ ኢንዱስትሪዎች ያሉበት ሃገር የለም ። መካከለኛ ኢንዱስትሪዎች የሚገኙበት ሃገር የለም ። የጀርመን መካከለኛ ኢንዱስትሪዎች ከ500 የማያንስ ሠራተኛ ያስተዳድራሉ ። ከ 5 የጀርመን የኢንዱስትሪ ኩባንያዎች 4 ቱ በቤተሰብ የሚመሩ ናቸው ።
የጀርመን ምርቶች አሁንም በፍጥነት በማደግ ላይ ባሉት አገራት ጨምሮ በመላው ዓለም ተፈላጊ ናቸው ። ከተፈላጊዎቹ የጀርመን ምርቶች መካከል መኪናዎች ፣ ማሽኖችና የስነ ቅመማ ውጤቶች ይጠቀሳሉ ። ጀርመን ወደ ውጭ ከምትልካቸው ምርቶች 3/4 ተኛው ጥራት ያላቸው የኢንዱስትሪ ወጤቶች ናቸው ። ጀርመን ውስጥ ለጥናትና ምርምር እንዲሁም ለልማት ከሚመደበው ገንዘብ 90 በመቶው የሚገኘው ከኢንዱስትሪው ዘርፍ ነው ። የሌሎች የአውሮፓ አገራት ኢንዱስትሪዎች በአማካይ 70 ከመቶውን ነው የሚሸፍኑት ። የጀርመን ኢንዱስትሪዎች ፌደሬሽን ፕሬዝዳንት ኡልሪሽ ግሪሎ እንደሚሉት የኢንዱስትሪው መጠናከር ለጀርመን ኤኮኖሚ እድገት ብዙ አስተዋጽኦ አድርጓል ።
« ጀርመን ዛሬ ለምትገኝበት ደረጃ ያበቃት ከ 150 ዓመታት በላይ ኢንዱስትሪን የኤኮኖሚዋ መሰረት ያደረገ አቅጣጫ መከተሏ ነው ። ኢንዱስትሪው ደካማ በሆነበት ክፍለ ዓለሙም ደካማ ነው ። ደካማ ኢንዱስትሪ ማለት ከፍተኛ የሥራ አጥ ቁጥር እንዲሁም ህብረተሰቡን አለማረጋጋት ማለት ነው ። ስለዚህ ኢንዱስትሪውን ማጠናከር እጅግ ጠቃሚ ነው ። »
በዓለም ዓቀፉ የፋይናንስ ቀውስ ወቅት በተለይም እጎአ በ2009 ጀርመን ውስጥ የኤኮኖሚ እንቅስቃሴ በ5 በመቶ አሽቆለቆለ ። ኤኮኖሚውን ከገንዘብ ቀውሱ በፊት ወደ ነበረበት ደረጃ ለመመለስ 2 ዓመት ጊዜ ወስዷል ። ይሄ ውጤት እንደ ዋዛ የተገኘ አይደለም በጎርጎሮሳውያኑ 2000 ዓም መባቻ ላይ የጀርመን ኤኮኖሚ ከባድ ፈተና ላይ ነበር ።
በ1998 ሥልጣን የያዙት የጀርመን ሶሻል ዲሞክራት ፓርቲ SPD ና አረንጓዴዎቹ አጀንዳ 2010 የተባለውን የኤኮኖሚ ተሃድሶ አቅድ መራማድ ጀመሩ ። በዚህ ሰብብ የአሠሪና ሠራተኛ እንዲሁም የማህበራሲ ኑሮ ድጎማ ሥርዓት ተናጋ ። እጎአ በ2007 የእህትማማቾቹ የክርስቲያን ዲሞክራቶች ህብረት ፓርቲና የክርስቲያን ሶሻል ህብረት ፓርቲ እንዲሁም የሶሻል ዲሞክራቶች ፓርቲ ጥምረት ተፈጠረ ። ተጣማሪው መንግሥት በዚህ መስመር ቀጥሎ የጡረታ መውጫ እድሜ ከ65 ወደ 67 ከፍ እንዲል ተደረገ ። መራሂተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል ጀርመን ዛሬ ለምትገኝበት ደረጃ አነዚህ ማሻሻያዎች አስተዋፅኦ አድርገዋል ይላሉ ።
