1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የዶይቼ ባንክ ኪሳራ

ረቡዕ፣ ጥር 25 2008

ኢትዮጵያ ለአስር አመታት የሚቆየውን የአንድ ቢሊዮን ዶላር ቦንድ ለዓለም ገበያ ስታቀርብ በአገበያይነት ከመረጠቻቸው የፋይናንስ ተቋማት መካከል አንዱ የጀርመኑ ዶይቼ ባንክ ነበር። ኢትዮጵያ ለሁለተኛ የቦንድ ግብይት ወደ ዓለም አቀፉ ገበያ ለመግባት ሽር ጉድ ስትል ግን ዶይቼ ባንክ በኪሳራ እና የአደረጃጀት ለውጥ ውስጥ ነው።

https://p.dw.com/p/1HoH4
Deutschland Deutsche Bank Schriftzug Symbolbild Verluste
ምስል Reuters/K. Pfaffenbach

የዶይቼ ባንክ ኪሳራ

የጀርመኑ ግዙፍ ባንክ ለሰራተኞቹ እና ለደንበኞቹ ማለቂያ የሌለው መርዶ እያሰማ ነው። ባንኩ ዘጠኝ ሺህ ሰራተኞቹን በያዝነዉ የጎርጎሮሳዊው 2016 ዓ.ም. ከሥራ ያሰናብታል። ከእነዚህ መካከል አራት ሺህ ያክሉ በጀርመን የሚገኙ ናቸው። የዶይቼ ባንክ እህት ኩባንያ የሆነው ፖስት ባንክ ይሸጣል። ባንኩ ባለፈው የጎርጎሮሳውያኑ 2015 ዓ.ም. የ6.7 ቢሊዮን ዩሮ ወይም 7.3ቢሊዮን ዶላር ኪሳራ እንደገጠመው ያስታወቀ ሲሆን አንድ አክሲዮን በዓለም ገበያ ያለው ዋጋም ከ50 ዶላር ወደ ወደ 17 ዶላር አሽቆልቁሏል። ባለፈው ሳምንት ከባንኩ ከፍተኛ አመራሮች ጋር ከጋዜጠኞች ፊት የቀረቡት ጆን ክራየን ለጊዜው የዶይቼ ባንክ ተባባሪ ሥራ አስፈጻሚ ናቸው።

ባንኩ ከዚህ ቀደም በፈጸማቸው የህግ ጥሰቶች በቀረቡበት ክሶች እና ቅጣቶች ምክንያት በዓመቱ አራተኛ የሥራ ዘመን ሊያተርፍ ካቀደው የገንዘብ መጠን 1.2 ቢሊዮን ዩሮ ቅናሽ ማሳየቱን አስታውቋል። ባንኩ በጎርጎሮሳዊው 2015 ዓ.ም ለገጠሙት የፍርድ ቤት ሙግቶች ያወጣው የገንዘብ መጠን በአጠቃላይ 5.2 ቢሊዮን ዩሮ ደርሷል። በጎርጎሮሳዊው 2014 ዓ.ም. አራተኛ የሥራ ዘመን 441 ሚሊዮን ዩሮ ትርፍ አስመዝግቦ የነበረው ዶይቼ ባንክ በ2015 ተመሳሳይ የሥራ ዘመን ብቻ 2.1 ቢሊዮን ዩሮ ኪሳራ ገጥሞታል። በጎርጎሮሳዊው 2014 ዓ.ም. ባንኩ 1.7 ቢሊዮን ዩሮ የተጣራ ትርፍ አግኝቶ ነበር።

John Cryan Deutsche Bank Pressekonferenz Frankfurt am Main
የዶይቼ ባንክ ተባባሪ ሥራ አስፈጻሚ ጆን ክራየንምስል picture-alliance/dpa/B.Roessler

