1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የጀርመናዊቷ ባለ በገና ጠጅ

ሐሙስ፣ ታኅሣሥ 7 2003

አንድ አባት ስለ ጠጅ፣ «ጠጅ እንዳል ተከበርክ ጥንት በዘመኑ፣ ዛሪ ነገሱብህ ዉስኪ ምናምኑ» ብለዉ ገጠመ አሉ! የቤተ-መንግስት መጠጥ የጨዋ መጠጥ በመባል የሚታወቀዉ ጠጃችን በባለሞያ በአዋቂ ሴት በመጣሉ በየቦታዉ ባለመገኘቱ

https://p.dw.com/p/Qd7B

«ጠጅ ለወረት፣ ጥሩ ወዳጅ ለችግር እለትም» ይባላል። ጠጅን አፍቃሪዎች ደግሞ ዛሪ ዛሪ «እኔስ አልተዉሽም ጠጅ የጥንቲቱ፣ ቀይጠዉ ቢያመጡሽ በስኳር በርዲቱ» እያሉ የብሄራዊዉን መጠጥ የጠጃችንን ጥራት ማቆልቆል ሲገጽሱም ይሰማል በዛሪዉ ጥንቅራችን እዚህ በጀርመን ጠጅ እያጣሉ ለተለያዩ አዉሮጻ አገራት የሚያከፋፍሉ ጀርመናዊት ባልቴት አግኝተን ልናስተዋዉቃችሁ ይዘናል!
በጀርመን በወይን ጠጅ ጠርሙስ ታሽጎ የሚሸጥዉ ጀርመናዊትዋ የሚጥሉት ጠጅ መጥርያዉ በገና ጠጅ ይሰኛል። የሃምሳ ዘጠኝ አመትዋ ጀርመናዊ ባልቴት ቪልሚነ ሽትዲአዉ የአርመን ክልስ ከሆኑት እናታቸዉ እና ከቤልጅጋዊ አባታቸዉ እዝያዉ ኢትዮጽያ ዉስጥ ተወልደዉ ሃያ አራት አመት እስኪሞላቸዉ ድረስ በኢትዮጽያ ኖረዋል የተማሩትም በፈረንሳዩ ሊሴ ገብረማርያም ትምህርት ቤት ነዉ። እንደ ወይዘሮ ቪሊ የጃንሆይ የስልጣን ዘመን አልቆ የደርግ ስርአተ ሲተካ ቤተሰቤ አገሪቷን ጥሎ ወደ ስዊዘርላንድ ለመግባት ተገደደ፣ ከዝያም በቬና ጀርመናዊዉን ባሌን ተዋዉቄ በፍንራንክፈርት ኑሮዪን ጀመርኩ ይላሉ። የአንደኛ እና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸዉን በሊሴ ገብረማርያም እንደጨረሱ ጎንደር ባህርዳር ጣና ሃይቅ አካባቢ በነበረ የአንድ ጣልያን ሆቴል ዉስጥ ቱሪስቶችን በማስተናገድ አገር በማሳየት አገልግለዋል። ደርግ ስልጣን ሲይዝ ቤታቸን ተወረሰ የምንኖርበት ቦታ ስናጣ አገራችንን ለቀቅን። አባቴ አፍሪቃን ሶሊዳሪቲ የሚባል ኢንሹራንስ ዉስጥ ነበር የሚሰሩት እናቴ ደግሞ የቤት እመቤት ነበሩ፣ ነገር ግን እናቴ ከማግባትዋ በፊት በኢትዮጽያን አየር መንገድ ጸሃፊ በመሆን አገልግላለች ሲሊ አጫዉተዉናል።
