1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የጀምስ ቤከር ተልዕኮ እና የኢራቅ የብድር ዕዳ ቅነሳ

ረቡዕ፣ ታኅሣሥ 7 1996
https://p.dw.com/p/E0g5
በኢራቅ የአሜሪካ ልዩ መልክተኛ ጄምስ ቤከር ኢራቅ ያለባት የውጭ ዕድ እንዲቀነስላት የያዙት የመግባባት ተልዕኮ እየተሳካላቸው ይመስላል ። የፓሪስ የአበዳሪዎች ክለብ አባላት ከሆኑት ሀገራት መካከል ፈረንሳይ እና ጀርመን የአሜሪካንን ጥያቄ በመቀበል ባወጡት የጋራ መግለጫ ኢራቅ ያለባት ዕዳ እንዲቀነስ ተስማምተዋል ። ቤከር ይህንኑ ተልኳቸውን በመቀጠል ከሩሲያ ፣ ከጣሊያን እና ከብሪታንያ ባለስልጣናት ጋር ይነጋገራሉ ። በዩናይትድስቴትስ ፣ በፈረንሳይ እና በጀርመን ከተሞች የወጣው የጋራ መግለጫ እንደሚለው ሃገራቱ በመጪው የአውሮጳውያን ዓመት ኢራቅ ከክለብ አበዳሪ ሃገራት የተበደረችው ዕዳ እንዲቀነስላት ተገቢ ውሳኔ አስተላልፈዋል ። መግለጫው ለኢራቅ የዕዳ ቅነሳ ማድረግ ህዝቧ ነጻ እና የበለፀገች ኢራቅን መገባንት እንደሚያስችለውም ጠቁሟል ። የበለፀገች ኢራቅን ለመገንባት ያስችላል ከተባለለት እዳ ላይ እያንዳንዳቸው አበዳሪ ሃገራት የሚቀንሱት መጠን ግን አሁን አልታወቀም ። የጋራ መግለጫው እንደሚለው በፓሪስ ክለብ ሃገራት መካከል ወደፊት በሚደረገው ስምምነት በምን ያህል መቶኛ ስሌት የኢራቅ ብድር እንደሚቀነስ ይወሰናል ። ኢራቅ ከአበዳሪው ክለብ አባላት የተበደረችው የገንዘብ መጠን ወደ አንድ መቶ ሃያ ቢሊዮን ዶላር እንደሚደርስ ሲገለፅ የቤከር ተልኮም ለኢራቅ ከፍተኛ ብድር ሰጥተዋል ተብለው ወደ ተረጋገጠላቸው ሃገራት ነው ። የኢራቅ ጦርነትን አጥብቀው የተቃወሙት እና ወታደራዊ ኃይል እና መሳሪያ አናዋጣም ያሉት ፈረንሳይ እና ጀርመን ከኢራቅ መልሶ ግንባታ በመገለላቸው የኢራቅ የብድር ዕዳ እንዲቀነስ የቀረበውን የአሜሪካ ጥያቄ አይቀበሉም የሚል ግምት ነበር ። የዩናይትድስቴትስ ባለስልጣናት ጦርነቱ ከመካሄዱ በፊት ኢራቅን መልሶ የመገንባት ተግባር እራሱን በራሱ ችሎ ይሃዳል ሲሉ እንዳልቆዩ ሁሉ አሁን ብድር እንዲቀነስ መጠየቃቸው ያስተዛዝባል በማለት የተቹ ጀርመናውያንም አሉ ። የኤኮኖሚ ተራድኦ እና የልማት ትብብር ሚንስትር ሃይደማሪ ቪኮሬች ሶይል አሜሪካዊው ቤከር ወደ ጀርመን ከማቅናታቸው በፊት በሰጡት አስተያየት የጀርመን ተቋማት ከኢራቅ መልሶ ግንባታ እንዲገለሉ በመደረጋቸው ሀገራቸው የቤከርን ጥያቄ ተቀብላ እንደማታስተናግድ ገልፀው ነበር ። ሆኖም ዋሽንግተንን ጨምሮ ሶስቱ ሃገሮች ባወጡት የጋራ መግለጫ ያለቅድመ ሁኔታ የዕዳን ቅነሳ ለማድረግ መስማማታቸው ተገልጿል ። ያም ሆኖ የመራሄ መንግስት ጌርሃርት ሽረደር ቃል አቀባይ እንዳስታወቀው የጀርመን ተቋማት የመገለላቸው ጉዳይ ከቤከር ጋር በተደረገ ውይይት ተነስቶ ነበር የሀገሪቱ የመከላከያ ሚንስትር ፒተር ሽትሩከር ቃል አቀባይ ደግሞ እንደገለፀው የቤከር ጉብኝት ዩናይትድስቴትስ የያዘችውን አቋም ሊያስለውጥ ይችላል የሚል ተስፋ አለ ። ቤከር ግን በበርሊን ቆይታቸው ስለ ዕዳው ቅነሳም ሆነ በመልሶ ግንባታ የመሳተፍ ጉዳይን አስመልክቶ የሰጡት አስተያየት የለም ። ቤከር በአምስት ሀገራት የሚያደርጉት የማግባቢያ ዘመቻ ለኢራቅ ስምንት ቢሊዮን ዶላር ባበደረችው ሩሲያ ዘንድም ጥያቄ አስነስቷል ። ሩሲያ ከኢራቅ የመልሶ ግንባታ ፕሮግራም መገለሏ እስከተገለፀላት ድረስ ብድር ቅነሳ እንዲኖር የስምምነት ሰነድ ለመጻፍ እንደማትነሳሳ አስታውቃለች ። ይህ አቋሟ እርግጠኛ መሆኑ የሚታወቀው ግን ቤከር ሞስኮ ገብተው ከባለስልጣናቷ ጋር ከተወያዩ በኃላ ነው ። አስራ ስምንት ቢሊዮን ዶላር ከተመደበለት የኢራቅ መልሶ ግንባታ ሶስቱ የኢራቅ ጦርነት ተቃዋሚ ሀገራት የመገለላቸው ጉዳይ እንደገና ይታይ እንደሆነ ትላንት የተጠየቁት የዩናይትድስቴትስ የመከላከያ ሚንስትር ራምስ ፊልድ ውሳኔው የፔንታጎን ባለመሆኑ የሚያውቁት ነገር እንደሌለ ገልፀው እንደገና ማሻሻያ የሚደረግ ከሆነ ግን ስህተት ይፈጠራል ሲሉ በድፍኑ አስጠንቅቀዋል ። ይህ የራምስ ፊልድ ማስጠንቀቂያ ዩናይትድስቴትስ የኢራቅን ብድር ለማስቀነስ ስትል የአቋም ለውጥ ትከተላለች ማለት እንዳልሆነ የሚያሳይ ነው ። ለማንኛውም ቤከር ከበርሊን ወደ ጣሊያን ዛሬ ሄደዋል ። ቀጣዩ ጉዟቸው ሞስኮ ሲሆን ያገኙትን ምላሽ ይዘው የጉዟቸውን መጨረሻ የሚያደርጉት የኢራቅ ጦርነት ተባባሪ በሆነችው በብሪታንያ ነው ።