1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የጀርመኑ የልማት ድርጅት ስራና ገቢ

ዓርብ፣ ግንቦት 21 2001

ድርጅቱ እንደ አዉሮጳዉያኑ አቆጣጠር በ1975 ሲመሰረት የጀርመንን የልማት ተራድኦ መርሕ ገቢር እንዲያደርግ ታስቦ ነዉ።ሕጋዊ አወቃቀሩ የግል የምጣኔ ሐብት ተቋም ይዘት ሲኖረዉ ዋና ምግባር-ተጠሪነቱ ለኢኮኖሚ ልማትና ትብብር ሚንስቴርን ነዉ።

https://p.dw.com/p/I09Q

GTZ በሚል የጀርመንኛ ምሕፃረ-ቃል የሚጠራዉ የጀርመን የልማት ተራድኦ ድርጅት ባለፈዉ የአዉሮጳዉያኑ አመት 2008 1.2 ቢሊዮን ዩሮ ገቢ ማግኘቱን አስታወቀ።ይሕ የገቢ መጠን ከድርጅቱ የቀደሚ አመት ገቢ አስራ-ስድስት በመቶ ያሕል ጭማሪ ነዉ።GTZ ከጀርመን የልማት ተራድኦ ተቋማት ሁሉ በልማት-ትብብሩ መስክ ከፍተኛ አስተዋዕ የሚያደርግ ድርጅት ሲሆን የሚተዳደረዉ በሐገሪቱ መንግሥት ነዉ።የድርጅቱን አመታዊ የሥራ ክንዉን በተመለከተ ማቲያስ በሊንገር የዘገበዉን ነጋሽ መሐመድ አጠናቅሮታል።

GTZ በአዉሮጳዉያኑ 2008 1.2 ቢሊዮን ዩሮ ማስገባቱ ለድርጅቱ ሐላፊዎች አኩሪ ምግባር ነዉ-የሆነዉ።ሐላፊዎቹ ከትናንት በስቲያ ሮብ አመታዊ የሥራ-አፈፃፀም ዘገባቸዉን ሲያቀርቡ እንዳሉት የያዝነዉ የአዉሮጳዉያኑ አመት 2009 የድርጅታቸዉ ምግባርም ካምናዉ አያንስም።ምክንያቱም የድርጅቱ የበላይ ቤርንድ አይዘንብሌተር እንዳሉት አለምን የመታዉ የገንዘብ ቀዉስ በአዳጊዎቹ ሐገራትም በመባባሱ።

«በአጠቃላይ ሲታይ የአለም አቀፉ የልማት ተራድኦዉ ተፈላጊነት እየጨመረ እንደሚሔድ ልንገነዘብ ይገባል።ለዚሕ በርግጥ ተዘጋጅተናል።ይሁንና ከዚሁ ጋር የሚጣጣም ምግባር መከናወንም አለበት። የወቅቱ-አብይ ጉዳይ የገንዘብ-ሥርአትን ማዳበር መሆኑ ግልፅ ግንዛቤ ያስፈልገዋል።»

GTZ-አሁንም ቢሆን የጀርመን ብሔራዊ ባንክን ከመሳሰሉ የገንዘብ ተቋማት ጋር በመተባበር እየሰራ ነዉ።ድርጅቱ እንደ አዉሮጳዉያኑ አቆጣጠር በ1975 ሲመሰረት የጀርመንን የልማት ተራድኦ መርሕ ገቢር እንዲያደርግ ታስቦ ነዉ።ሕጋዊ አወቃቀሩ የግል የምጣኔ ሐብት ተቋም ይዘት ሲኖረዉ ዋና ምግባር-ተጠሪነቱ ለኢኮኖሚ ልማትና ትብብር ሚንስቴርን ነዉ።

