1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የጀርመንና የቻይና ልዩ ግንኙነት

ዓርብ፣ ሰኔ 27 2006

የጀርመን መራሂተ መንግስት አንጌላ ሜርክል በያዝነዉ ሳምንት መጨረሻ ቻይናን ይጎበኛሉ። ሜርክል የጀርመን ከፍተኛ የንግድና ባንክ ባለስልጣናትን አስከትለዉ ለአራት ቀናት በቻይና በሚያደርጉት ጉብኝት ከፕሬዝደንት ሺ ቺ ፒንግና ከጠቅላይ ሚኒስትር ሊ ኪጂንግ ጋ ይነጋገራሉ።

https://p.dw.com/p/1CW2T
Bundeskanzlerin Merkel Flugzeug Bundesflugzeug
ምስል Michael Kappeler/AFP/Getty Images

የጀርመንን መራሂተ መንግስትነት ስልጣን ከያዙ ከጎርጎሪዮሳዊዉ 2005ዓ,ም አንስቶ አንጌላ ሜርክል የአሁኑ ጉዟቸዉን ጨምሮ ቻይናን ለሰባተኛ ጊዜ ነዉ የጎበኙት። ከቤጂንግ ጋ የጠበቀ ግንኙነት ለመመሥረትም ከአዉሮጳ ሃገራት ሁሉ ጀርመን ከፍተኛ ጥረት እያደረገች መሆኗን የዶቼ ቬለዉ ማቲያስ ፎን ሃይን ባጠናቀረዉ ዘገባ አመልክቷል።

እንደማትያስ ፎን ሃይን አተያይ የጀርመንና የቻይና ግንኙነት እየጎለበተ መሄዱ አያጠያይቅም። መራሂተ መንግስት አንጌላ ሜርክል ስልጣን ከያዙ አንስቶ ቻይናን ሲጎበኙ የአሁኑ ለሰባተኛ ጊዜ መሆኑ ነዉ።ባለፈዉ መጋቢት ወር ደግሞ የቻይና መንግስታ የገዢዉ ፓርቲዉ የበላይ ሺ ፒንግ በርሊንን ጎብኝተዋል። በጀርመን የጸደይ ወራት ደግሞ የዉጭ ጉዳይ ሚኒስትር ፍራንክ ቫልተር ሽታይንማየርና የኤኮኖሚ ሚኒስትር ዚግማር ጋብርኤል ፔኪንግ ነበሩ። በመጪዉ የመፀዉ ወራት ማለት በጥቅምት ወር ደግሞ በሁለቱ ሃገራት መካከል የቴክኖሎጂ ስልጠናና የባህል መርሃግብሮችን ለማጠናከር የቻይና ምክር ቤት አባላት ከጀርመን ቡንደስታኽ አባላት ጋ ለመመካከር ይመጣሉ ተብሎ እየተጠበቀ ነዉ። የታሰቡት መርሃግብሮች ተግባራዊ እንዲሆኑም የመንግስትን ከፍተኛ አካላት ተሳትፎ እንደሚፈልጉ ነዉ ሜርካቶር የተሰኘዉ የቻይና ጥናት ተቋም ባልደረባ የሚያመለክቱት፤

Symbolbild Deutschland China Flaggen
ምስል Ed Jones/AFP/Getty Images

«የጀርመንና የቻይናን ግንኙነት የማበልፀጉ ጉዳይ ነዉ። በርከት ያሉ የሁለትዮሽ ስብሰባዎች መደረጉም እዉነት ነዉ። ትርጉም ያላቸዉ የቴክኖሎጂ ስልጠናና የባህል መርሃግብሮች በሁለቱ ወገኖች መካከል እንዲኖሩም ለመመካከር በጥቅምት ወር ተስማምተዋል። ይህ ተግባራዊ እንዲሆን ደግሞ ሥራዉን በሚያከናዉኑት ወገኖች ድርድር ብቻ ሳይሆን በከፍተኛ ደረጃ ላይ የሚገኙትንም ድጋፍ ይፈልጋል።»

