1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የጀርመን መራሒተ መንግሥት መግለጫ

ረቡዕ፣ መስከረም 10 2010

የጀርመን መራሒተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል ፒዮንግያንግ የኑክልየር መርሀግብሯን ካላቆመች ዩኤስ አሜሪካ ሰሜን ኮሪያን ሙሉ በሙሉ ለማጥፋት ትገደዳለች ሲሉ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ትናንት ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ ባደረጉት ንግግር ያሰሙትን ዛቻ የጀርመን መራሒተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል  በጥብቅ ወቀሱ።

https://p.dw.com/p/2kOFH
Deutschland wählt DW Interview mit Angela Merkel
ምስል DW

ሜርክል ዛሬ ከዶይቸ ቬለ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ከሰሜን ኮርያ ጋር በአቶም መርሀግብሯ ሰበብ የተፈጠረው ውዝግብ በሰላማዊ ዘዴ ብቻ መፍትሔ ሊፈለግለት እንደሚገባ አስታውቀዋል።
« ይህን ዓይነቱን ዛቻ እቃወማለሁ። እኔም ሆንኩ የጀርመን መንግሥት ማንኛውንም ዓይነት ወታደራዊ መፍትሔ ትክክለኛ ሆኖ አናየውም፣ የምንደግፈው ዲፕሎማሲያዊውን ጥረት ነው።  ይህ እንዲሆን በተቻለ መጠን መሰራት አለበት። በኔ አስተያየት ማዕቀብ መጣል እና ማዕቀቡንም ገቢራዊ ማድረግ ትክክለኛው መልስ ነው። ሰሜን ኮርያን በተመለከተ ሌላ የሚወሰድ ርምጃን ስህተት ነው። በዚህም የተነሳ ከአሜሪካዊው ፕሬዚደንት ጋር ግልጽ ልዩነት አለን። » 
 መራሒተ መንግሥቷ የአቶም መርሀግብር ውዝግብን ለማስወገድ ድርድር ጠቃሚ መንገድ መሆኑን ከኢራን ጋር የተደረሰውን ስምምነት በምሳሌነት በመጥቀስ ገልጸዋል። የፊታችን እሁድ በጀርመን በሚደረገው አጠቃላይ ምርጫ አማራጭ ለጀርመን  (አ ኤፍ ዴ ) የተባለዉ ቀኝ አክራሪ ፓርቲ ከ10% በላይ ድምፅ በማግኘት የሶስተኛ ቦታ ይዞ በምክር ቤት ሊወከል ይችል ይሆናል ስለመባሉ ለቀረበላቸው ጥያቄ ሜርክል ትልቆቹ ፓርቲዎች የሕዝቡን ጥያቄዎች በመመለስ ይኸው ፓርቲ  የሚያገኘውን ድጋፍ መቀነስ እንደሚቻሉ አመልክተዋል።ይሁንና፣ ፓርቲው ምክር ቤት ቢገባ አብረው ለመስራት እንደማይፈልጉ አስታውቀዋል።
« ይህን አልፈልግም ምክንያቱም ከአኤፍ ዴ ጋር ጭራሽ አብሬ አልሰራም። »
ካለፉት ጥቂት ጊዜያት ወዲህ እየሻከረ ስለመጣው ከቱርክ ጋር ስላለው ግንኙነት፣ ስለስደተኞች ጉዳይ ለመራሒተ መንግሥቷ ከቀረቡት ጥያቄዎች መካከል ጥቂቶቹ ነበሩ።

Deutschland wählt DW Interview mit Angela Merkel
ምስል DW

አርያም ተክሌ

ነጋሽ መሀመድ