ድርጅቱ በሁለት ሺሕ ስምንት ካስገባዉ ሰባ-ሰወስት ከመቶ የሚሆነዉ ገንዘብ የተገኘዉም ከዚሁ ሚንስቴር ነዉ።በሚንስቴሩ መስሪያ ቤት የGTZ አማካሪ ቦርድ አባል ኤሪሸ ሽታተር እንደሚሉት የድርጅቱ አኩሪ ዉጤት መሠረት የኢኮኖሚ ልማት ትብብር ሚንስትር የወይዘሮ ሐይደማሪ-ቪቾሪክ ሶይል መርሕ ነዉ።

«የዚሕ ጥሩ ዉጤት መሠረት የሚንስትሯ የተሳካ መርሕ ነዉ።ሚንስትሯ በግልፅ ተሟግተዉ ለሚንስቴር መስሪያ ቤቱ በጀት አስጨምረዋል።ይሕ የተደረገዉ ጭምሪ በጀት የGTZ ገቢ ከፍ እንዲል አድርጓል።»

GTZ ከልማት ተራድኦዉ ሚንስቴር በተጨማሪ ከጀርመን የተፈጥሮ ጥበቃና ዉጪ ጉዳይ ሚንስትሮች፥ ከአዉሮጳ ሕብረትና ከልማት ደንበኞቹ መንግሥታትም ገንዘብ ያገኛል።አሁን ደግሞ ሐላፊ ቤርንድ አይዘንብሌተር እንደሚሉት የአለም አቀፉ የልማት ተራድኦ ድርጅታቸዉ አዲስ አለም አቀፍ ደንበኛ አግኝቷል።

«ኮንትራት የሚሰጥ አዲስ ድርጅት አግኝተናል።የቢልና የማሊንዳ ጌትስ በጎ አድራጎት ድርጅት ከኛ መስራት ጀምሯል።የቀን ገቢያቸዉ ሁለት ዶላር የማይሞላ ሐምሳ-ሚሊዮን ያሕል ሰዎች የአነስተኛ የብድር አገልግሎት እንዲገኙ በጋራ እየሰራን ነዉ።»

ድርጅቱ አስራ-ሰወስት ሺሕ ሠራቶች አሉት።10 ሺዉ ድርጅቱ የሚሠራባቸዉ ሐገራት ዜጎች ሲሆኑ ሰወስት ሺሕዉ ጀርመናዊያን ባለሙያዎች ናቸዉ።አፍሪቃና አፍቃኒስታን ድርጅቱ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ ይንቀሳቀሳል።ካቀዳቸዉ ፕሮጄክቶች ሰማንያ-ሰወስት በመቶዉ ተሳክተዉለታል። ለሃያ በመቶ ጥቂት የሚቀረዉ ግን አልሆነለትም።ላለመሳካቱ ምክትል ሐላፊ ቮልፍጋንግ ሽሚት ምክንያት አላቸዉ።

Drogenzentrum Kabul der GTZ
የካቡል የGTZ ፀረ-አደንዛዥ ዕፅ ማዕከልምስል GTZ

«የምንሰራዉ በማደግ ላይ ባሉት ሐገራት ዉስጥ ነዉ።የምንሠራዉ እኛ ሥራችንን ለማከናወን የምንመኘዉ አይነት ዋስትና በሌለባቸዉ፥ በቅጡ ባልተረጋጉ ሐገራት ነዉ።ሥራችንን ሥንጀምር የሚኖረዉ መረጋጋት ባቀድነዉ መሠረት እስከንጨርስም ይኖራል ማለት የምንችልበት አካባቢያዊ ፀጥታ ላይኖር ይችላል።»

ለዚሕ የቅርቡ ምሳሌ ሲሪላንካ ናት።ድርጅቱ በሲሪላንካዉ የርስ በርስ ጦርነት ምክንያት በየመስኩ የነበሩ ሰራተኞቹን በሙሉ ወደ ርዕሠ-ከተማይቱ ማዛወር ግድ ነበረበት።

ማቲያስ በሊንገር/ነጋሽ መሐመድ

ተክሌ የኋላ