የዶቸ ቬለ ሽልማትን ቻይናዊዉ ደራሲ አሸነፈ
ማክሰኞ፣ ሚያዝያ 29 2005
ዶቸ ቬለ ለአምደ መረብ-ፀሐፊዎችና ዓምደኞች በየዓመቱ ከሚሠጠዉ ሽልማት የዘንድሮዉን (2013)ቻይናዊዉ አምደኛ እና ደራሲ ሊ ቼንግፔንግ አሸነፈ።ዶቸ ቬለ Bobs ወይም የምርጥ ብሎግ ሽልማት የሚለዉን ሽልማት በመላዉ ዓለም ከሚገኙ የአምደ መረብ አምደኞች አወዳድሮ ይሸልማል።የዘንሮዉን ሽልማት ያሸነፈዉ ሊ ብሎገር፥ ደራሲና ሐያሲ ነዉ።ሸላሚዎቹ ዳኞች እንዳሉት የመንግሥትን አሠራሮች በመተቸት የሚታወቀዉ ሊ ከሐገሩ ዜጎች በተለይም ከወጣቶቹ ከፍተኛ ዝናንና አድናቆትን ያተረፈ ነዉ።የሊ ብሎግ ከሰባት ሚሊዮን በላይ አባላት አሉት።የዶቸ ቬለዋ የቋቋዎች አገልግሎት ሐላፊ ወይዘሮ ኡተ ሼፈር እንደሚሉት ደግሞ ሊን የመሳሰሉ ወጣቶች በንቃት የሚሳተፉበት የአምደ መረብ አገልግሎት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየሰፋና እያደገ ነዉ።
«ቦብስ 2013 ያሳየን፥ የአምደ መረብ እንቅስቃሴ ማለት የአምደ-መረብ ፖለቲካዊ እና ማሕበራዊ ሥራ መቀየሩን ነዉ።እንቅስቃሴዎቹና ተሳታፊዎቹ ፈጣሪዎች፥ተንቀሳቃሳሾች፥ሁሉን መገናኛ ዘዴዎች ያሰባጠሩ፥ በቴክኒክ ረገድም ባለ ብዙ ገፅታ ሆነዋል።ይሕ ማለት መልክና ቅርፃቸዉ ተቀይሯል ማለት ነዉ።በዚሕ ዓመት ለፕሮጀክታችን በጣም ከፍተኛ የሆነ ጉጉት አይተናል።ይሕ የሚያሳየዉ የአምደ መረብ ንቅናቄ በመላዉ ዓለም ምን ያሕል ተፈላጊ እንደሆነ ነዉ።»
ዓለም አቀፉ የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች ድርጅት ድንበር የለሽ ዘጋቢዎች ደግሞ የዘንድሮዉን የአምደ መረብ ሽልማቱን ለቶጎዊቷ ጋዜጠኛ ለ ፋቢ ኮሚሲ ሰጥቷል።ጋዜጠኛ ፋቢ የቶጎ ጋዜጠኞች የሚደርስባቸዉን ግፍና በደል በአምደ መረቧ በማጋለጥና የመንግሥትን የሐይል እርምጃ በመተቸት የታወቀች ጋዜጠኛ ነኝ።
«ብሎጌ ከሁሉም በላይ የቶጎ ጋዜጠኞች ያሉበትን ሁኔታ የሚያንፀባርቅ ነዉ።ፕሬሱ እዚሕ ከፍተኛ ችግር አለበት።እኛ ሐገር ዲሞክራሲ የለም።ይሕን ብሎጎ መምራት ከጀመርኩ ጥቂት ዓመታት ሆኖኛል።የዶቸ ቬለን ትኩረት ያገኛል ብዬ አስቤ ግን አላዉቅም ነበር።በጣም ተደስቻለሁ፥ ኮርቻለሁም።»
ትላለኝ ፋቢ።የዶቸ ቬለ ለምርጥ ማሕበራዊ እንቅስቃሴ፥ ለምርጥ ፈጠራ፥ እና ለምርጥ የጀርመንኛ ቋንቋ ብሎግም የቦብስ ሽልማትን ሰጥቷል።
ነጋሽ መሐመድ
ልደት አበበ