« ዛሬ የምንገኘው መገኘት የሚገባን ደረጃ ላይ ነው ። ምክንያቱም ጠንካራ የአሠሪና ሠራተኛ ህግ ማሻሻያ ተግባራዊ በማድረጋችን ነው ። አጀንዳ 2010 ባልነው የማህበራዊ ዋስትና ስርዓት እንዲሁም የጡረታ መውጫ እድሜ 67 መሆኑና ሌሎችም በዛ ያሉ ለውጦችን አድርገናል ። »
ሜርክል ጀርመን ባለፉት 10 ዓመታት አዲስ የኤኮኖሚ መሰረት መጣሏን ይናገራሉ ።
ጀርመን ከገንዘብ ቀውሱ ለትንሽ ነው ያመለጠችው ። በወቅቱ ከስረው የነበሩ የጀርመን ኩባንያዎች ህልውና እንዲያንሰራራ በኤኮኖሚ ማነቃቂያ መርሃ ግብር ድጋፍ እንዲያገኙ ተደርጓል ። ለመራሄ መንግሥትነት የተቃዋሚው የሶሻል ዲሞክራቶቹ ፓርቲ ያቀረባቸው እጩ ተወዳዳሪው ፕየር ሽታይንብሩክ CDUና SPD በተጣመሩበት መንግሥት ኩባንያዎች የፋይናንስ ድጋፍ የሚያገኙበትን አሰራር መርተዋል ። የከተሞችና ማዘጋጃ ቤቶች ገንዘብ ሥራ ላይ የሚውልበትን መርኃ ግብር መሠረተ ልማት የሚታደስበትን ደንብ አጭር የሥራ ጊዜ እነዚህ ሁሉ ሽታይን ብሩክ እንደሚሉት SPD ያፈለቃቸው ሃሳቦችና ተፈፃሚነት ያገኙም ነበሩ ። ህዝቡ በአመዛኙ እንደሚያስበው ግን ኤኮኖሚው በጥሩ ሁኔታ እንዲገኝ ያበቁ ሜርክል ናቸው ።
ለጀርመን መራጭ ህዝብ ፍትሃዊነት ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ጉዳይ ነው ። በገንዘብ ቀውሱ ወቅት ክስረት የገጠማቸውን ባንኮች ለማዳን ቀረጥ ከፋዩ ህዝብ በቢሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ መክፈል ነበረበት ። መንግስት ከገባው ተጨማሪ ዕዳ 80 ከመቶው የፋይናንሱን ዘርፍ እንዲያንሰራራ ለማደረግ የዋለ ነው ። ይህም ገንዘብ ለትምህርትና ለመሠረተ ልማት ሳይውል በመቅረቱ ዜጎችን ሳይጎዳ አልቀረም ። በከተሞችንንና በቀበሌዎች የሚያማትር ሰው የተበላሹ መንገዶችንና እድሳት የሚያሻቸውን ትምህርት ቤቶች ማየት የተለመደ ነው ። የጀርመን የኢንዱስትሪዎች ፌደሬሽን ፕሬዝዳንት ግሪሎ በበኩላቸው ያለ ኤኮኖሚ ስኬት የተሻለ ፍትህ ሊገኝ አይችልም ነው የሚሉት ። ለዚህ ደግሞ አዳዲስ የመዋቅር ተሃድሶ መደረግ አለበት ።በትምሕርት በመሠረተ ልማትና በመገናኛ ዘርፍ በሰፊው ገንዘብ ሥራ ላይ እንዲውል ካልተደረገ በጀርመን የኤኮኖሚእድገት በግልፅ ዝቅተና ደረጃ ሊይዝ እንደሚችል አያጠራጥርም ። እንደ ግሪሎ የአውሮፓ አርአያ የሆነችው ጀርመን አቅጣጫዋ ከተስተካከለ ቦታዋን ሳትለቅ ወደፊት መቀጠሏ አይቀርም ።
ሂሩት መለሰ
አርያም ተክሌ