በአዉሮጳዋ ባለጠንካራ ኤኮኖሚ ሀገር ጀርመን የቻይና ገበያን ማግኘት ወሳኝ ጉዳይ ነዉ። ለዚህም ነዉ ሜርክል ከከፍተኛ የንግዱ ዘርፍ ልዑካን ጋ ወደቻይና የሚጓዙት። ከሜርክል ጋ ከሚጓዙት መካከል የዚመንስ፣ የፎልክስ ቫገን፣ ኤርበስ፣ ሉፍትሃንዛ እና የዶቼ ቫልን ዋና ኃላፊዎች ዋነኞቹ ናቸዉ። ቻይና ጀርመን ምርቶቿን በከፍተኛ ደረጃ ከምትሸጥባቸዉ ሃገራት ሁለተኛዋ ናት። በቅርብ አስርት ዓመታት ዉስጥም በርሊን ወደቤጂንግ የምትልከዉ እቃ በጣም እየጨመረ ነዉ። ባለፈዉ ጎርጎሪዮሳዊ ዓመት ብቻም ሽያጩ 67 ቢሊዮን ዩሮ ደርሷል። በተለይም የዛሬ አምስት ዓመት ገደማ በአዉሮጳ የፋይናንስ ቀዉስ በተከሰተ ጊዜ ከአዉሮጳ ገበያዎች ይልቅ የቻይና ለጀርመን ጠጋኝ ሆኖ ነዉ የተገኘዉ። የእስያዋ ባለግዙፍ ኤኮኖሚ ሀገር ቻይናም ብትሆን ባለፈዉ ዓመት ብቻ ወደጀርመን 73 ቢሊዮን ዩሮ የሚያወጣ ምርቷን ለጀርመን ሸጣለች። ምንም እንኳን የሜርክል የአሁኑ የቻይና ጉዞ ዋና ዓላማ የሁለቱን ሀገራት የኤኮኖሚ ትስስር ማጠናከር ላይ ያነጣጠረ ቢሆንም የምዕራቡን ዓለም ትኩረት የሳበዉ የዩክሬን ቀዉስ፣ የኢራቅ እና የሶርያ ወቅታዊ ሁኔታም ሳያነጋገራቸዉ እንደማይቀር ይታመናል። ቻይና ባላት የመልክዓ ምድር አቀማመጥ የዩክሬን ዉዝግብ ያሳሰባት አትመስልም የሚሉ ቢኖሩም ሜሪክል በዚህ አጋጣሚ ሁኔታዉ እንዳይባባስ ሩሲያ ላይ ተፅዕኖ እንድታደርግ ግፊት ሊያደርጉ እንደሚችሉ ይገመታል። ሴባስቲያን ሃይልማን እንደሚሉት ግን ቻይና በዓለም ዓቀፉ ፖለቲካ ረገድ የምትወስደዉ አቋም ከራሷ ጥቅም ጋ የተገናኘ ነዉ።

Merkel empfängt Xi Jinping
ምስል picture-alliance/dpa

«ቻይና በዚህ ዓለም ዓቀፍ የፖለቲካ መድረክ የራሷን ጥቅም ለማስከበር ከምር ነዉ ሁኔታዎችን በሚገባ የምትከታተለዉ። በአሁኑ ጊዜ የዩክሬንና ሩሲያን ከሚመለከተዉ ጉዳይ አኳያ ቻይና የራሷን ፖለቲካዊ ተግባር ማከናወን የምትችልበት ተጨማሪ ድርሻ ለማግኘት በቅታለች። እንደእኔ አመለካከት ቻይና በረቀቀ ዘዴ የፖለቲካ ጅዋጅዌ ጨዋታዉን ለመጫወት የሚያስችል ሁኔታና ቦታ አግኝታለች። የራሷን ጥቅም ማስጠበቅ የምትችልበትን ብልሃትና ዘዴ በማግኘቷም አዲስ ስልት መቀየሷ አልቀረም።»

መራሂተ መንግስት አንጌላ ሜርክል እሁድ ማታ ወደቤጂንግ በመጓዛም ከጠቅላይ ሚኒስትር ሊ ኪጊያንግ ጋ ይነጋገራሉ። ሰኞ ዕለት ደግሞ የቻይና ገዢ ፓርቲ ሊቀመንበርና የሀገሪቱ ፕሬዝደንት ከሆኑት ከሺ ፒንግ ጋ እንደሚገናኙ ይጠበቃል። ሜርክል ጉብኝታቸዉን የሚጀምሩት እንደጀርመን 80 ሚሊዮን ህዝብ በሚኖርባት የቻይና ቺንግዱ ከተማ ነዉ።

ማቲያስ ፎን ሃይን /ሸዋዬ ለገሠ

ተክሌ የኋላ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