1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የጀርመንና የኢትዮጵያ ግንኙነት፤ የሜርክል ጉብኝት

ረቡዕ፣ መስከረም 22 2000

የጀርመኗ ቻንስለር ወሮ/አንጌላ ሜርክል በሶሥት የአፍሪቃ አገሮች የሚያደርጉትን ይፋ ጉብኝት በአዲስ አበባ ይጀምራሉ። ቻንስለሯ ወደ አካባቢው ማምራታችው የጀርመን መንግሥት በተለይም ከሣሃራ በስተደቡብ በሚገኘው የአፍሪቃ ክፍል የልማት ትብብሩን ለማጠናከር ታላቅ ፍላጎት እንዳለው የሚያመለክት ነው።

https://p.dw.com/p/E0cf
አንጌላ ሜርክል
አንጌላ ሜርክልምስል AP

የጀርመንና የኢትዮጵያ ግንኙነት ቢቀር እስከ ሃያኛው ምዕተ-ዓመት መጀመሪያ መለስ ያለ ረጅም ታሪክ ሲኖረው ምናልባት ከወታደራዊው የደርግ አገዛዝ ዘመን በስተቀር በአብዛኛው የወዳጅነት ግንኙነት ሆኖ ነው የቆየው። ኢትዮጵያ ጀርመን በአፍሪቃ ክፍለ-ዓለም በምታካሂደው የልማት ተራደኦ ዓቢይ ትኩረት ከሚሰጣቸው ዋና ዋና አገሮች አንዷ ስትሆን ከይፋው መንግሥታዊ ትብብር ባሻገር የጀርመን ኩባንያዎችና ባለሃብቶች የገበያ ተሳትፎም በተለይ ከዘጠናኛዎቹ ዓመታት አጋማሽ ወዲህ እየጨመረ ነው የመጣው። ጀርመን በአቅም ግንባታ ረገድ፣ በአስተዳደር ዘርፍ፣ በሙያተኞች ሥልጣና፤ በምግብ ዋስትናና ሌሎች መስኮችም ዕርዳታ ታደርጋለች።

ፌደራል ሬፑብሊክ ጀርመን ከዩ-ኤስ-አሜሪካ፣ ከጃፓንና ከኔዘርላንድ ቀጥላ ለኢትዮጵያ ዋና ዋና ዕርዳታ አቅራቢዎች ከሚባሉት የበለጸጉ መንግሥታት አንዷ ናት። በ 2005 ዓ.ም. በሁለቱ መንግሥታት መካከል በተደረገ ስምምነት በሶሥት ዓመታት ውስጥ 69 ሚሊዮን ኤውሮ ለመስጠት ቃል ስትገባ ከዚሁ 43 ሚሊዮኑ ለፊናንስ ትብብር፤ የተቀረው 26 ሚሊዮንም ለቴክኒካዊ ተራድኦ ነበር የተመደበው። ጀርመን ኤይድስን መከላከልን በመሳሰሉ የጤና ጥበቃ ፕሮዤዎችም ትረዳለች። የኤኮኖሚ ዕድገትን ለማራመድ አስፈላጊ በሆነው የአቅም ግንባታ በኩልም ሙያተኞችን በማሰልጠን የምትሰጠውን ድጋፍ እያስፋፋች ነው። ይህም ከኤኮኖሚው ዘርፍ ፍላጎት እንዲጣጣም፤ ማለት የሠለጠነ የሙያ ሃይል ፍላጎትን ማርካት እንዲቻል አጠቃላይ ለውጥን ዒላማው ያደርጋል።