በበገና ጠጃቸዉ የሚታወቁት ወሮ ቪሊ ኢትዮጽያን አገር ቤት አዉሮጻዊዉን ደግሞ እንደ ኢትዮጽያዊ ፈረንጅ በማለት ነዉ የሚጠሩት። እኔና እናንተም የወሮ ቪሊን አንደበት ሰምተን ስራቸዉን አይተን ከአበሻ ብናሰልፋቸዉም መልካቸዉን አይተን ግን ከፈረንጅ መቀላቀላችን አንድና ሁለት የለዉም፥ «ጠጅና መኮንን፣ ደሃና ጎመን» የሚባለዉ አነጋገር ዛሪ ተቀባይነትን ባያገኝም፣ በወጋችን በዚያ በደጉ ዘመን «ጮማ ቆርጠን፣ ጠጅ ጠጥተን ማለፋችን» አንድና ሁለት የለዉም በወጋችን ማለቴ ነዉ። ጀርመናዊቷ የጠጅ ንግስት እኩያ ሁለት ሴት ልጆች አድርሰዉ የኮንፒዉተር እና ሶፍት ዊር ስራ ሲሰሩ መስራ ቤታቸዉ በመዘጋቱ ሰበብ ነዉ ጠጅን በመሸጥ ለመተዳደር የወሰኑት ወይዘሮ ቪሊ በመቀጠል፣ ኢትዮጽያ ስንኖር አያቴ ጥሩ ጠጅ ይጠምቁ ነበር። ሌላዉ ጠጅ በመጥመቅ ለምን የአገሪን አላስተዋዉቅም በሚል ይህንን ሃሳብ ይዤ ተነሳሁ ይላሉ።
ገደል ግቡ ጠጅ ቤት፣ ወንድ ይቅመስሽ ጠጅ ቤት፣ ይሸትሃል ቅመስ ጠጅ ቤት፣ ሳጠራ ጠጅ ቤት፣ ሹልክ ብሎ ቅምስ ጠጅ ቤት፣ እና ኦባማ ጠጅ ቤት፣ በአዲስ አበባችን ከሚገኙት ጠጅ ቤቶች ጥቂቶች ናቸዉ። በጀርመን የሚመረተዉ ደረቅ እና ለጋ ጠጅ ደግሞ በገና ጠጅ ይሰኛል። በገና ከኢትዮጽያ የሙዚቃ መሳርያዎች ቀዳሚዉን ቦታ ይዞ ስለሚገኝ ጠጅም የጨዋ የባላባት መጠጥ ተብሎ በመሰየሙ እና በታወቁ ይህንንም ታሪክ ተንተርሰዉ ስሙን እንዳወጡ ይገልጻሉ።
የጨዋ መጠጥ የባላባት መጠጥ በመባል የሚታወቀዉ ጠጅ ለገበያ ተብሎ ጥራቱ መቀነሱ በተለያዩ መንገዶች እዝያዉ ጠጅ ቤት በማሲንቆ ይገለጻል። «እወዳት ነበረ ጠጄን ከነጠጇ፣ ዘመን አበላሽቷት ተበላሸ ጠጇ» «ጠጁን ጥለሽዋል ከሲሚንቶ ከርድ ፣ አንዷን የቀመሰ ያሳየናል ድድ» «ጠጅሽን ጠጣነዉ፣ ጥንት በማር ዘመን፣ ዛሪ እያየነዉ ነዉ ከስኳር ሲመጠን» «ጠጅን ጠጣን ድሮ በማር ሲጠመቅ፣ የዛሪ ስኳርሽን ስጭዉ ለማያዉቅ» በሌላ በኩል ደግሞ ያማረ ጣዕም ያለዉ ጠጅ ሲገኝ ደግሞ « ጠጅ ይጠጣል ሰዉ ያለስጋቱ፣ ጠምቀሽዉ የለ ወይ ከማር ከንቢቱ» ይባልለታል፤ ጀርመናዊቷ ባልቴትም ጠጃቸዉ ከዉሃ ከስኳር ከማር በስተቀረ ሌላ ነገር እንደማይቀላቅሉ በጀርመን የጤና ጉዳይ ተመርምሮ ሰርተፍኬት ያለዉ አልኮል መጠጥ በመሆኑም ግብር እንደሚከፈሉ ሁሉ ገልጸዋል። እንደዉም አሉ ጀርመናዊቷ ጠጅ ጠማቂ አስር ቀናት ያህል የቀረዉ የፈረንጆቹን ገናን በማስመልከት የሚዘረጋዉ የገና ገበያ ላይ ገበና ጠጅን አቅርበዉ በጣም ተወዶላቸዋል። ጥራት ያለዉ የኢትዮጽያን ባህላዊ መጠጥም ለምዕራቡ አለም ለማስተዋወቅ ነዉ ምኞታቸዉ። «ጠጅ ለጨዋ ልጅ መጫወቻዉ፣ ለባለጌ ደግሞ መማቻዉ» እዲሉ ፈረንጆቹ የታሸገዉን የጠርሙስ ጠጅ እየገዙ ለገና በአል ስጦታም ይሰጣቱታል። ጠጁም የሚጣለዉ ትልቅ ፋብሪካ ዉስጥ በግዙፍ ደንበጃኖች ነዉ። በገና ጠጅ በተለያዩ አዉሮጻ አገራት በገፍ በመሸጥ ላይ ነዉ።

