1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የጀርመን ቤተ ክርስቲያን የልማት አገልግሎትና ኢትዮጵያ፧

ማክሰኞ፣ የካቲት 25 2000

ኢትዮጵያና ጀርመን በልማት ትብብር ረገድ ያላቸው ግንኙነት፧ በመንግሥት ደረጃ ብቻ ሳይሆን፧ በተለያዩ ተቋማትም ሆነ ማኅበራት ጭምር የሚካሄድ መሆኑ የታወቀ ነው። በቅርቡ፧ የጀርመን ቤተ ክርስቲያን የልማት አገልግሎት ከፍተኛ የልዑካን ቡድን፧ ከ ሦስት የህዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት(ቡንደስታኽ) አባላት ጋር፧ ሰሜንና ደቡብ ኢትዮጵያን ተዘዋውሮ ጎብኝቶ ነበር።

https://p.dw.com/p/E0Wr
ምስል picture-alliance/dpa
ጎብኝተው ከተመለሱት የህዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት አባላት መካከል፧ የክርስቲያን ዴሞክራት ኅብረት ፓርቲ አባል፧ እንዲሁም፧ በምክር ቤቱ፧ የኤኮኖሚ ትብብርና ልማት የቋሚ ኮሚቴ አባል፧ በተጨማሪም፧ በጀርመን ፓርላማ፧ የአፍሪቃ ወዳጅነት ቡድን አባል የሆኑትን፧ Harwig Fischer ን Ludger Schadomsky አነጋግሮአቸዋል። ተክሌ የኋላ አጠናቅሮታል።
በጀርመን ቤተ ክርስቲያን የልማት አገልግሎት የሥራ አስፈጻሚ አካል ባልደረባ፧ Dr. Claudia Warning የተመራው የልዑካን ቡድን ተጓዳኝ፧ የፓርላማ አባል Hartwig Fischer ከላይ ሳይሆን፧ ከታች ተዋቅሮ የተከናወነ ቀጣይነት ያለው የልማት ተግባርና እንቅሥቃሴ፧ የሰዎችን ኑሮ ለማሻሻል መበጀቱን፧ የውሃ ልማት፧ የጤናና የመሳሰሉ ዘርፎች ኮሚቴዎች፧ የልማት ፕሮጀክቶችን በሚገባ ማከናወናቸውን መሥክረዋል።
ከ 1997ቱ አከራካሪ የምርጫ ሂደትና መንግሥትም ከሚከተለው የሰብአዊ መብት አያያዝ አኳያ የሚያነጋግሩ ጉዳዮች እንዳሉ ሆነው፧ አሁን እንደገና የፊታችን ሚያዝያ አገር አቀፍ የማሟያ የወረዳና የቀበሌ ምርጫ ከሚካሄድበት ጊዜ ተደርሷል። ከኢትዮጵያን ጋር ባደረጉት ውይይት፧ ሳይገነዘቡ አልቀሩምና፧ የህዝቡን መንፈስ እንዴት አገኙት? ተብሎ ለቀረበላቸው ጥያቄ፧ ፊሸር ሲመልሱ....
«ማለት የምችለው፧ ሲቭሉን፧ ህብረተሰቡን ሲመለከቱት፧ በነፍስ-ወከፍ የሰዎችንሁኔታ ሲመለከቱት፧ በመንደር፧ ከርዙ ከተሰባሰቡ ሰዎች ጋር ተነጋግረናል። የለውጥ ስሜት ነው የሚያንጸባርቁት፧ ትልቅ ተስፋ ነው ያላቸው፧ ነገር ግን፧. የተለያዩ የመገናኛ ብዙኡን ባለመኖራቸው ብርቱ ቅሬታቸውን ያንጸባርቃሉ። ስለሆነም አገሪቱ የተለያዩ ነጻ የመገናኛ ብዙኀን እንዲኖሯት፧ በሰፊው የተለያዬ የሐሳብ መንሸራሸር እንዲኖርና በህዝብ ዘንድ እንዲሰርፅ ይመኛሉ። እንደሚመስለኝ፧ አሁን የተያዘው አቅጣጫ፧ ትክክለኛ ነው። ግን፧ ተግባራዊ መሆን አለበት፧ በዴሞክራሲ ጎዳና ለመጓዝ!«
የመገናኛ ብዙኀንና የመንግሥት ያልሆኑ ድርጅቶች መተዳደሪያ ደንብ፧ መንግሥታቸው ዐቢይ ግምት በመስጠት የሚነጋግርባቸው ጉዳዮች መሆናቸውን የጠቆሙት ፊሸር ከ 1997 ምርጫ ማግሥት በኋላ፧ የተገታው ቀጥተኛው የበጀት እርዳታ እንደገና የሚንቀሳቀስበት ሁኔታ ይኖር እንደሁ ተጠይቀው፧ «አይሆንም!« ነው ያሉት።