ጀርመን የመሬትን፣ የደንና የውሃ ሃብትን አጠቃቀምና አያያዝ በማሻሻል የኢትዮጵያ የእርሻ ምርት በረጅም ጊዜ ተገቢውን ዕድገት እንዲያሣይ ለማድረግም ትተባበራለች። በዚህ መስክ ያለው ትብብር አገሪቱን ከሰሜን እስከ ደቡብ የሚያዳርስ ሲሆን ዋና ዓላማውም በተለይ የምግብ እጥረትንና ረሃብን መቋቋም ነው። ጀርመን መንግሥትና የአስተዳደር ስርዓቱን በተመለከተ ለፌደራላዊ አወቃቀር የሚደረገውን ጥረት የምትደግፍ ሲሆን የድሃ-ድሃ በተባሉት አገሮች ድህነትን ለመታገል በተደረገው ዓለምአቀፍ ስምምነት መሠረት በ 2000 ዓ.ም. ለኢትዮጵያ የ 5.4 ሚሊያርድ ዶላር የዕዳ ስረዛ አድርጋለች። የሁለቱ መንግሥታት ትብብር በኢትዮ-ኤርትራው ጦርነት ወቅት ጥቂት ከመታወኩ በስተቀር በአጠቃላይ እያደገ ነው የመጣው። ይህም ባለበት የሚቀጥል ይመስላል።

እርግጥ በኢትዮጵያ ከግንቦቱ የ 2005 ምርጫ በኋላ የተከተለው ዓመጽና አስቸጋሪ የሰብዓዊ መብት ሁኔታ ግንኙነቱን ሳያከብደው አልቀረም። ሆኖም የቻንስለር አንጌላ ሜርክል ጉብኝት የሚያሣየው የጀርመን መንግሥት በንግግር መቀጠሉን እንደሚመርጥ ነው። ለምሳሌ የጀርመን የመልሶ-ግንባታ ክሬዲት ባንክ፤ በአሕጽሮት KfW የተሰኘው የፊናንስ ተቋም ከሣሃራ በስተደቡብ ጉዳይ ምክትል ፕሬዚደንት ብሩኖ ቬን የሚያረጋግጡት ይህንኑ ነው።

“ኢትዮጵያ ለኛ እጅግ ጠቃሚ ናት። ምክንያቱም በወቅቱ ሰፍኖ ከቀጠለው የአፍሪቃ ቀንድ አካባቢ ቀውስ አንጻር መፍትሄ በመሻቱ ረገድ የኢትዮጵያ ሚና እጅግ ከፍተኛ ነው። ይህንንም ማጠናከር ያስፈልጋል። ከዚህ በተጨማሪ አዲስ አበባ የአፍሪቃ ሕብረት መቀመጫ ናት። ሕብረቱ ደግሞ በፖለቲካ ሂደቱ ጥሩ አዝማሚያ ይዞ ነው የሚገኘው። በተለይ በአሕጉሪቱ የሰላም ጥበቃ ተልዕኮ ተሳትፎውን እያሰፋ መጥቷል። ስለዚህም ጀርመን በዚህ ጉዳይ ሕብረቱን ለማጠናከር አብራ መሥራቷ ጠቃሚ ነገር ይመስለኛል”

ጀርመን የግል የኤኮኖሚ ዘርፏን ጨምሮ በአፍሪቃ የበለጠ ተሳትፎ በማድረግ ግንኙነቷን ይበልጥ ለማጠናከር እንደምትፈልግ የቅርቡ የአገሪቱ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የአፍሪቃ ጉብኝት፤ አሁን ደግሞ የቻንስለር አንጌላ ሜርክል ጉዞ በግልጽ የሚያሣይ ነው። ቻንስለሯ በወቅቱ የዓመቱን የ G-8 መንግሥታት ርዕስነት የያዙ መሆናቸው ደግሞ ጉብኝቱን ለየት ያለ ክብደት ይሰጠዋል። አንጌላ ሜርክል ከሚጎበኛቸው ሶሥት አገሮች መካከል አንዷ ደቡብ አፍሪቃ ከጀርመን ጋር ያላት የኤኮኖሚ ትብብርም ሆነ የንግድ ልውውጥ እጅግ የጠነከረ ነው። ከኢትዮጵያና ከላይቤሪያ የሚነጻጸር አይደለም። የጀርመን ኢንዱስትሪ ከአውቶሞቢል ኩባንያዎች አንስቶ በተለያዩ ዘርፎች በአገሪቱ ተቆናጧል። የግሉ መዋዕለ-ነዋይ ፍሰትም እየጠነከረ የመጣ ጉዳይ ነው።