Begena Tej - äthiopischer Tej-Wein
ጠጅ ከፋብሪካ ወደ ገበያምስል DW/Hahn

በቤልጅግ፣ በኦስትርያ በለንደን በጀርመን ከፍተኛ ገበያ እንዳላቸዉ እና በተለይ የኢትዮጽያ የባህል ምግቤቶች ለሽያጭ እንደሚወስዱት ተናግረዋል። ይሁንና አንዱን ጠርሙስ ስንት እንደሚሸጡት ለተጠየቁት ጥያቄ የደንበኞቼን ገበያ ማበላሸት ስለማልፈልግ የምሰጥበትን ዋጋ መናገር አልፈልግም ግን በገበያ ቦታዎች ከአስር እስከ አስራሶስት ይሮ እንደሚሸጥ ሳይገልጹ አላለፉም።
«ጠጅ ይሻላል በመጠኑ የጨዋ ልጅ ይበልጣል በቀጭኑ» «ምን ብቀጥን ጠጅ ነኝ» «ጠጅ የወረት ወዳጅ» በሌላ አለም የሌለዉ ባህላዊ የኢትዮጽያ መጠጥ ጠጅ ብጫ አይደለም ጠላ፣ ቅራሪ፣ ቡቅሪ፣ ኮረፊ፣ ዱቃ በጣም ጥቂቶቹ የመጥ አይነቶች ሲሆኑ ከተለያዩ የእህል ዘሮች የሚሰሩ መኩሪያችን መለያዎቻችን በመሆናቸዉ እኛ ተተኪዎቹ አሰራሩን ወጉን መማር መጻፍ የሚገባን ይመስለናል። በተለያዩ ብሄር ብሄረሰቦች አካባቢስ የሚሰራዉ የምግብ አይነት ጥናት ተደርጎበታል? ሌላ ግዜ የምናነሳዉ ጥያቄ ይሆናል። ጀርመናዊትዋ ባለ ጠጅ ግን ይህን ለገበያ ልሰራ ስዘጋጅ ለሌዋ ኢትዮጽያዊ ወገኔም ሃሳብን ለማካፈል ፈልጌ ነዉ ይላሉ አዎ ይላሉ በመቀጠል ያለልን ችሎታ በሃሳብ ልንረዳዳ ይገባል። ኢትዮጽያ ዉስጥ የማናዉቀዉ ብዙ ነገር ልነሰራ የምንችለዉ ነገር አለ
የበገና ጠጅ ጠርሙስ ላይ የተለጠፈዉ መለያ አብዛኛዉን ግዜ በኢትዮጽያ አብያተ ክርስትያናት ግድግዳ ላይ የሚገኘዉ ጥንታዊ የሰዉ ስዕል በገና ሲደረድር። ጠጁንም ብቻ ሳይሆን ባህሉን አብሪ አያይዤ ለመግለጽ የሞከርኩት ነዉ ሲሉም ይገልጻሉ፥ በገንዘብ ሳይሆን በሃሳብ ብንረዳዳ ያለንን እዉቀት ለሌላዉ ብናካፍል ትልቅ ቦታ እንደርሳለን ሲሉም በማስረገጥ ይገልጻሉ። ታድያ አድማጮች በጀርመን ጠጅ በአንዲት ፈረንጅ ሲጣል ዘንድሮ ስድስተኛ አመቱን ደፍኖአል። ባልተቲትዋ እዚህ ላይ አሉ እዚህ ላይ አንዳንድ ኢትዮጽያዉያን ባይረዱኝ ኖሮ እዚህ ባልደረስኩ ነበር
በርካታ ኢትዮጽያዉያን ረድተዉኛል እዚህ በፍራንክፈርት መስፍን የላሊበላ ባለቤት የሰራሁትን ጠጅ ለፈረንጆቹ በማስረዳት ባህላችንን በመግለጽ ሃሳብ እየሰጠኝ እዚህ ደርሻለሁ፣ በኔዘርላንድም እንዲሁ ኢትዮጽያዉያን እህቶቼ ረድተዉኛል የነሱን እርዳታ ባላገኝ ኖሮ ምናልባትም እዙህ ባልደረስኪ ነበር።
የጠጅን መልካምነት ለመግለጽ የጠጅ ሳር ሽታ መልካም በመሆኑ የጠጅ ሳር መባሉን ተዘግቦአል። በቤተ-መንግስትም ጠጅ አሳላፊ፣ የጠጅ መልከኛ ይባል ነበር አሉ። አሳላፊዉ የሚጠጣበት ብርሌ ሹማምንቱ የሚጠጡበት ብርሌ እራሱ የተለያዩ መሆናቸዉ ዝክረ ነገር ላይ ተዝቦ እናገኛለን። ጀርመናዊቷ የበገና ጠጅ ባለቤት እንደጠጅ ሁሉ ሌላም ሌላም መስራት እና ማደግ እንችላለን ባይ ናቸዉ።
ከወይዘሮ ቬሊ ጋር ይህን ቃለ መጠይቅ አድርጌ በሹሩቤ ወይም በብርሌ ሳይሆን በፈረንጆቹ የወይን ጠጅ መጠጫ ብርጭቆ ለጤናችን ብዮ ከባልቴቱ ጋር አጋጭቼና ቀምሼ ደረቅ በገና ጠጅ አንድ ጠርሙስ፣ ለጋ የበገና ጠጅ አንድ ጠርሙስ ተሰጥቶኝ በናንተ በአድማጮቻችን ስም አመስግኜ ተለያየሁ! እኔም ጥንቅሪን እዚሁ ላይ ልቋጭ አዜብ ታደሰ ነኝ ጤና ይስጥልኝ! ሙሉዉን ጥንቅር ያድምጡ!

አዜብ ታደሰ
ሂሩት መለሰ