«አይሆንም! አሁን ባለው ሁኔታ ቀጥተኛ የበጀት እርዳታ እንደገና እንዲሰጥ አይደረግም። ነገር ግን፧ ለፕሮጀክቶች ሥራ ማስኬጃ የገንዘብ እርዳታ ማድረጉ ግን ትክክል ነው። በዚያ፧ የመንግሥት ያልሆኑ ድርጅቶች በትጋት ነው ተግባራቸውን የሚያከናውኑት። ለምሳሌ ያህል፧ የጀርመን የቴክኒክ ተራድዖ ማህበር አገልግሎት፧ 5 ዪኒቨርስቲዎች ለመገንባት የሥራ ውል አለው። ይህ በአጠቃላይ፧ 5 ቢልዮን የሚያወጣ ለትምህርት ብቻ የሚውል ነው። በሚመጡት 5 ዓመታት፧ 5 ቱ ቢልዮን፧ እንደሚሰጥ ቃል የተገባው በፓሪስ ክለብ ሲሆን፧ ፕሮጀክቱ፧ በኢትዮጵያ ሰፊ ተሳትፎ ጭምር ተግባራዊ ይሆናል።«
ኢትዮጵያ፧ በሶማልያ ስለምታበረክተው ድርሻስ ተነጋግራችኋል ወይ? ለፊሸር የቀረበላቸው ሌለው ጥያቄ ነበር።
«ከአምባሳደራችን ጋር ብቻ ሳይሆን ከውጭ ጉዳይ ሚንስትራችንም ጋር ከተነጋገርንባቸው ነጥቦች አንዱ ነው። በመጠኑም ቢሆን፧ ጀርም በሰፊው የበኩሏን አስተዋጽዖ አላደረገችም የሚል ቅሬታ ተሰምቷል። እኛም፧ በየትኞቹ የዓለም ክፍሎች ድርሻችን በሰፊው እየተወጣን እንዳለን አስረድተናል። ከኢትዮጵያው ውጭ ጉዳይ ሚንስትር ጋር (ከአቶ ሥዩም መሥፍን ጋር ማለታቸው ነው) በተነጋገርንበት ወቅት ነበረ ይህ ጉዳይ የተነሣው። አቶ ሥዩምም፧ ኢትዮጵያ በዚያ የመሪነት ሚና ለመያዝ አንዳች ፍላጎት እንደሌላት በጥሞና ገልጸውልናል።
ተልእኮው፧ በተ. መ. ድ. ሥልጣን ሰጪነት፧ የአፍሪቃ ኅብረት ተግባር መሆኑን ይህም፧ በረጅምና በመካከለኛ እቅድ ፀጥታ ለማሥፈን ነእ። እንደ ውጭ ጉዳይ ሚንስትሩ ግንዛቤ እርምጃው፧ ቀስ በቀስ ማረጋጊያና፧ ሰላም ማስገኛ ነው።«
የኢትዮጵያንና የኤርትራን የድንበር ውዝግብ በተመለከተስ ተነጋግረዋል ወይ? የው. ጉ. ሚ. ሥዩም መሥፍን አቋም ምንድን ነው?
«ኤርትራን በተመለከተ ሁኔታው ከባድ በመሆኑ፧ ሁለቱም ወገኖች የድንበር አካላዩ ኮሚሽን የሰጠውን ብዪን፧ አልተቀበሉትም። ምክንያቱም፧ የድንበር ማካለያው መሥመር፧ ዓለም አቀፉ ኮሚሽን ያቀረበው ሐሳብ፧ መስመሩ፧ በከፊል፧ መንደሮችን አቆራርጦ የሚያልፍ በመሆኑ ከዚህ ወይም ከዚያ ወገን ተቀባይነትን የሚያገኝ አልሆነም። ከ ው. ጉ. ሚንስትሩ ጋር ከተነጋገርን በኋላ እንደተገነዘብኩት፧ አንድ የአስቸኳይ ሁኔታ ውይይት የሚያስፈልግ ይመስለኛል። ይህ ዝርዝር ውሳኔዎችን የሚያቃልል ይሆናል። ግን፧ እንደማዬው፧ ማለቂያ የሌለው ታሪክ ነው።
ኤርትራ፧ በአሁኑ ጊዜ፧ ከጀርመን ጋር ያላት ግንኙነት በጣም የቀነሰ ነው። ችግሩ፧ በአሁኑ ጊዜ፧ የተ. መ. ሰላም አስከባሪ ኃይል ከኤርትራ በአጠቃላይ የሚወጣበት ሁኔታ ያለ ነው የሚመስለው። ምክንያቱም፧ በነዳጅ እገዳ ሳቢያ፧ የመቆጣጠር ተግባሩ የተገደበ ሆኗልና። ምግብም ቢሆን፧ ማኣቅረብ የሚቻልበት ሁኔታ የለም። ይህ ነጥብ፧ በሚመጡት ቀናት የምንመክርበት ጉዳይ ሆኖ ይቀጥላል። ከባልደረቦቼ፧ ከፓርላማ አባላት ጋር፧ ከመደበኛ ስብሰባ ውጭ እነጋገራለሁ። ይህን የማደርገው፧ በዚህ ነጥብ ላይ እንደገና፧ በፖለቲካ ርእስነት ጠለቅ አድርገን መምከር ይቻል እንደሁ ለማሳሰብ ነው።«