ላይቤሪያ እርግጥ ከረጅም ጊዜ የእርስበርስ ጦርነት በኋላ ገና ከቅርብ ወዲህ ወደ ጤናማ ሁኔታ ላይ በመመለስ የምትገኝ ናት። የአገሪቱ መንግሥት ከሕዝብ የሚጠበቅበትን ተሃድሶ ዕውን ለማድረግ አስፈላጊው ብቃትም ሆነ አቅም የለውም። ስለዚህም ቻንስለር አንጌላ ሜርክል የጀርመንን የድጋፍ ፍላጎት ለማሣየት የሚያደርጉት ጉብኝት ተሥፋ ሰጭ ነው። ፕሬዚደንት ጆንሰን ሰርሊፍ ለልማት ዕርዳታ ቁልፍ የሆነውን አንዱን ቅድመ-ግዴታ፤ ማለትም በጎ አስተዳደርን በማያሻማ ሁኔታ የተቀበሉ መሆናቸውም ትብብሩን ቀላል ያደርገዋል። በአንጻሩ የፖለቲካውና የሰብዓዊው መብት ይዞታ አከራካሪ በሆነባት በኢትዮጵያ ብሩኖ ቬን እንደሚሉት ከውይይት ሌላ ምርጫ የለም እንጂ ሁኔታው ከበድ ያለ ነው።

“አስቸጋሪ መሆኑ ግልጽ ነው። ነገር ግን በውይይት ከመቀጠሉ ሌላ የተሻለ ምርጫ የለም። በጎ አስተዳደር ጀርመን ከሣሃራ በስተደቡብ ካለው የአፍሪቃ ክፍል ጋር በምታደርገው የልማት ትብብር ከሶሥት ዓበይት ዓላማዎቿ አንዱ ነው። ጀርመን የአገሪቱን አስቸጋሪ የፖለቲካ ሁኔታ ምክንያት በማድረግ ቀድሞ በታቀደ የበጀት ዕርዳታዋ ላለመቀጠል ከሌሎች ለጋሽ ሃገራት ጋር በመሆን መወሰኗ ይታወሣል። ሆኖም ለሲቪሉ ሕብረተሰብ ብቻ ሣይሆን ለፓርላማውና ለግሉ የኤኮኖሚ ዘርፍ ጭምር የተሻለ ሁኔታን ለማመቻቸት ከመንግሥቱ ጋር ግንኙነት ማድረጉና መነጋገሩ እንደሚያስፈልግ አምናለሁ። በጥቅሉ ከባድ ቢሆንም በውይይቱ መቀጠል ይኖርብናል ማለት ነው”

በመንግሥታዊው የልማት ትብብር መስክ ግንኙነቱ ከሞላ-ገደል ዕርምጃ የሚታይበት ሲሆን በሌላ በኩል የግል መዋዕለ-ነዋይን በመሳቡ ረገድ ገና ብዙ እንደሚቀር ነው የሚነገረው። በኢትዮጵያ የኤኮኖሚና የንግድ እንቅስቃሴ ለመሳተፍ ወደ አገሪቱ የሚገቡት የጀርመን ባለሃብቶች ቁጥር ቢጨምርም የንብረት ዋስትና ስጋትና ቢሮክራሲ አሁንም ለብዙዎች መሰናክል መሆኑ አልቀረም። ይህ በተለይ መለስተኛ ኩባንያዎችና የግል ባለሃብቶችን ይመለከታል። ተቀማጭነቱ በአዲስ አበባ የሆነው ሃያ ገደማ የሚጠጉ ዓባል ኩባንያዎችና ባለሃብቶችን ያቀፈው የጀርመን ኢትዮጵያ የንግድ ማሕበር ፕሬዚደንት አሂም ብራውን መለስተኛ የጀርመን ኩባንያዎችን የሚመክሩት ሴኬት ለማግኘት ትዕግሥት እንደሚያስፈልግ ነው።

“ያው የተለመደው ችግር ነው ያለው። ትናንሽ ኩባንያዎችም ቢሆን እንደማንኛውም ኢትዮጵያ ውስጥ በተግባር እንደተሰማራ ኩባንያ ሁሉ ቢሮክራሲን መታገል አለብን። የኢትዮጵያ ቢሮክራሲ ገና ልምድ የሌለው በወጣት እግሩ የቆመ ነው ለማለት ይቻላል። ማለት ለመከተል የሚያመች ቀጥተኛ መርህ የለም። ሕጋዊ ዋስትናን የሚሰጥ በትክክል የተቀመጠ ነገር ይጎላል። ያለው በየወሩ የሚታደስ ደምብ ነው ለማለት እችላለሁ። እንግዲህ ኩባንያዎች ይህን ሁሉ ችግር ማለፍ አለባቸው”