ባንኩ ከገጠመው ቀውስ ለመውጣት ለሚያደርገው የአደረጃጀት ለውጥ እና ከሥራቸው ለሚሰናበቱ ሰራተኞች ክፍያ 800 ሚሊዮን ዩሮ እንደሚያስፈልገውም ባንኩ ጨምሮ ገልጧል። ዶይቼ ባንክ አሁንም ያልተዘጉ የክስ መዝገቦች እና ምርመራዎች አሉበት። እስካሁን ባንኩ በህግ የተቀመጠ አማካኝ የወለድ ምጣኔን በመተላለፍ እና ኢራንን በመሰሉ አገሮች ላይ የተጣሉ ማዕቀቦችን በመተላለፍ በቢሊዮን የሚቆጠር ዩሮ ተቀጥቷል።አግባብ ያልሆነ የውጭ ምንዛሪ ግብይት ይፈጽማል እየተባለም ይወቀሳል። የባንኩ የሩሲያ ቢሮ ሰራተኞች ለደንበኞቻቸው ህገ-ወጥ የገንዘብ ዝውውር ፈጽመዋል የሚል ሌላ ክስም አለባቸው።

ባንኩ የገባበትን ቀውስ በማሳወቅ የአስር አመት ኃላፊነታቸውን የጀመሩት ተባባሪ ሥራ አስፈጻሚ ጆን ክራየን ገና ካሁኑ ጥብቅ እርምጃዎች በከፍተኛ ጥንቃቄ ሊተገበሩ እንደሚገባ ባለፈው ሳምንት አስታውቀዋል። ጆን ክራየን ወደ አዲሱ ቢሯቸው ገና ከመግባታቸው ከወሰዷቸው እርምጃዎች መካከል የባንኩ ከፍተኛ አመራሮች የሚገባቸውን ጉርሻ አለያም ቦነስ ሙሉ በሙሉ በመሰረዝ ነበር።

«በ2016 እና ወደ ፊት የባንኩ ወጪዎች ፈተና ይሆኑብናል። በመጀመሪያ ወደ አንድ ቢሊዮን ዩሮ የሚጠጋ ገንዘብ ባንኩን እንደገና ለማደራጀት እና ለሚሰናበቱ ሰራተኞች ወጪ እናደርጋለን። በተለያዩ ምክንያቶች የ2016 ወጪያችን ከፍ እንዳለ ይቆየናል ብለን እንገምታለን። የሰራተኞቻችን የደሞዝ ክፍያ ለማስተካከል 200 ሚሊዮን ዩሮ ያስፈልገናል። ለሶፍትዌሮች ተጨማሪ 300 ሚሊዮን ዩሮ ወጪ እናደርጋለን። ትኩረታችን የባንኩን አደረጃጀት በመቀየር ስለምናደርግ በቴክኖሎጂ እና ለመሰረተ-ልማት ስራዎች አስፈላጊ መዋዕለ ንዋይ እናፈሳለን። እነዚህን ሥራዎች በወጪ ቆጣቢ እርምጃዎች ተግባራዊ ለማድረግ አቅደናል። አሁንም ይሁን በመጪዎቹ አመታት የባንኩን ወጪዎች መቀነስ ዋንኛ ትኩረታችን እንደሚሆን ላረጋግጥላችሁ እወዳለሁ።»

Infografik Deutsche Bank Gewinne 2006-2015 Englisch

ባለፉት ሶስት አመታት በበርካታ ክሶች እና ውንጀላዎች ስሙ ሲብጠለጠለል የቆየው ዶይቼ ባንክ ጥሷቸዋል ለተባለባቸው የባንክ አሰራሮች እና የሥነ-ምግባር ህግጋት መቀጫ ከ12 ቢሊዮን ዩሮ በላይ ወጪ አድርጓል። ወደ ፊት ለሚጠብቁት የፍርድ ቤት ክርክሮች እና ቅጣቶች በቢሊዮን የሚቆጠር ዩሮ መድቧል። አዲሱ ተባባሪ ሥራ አስፈጻሚ ጆን ክራየን የባንኩ ወቅታዊ ኪሳራ እና ቀውስ የከረመ ነው የሚል እምነት እንዳላቸው ጠቆም አድርገዋል።

«ያለፉት ሁለት አስርት አመታት በርካታ ግቦች እና የማስፈጸሚያ ስልቶች የታቀደቡቸው ቢሆኑም እቅዶቹ ያን ያክል ትርጉም ወዳለው ትግበራ አልተቀየሩም።»