ኢትዮጵያ ውስጥ ከአንድ ዓመት ገደማ ወዲህ በተለይ በግንባታው መስክ ሰፊ እንቅስቃሴ ነው የሚታየው። ብዙ ቤቶች የሚታነጹ ሲሆን የሕንጻ ተቋራጮች ተፈላጊነትም እየጨመረ ሄዷል። በሌሎች ገበዮች ለምሳሌ ዋነኛውን ኢትዮጵያ ለውጭ የምትሸጠውን ምርት ቡናን በተመለከተ የጀርመን ኩባንያዎችም በንግዱ ይሳተፋሉ። አንዱ እንዲያውም ቀደም ሲል የጠቀስነው የጀርመን ኩባንያዎችን ጥቅም የሚያስጠብቀው ድርጅት የጀርመን ኢትዮጵያ የንግድ ማሕበር ዓባል ነው። ወደ ጀርመንና ወደ ሌሎች የአውሮፓ አገሮች አበባ የሚሸጡ አምራችችም አልታጡም።
አጠቃላዩ ሁኔታ ይህ ሲሆን በሌላ በኩል ኢትዮጵያ በሶማሊያው ጦርነትና ከኤርትራ ጋር ባላት የድንበር ውዝግብ፤ ከዚያም አልፎ በውስጣዊው የፖለቲካ ችግር ሳቢያ ባለፉት ጊዜያት በዓለም መገናኛ ብዙሃን አዘውትራ መጠቀሷ ወደኋላ እንዲሉ ያደረጋቸው የውጭ ባለሃብቶች አልጠፉም። ወደ ኢትዮጵያ ሄደን ገንዘባችንን በሥራ ላይ ብናውል ደስ ባለን፤ ግን ሁኔታው አስተማማኝ አይደለም የሚሉ የጀርመን ኩባንያዎች አሉ። አሂም ብራውን ግን የሶማሊያ ሁኔታ በአገሪቱ ገበያ ላይ ተዕጽኖ ማድረጉ አይታያችውም።

“በተጠቀሱት ነጥቦች ምክንያት ወደ ኢትዮጵያ ከመምጣት የተቆጠበ ባለሃብት መኖሩን አልሰማሁም። እርግጥ እዚህ የውጭና የውስጥ ችግር አለ። ግን የሶማሊያን የመሰለው የውጭ ችግር እዚህ ምንም ተጨባጭ ተጽዕኖ እንደሌለው በቀላሉ ለመገመት አያዳግትም። እርግጥ ውስጣዊው ችግር ከበድ ያለ ነው። ሕጋዊ ዋስትናን በጥሩ ሁኔታ መጠበቅ አይቻልም። በአጭሩ ቀጥተኛ የሆነ ሕጋዊ ዋስትና የለም። በሌላ በኩል መንግሥት ስርዓቱን ፍቱን ለማድረግ አጥብቆ እየሠራ ነው። ቢሆንም ተቀባይነት ከሚኖረው መስፈርት ላይ ለመድረስ ገና ብዙ ጊዜ ይወስዳል። እኛ በአውሮፓ የምናውቀው ዋስትና፤ ለምሳሌ ውሎችን ማክበር፤ ወይም ውሎች ሳይከበሩ ቢቀሩ መክሰስ መቻል፤ ይህ እዚህ የለም። እርግጥ የሕግን መንገድ ተከትሎ መሟገት ይቻል ይሆናል። ግን ውሣኔ ማግኘቱ ለዓመታት ሊጓተት የሚችል ነው”

የጀርመኗ ቻንስለር በጉብኝታቸው ሂደት ከይፋው የልማት ተራድኦ ባሻገር ይህን የግሉን ኤኮኖሚ ዘርፍ ችግርም ሳያነሱ እንደማይቀሩ ዕምነት አለ።