ባንኩ የሰራተኞቹን ቁጥር በመቀነስ የወሰደው እርምጃ በአክሲዮን ገበያ ዋጋውን ከፍ በማድግ ትርፋማ በሆነ ነበር-ቢያንስ እንደ ባለሙያዎቹ እምነት። በሆሄናሄም ዩኒቨርሲቲ የባንክ አገልግሎት ባለሙያ የሆኑት ሐንስ ፒተር በርግሆፍ ዶይቼ ባንክን ለመታደግ መወሰድ ያለባቸው እርምጃዎች በርካታ መሆናቸውን ይናገራሉ።

«አንድ ብቻ ሳይሆን በርካታ እርምጃዎች መወሰድ አለባቸው። አብዛኞቹ ደግሞ ከባንኩ የአሰራር ባህል ጀርባ ያሉ ናቸው። ዶይቼ ባንክ ወግ አጥባቂ እና ጥንቁቅ መሆን ይኖርበታል። ለደንበኞቹም የተሻለ አስተማማኝ ሊሆን ይገባል። በባንኩ ላይ ኪሳራ የፈጠሩት ችግሮች በሙሉ የተከሰቱት ከ2007/8 የፋይናንስ ቀውስ ጀምሮ ነው። ደንበኞች ዶይቼ ባንክ ላይ እምነት የላቸውም። ትርፋማ ለመሆን ይህ እምነት መመለስ አለበት። ችግሩ የባንኩ ባለድርሻዎች አሁን ገንዘብ ማግኘት ስኬታማ መሆን ያምራቸዋል።ትርፍ ለማግኘት የታቀደ የአሰራር ስልት አሁን ተግባራዊ ከተደረገ ውድቀት ይከተላል። ምክንያቱም እንዲህ አይነት አሰራር ረጅም ጊዜ ይፈልጋል።»

እስከ መጪው ግንቦት ወር ድረስ በተባባሪ ሥራ አስፈጻሚነት የሚቆዩት ጆን ክራየን ዶይቼ ባንክ ከገጠመው ቀውስ ሊታደጉት የሚችሉ የእሳት አጥፊ ባለሙያ ተደርገው ተቆጥረዋል። በአውሮጳ የባንክ አገልግሎት ውስጥ የከበረ ስም ያላቸው ክራየን በዶይቼ ባንክ ደንበኞች ዘንድ እምነት እንዳላቸው ይነገራል። ሮበርት ሐልቨር የፋይናንስ ተንታኝ ናቸው።

«ሚስተር ክራይን ካሁን ቀደም ዩቢኤስ ባንክ ከገባበበት ውድቀት ታድገውታል። አንዳንድ ሰዎች 'የተበላሸን አራቂ'ይሏቸዋል። እኔ ግን እንደ ዳግም ፈጣሪነው የምቆጥራቸው። በመጀመሪያ አስቀያሚ ጉዳዮችን መፍትሔ በመስጠት በዘላቂነት ለተሻለ ስራ አብረዋቸው የሚሰሩትን የሚለዩ ሰው ናቸው።»

Frankfurt Zentrale der Deutschen Bank
ምስል picture-alliance/U. Baumgarten

ባገለገሉባቸው ባንኮች እና የፋይናንስ ተቋማት ዘንድ በገንዘብ ቆጣቢነታቸው እና ወጪ ቅነሳ የሚታወቁት ጆን ክራይን በእርግጥም የስዊዘርላንዱ ዩ.ቢ.ኤስ. በአንድ ወቅት ከገባበት ቀውስ ታድገውታል። ከጀርመን የመዋዕለ ንዋይ እና ብድር አቅራቢ ተቋማት መካከል ለግዙፉ ዶይቼ ባንክ ቀውስ ሁነኛው መፍትሔ መሆናቸውን የሚጠራጠሩ ፤እርምጃና ውሳኔዎቻቸውን አብዝተው የሚተቹም አልጠፉም። ከእነዚህ መካከል ዘላቂ እድገትን የሚያቀነቅነው የዎርልድ ፊውቸር ካውንስል የፖሊሲ ኦፊሰሯ ሱሌይካ ሬይኔርስ አንዷ ናቸው።

«ዶይቼ ባንክ ለኢኮኖሚው አስጊ መሆኑን አሁንም ይቀጥላል። አሁንም ትኩረት ያደረገው በፋይናንስ አሰራሩ ላይ አላስፈላጊ አደጋ በሚፈጥሩት በቅጥ ያጣ የደህንነት ሥራ እና የውጭ ምንዛሪ ግብይት ላይ ነው።»

ብሪታኒያዊው ጆን ክራይን የካምብሪጅ ዩኒቨርሲቲ ምሩቅ ናቸው። ስራቸውን በፋይናንስ ኦፊሰርነት በለንደኑ በኤስ.ጂ. ዎርበርግ የጀመሩ ሲሆን በሙኒክ የኢንቨስትመንት ባንክ ኃላፊ ሆነውም ነበር። የጀርመኑን ዶይቼ ባንክ በጎርጎሮሳዊው 2013 ዓ.ም. የተቀላቀሉት ክራይን እንደ ሮበርት ሐልቨር ባሉ የፋይናንስ ተንታኞች ለጀርመን የባንክ አገልግሎት ዘርፍ ሁነኛ ሰው እንደሆኑ እምነት ተጥሎባቸዋል። ይህ ለሱሌይካ ሬይኔርስ የሚዋጥ አይነት አይመስልም። ወ/ሮዋ ክራይን አሁን በባንኩ መውሰድ የጀመሯቸውን እርምጃዎች አብዝተው ይተቻሉ።

«ክራይን ክፍያን በተመለከተ ሁነኛው የሥራ አስፈጻሚ አይደሉም። አሁን እንኳ የሰራተኞችን ክፍያ የሚቀንስ ውሳኔ አስተላልፈዋል። በሌላ በኩል የተጋነነውን የቦርድ አባላት ክፍያ በተመለከተ ምንም የወሰኑት ነገር የለም።»

ከዘጠኝ አመት በፊት የዶይቼ ባንክ አንድ የአክሲዮን ዋጋ ከአንድ መቶ ዩሮ በላይ ደርሶ ነበር። ግዙፉ የጀርመን የአበዳሪ ተቋም በተለያዩ የዓለም ክፍሎች የከፈታቸው ቢሮዎች በሁሉም የሥራ ዘርፎች ትርፋማ ነበሩ። ባንኩ በጎርጎሮሳዊው 2007 ዓ.ም. ስድስት ቢሊዮን ዩሮ ያተረፈ ሲሆን የዚያን ጊዜው ዋና ሥራ አስፈጻሚ ጆሴፍ አከርማን ስኬታማ ተብለው 12 ሚሊዮን ዩሮ ጉርሻ ወደ ኪሳቸው አስገብተዋል። ከዘጠኝ አመታት በኋላ ግን ነገሮች ሁሉ የተገላቢጦሽ ይመስላሉ። ባለፈው ሳምንት በነበረው ጋዜጣዊ መግለጫ ለመሆኑ ዶይቼ ባንክ ወደ ትክክለኛው አሰራር መቼ ይመለሳል ብለው ያምናሉ?ተብለው የተጠየቁት ክራይን የሰጡት መልስ «የእምነት ጥያቄ ነው ብዬ አላምንም። ልናሳያችሁ ይገባል ብዬ አምናለሁ።»የሚል ነበር።

ክራይን ምንም ይበሉ ምን መጪው ጊዜ ለዶይቼ ባንክ የፈተና ይመስላል። ታዋቂው የፋይናንሺያል ታይምስ አርታዒ ፓትሪክ ጄንኪንስ «አሁን የዶይቼ ባንክ ባለድርሻ ለመሆን ሁነኛው ጊዜ ነው። ነገር ግን ባንኩ ወደ ባሰ ውጥንቅጥ ላለመግባቱ ማረጋገጫ የለም።» ሲል የጻፈው ለዚህ ይመስላል።

እሸቴ በቀለ

ነጋሽ መሐመድ