1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የዳቮስ ዓለምአቀፍ የኤኮኖሚ መድረክ

ሐሙስ፣ ጥር 25 1998
https://p.dw.com/p/E0e2
ቻንስለር ሜርከል በዳቮስ ንግግር ሲያሰሙ
ቻንስለር ሜርከል በዳቮስ ንግግር ሲያሰሙምስል AP

የመድረኩ ውይይት ባለፈው ዓመት አፍሪቃን ዓቢይ ማተኮሪያው ማድረጉ ሲታወስ ዘንድሮ ማዕከላዊው ጉዳይ እየተፋጠነ የመጣው የቻይናና የሕንድ የኤኮኖሚ ዕድገት ነበር። ልዑካኑ የቅርቡን የፍልሥጤም ምርጫ ጨምሮ በመካከለኛው ምሥራቅ ሁኔታና ማወዛገቡን በቀጠለው የኢራን የአቶም መርሃ-ግብር፤ እንዲሁም በዓለም ንግድ ድርድር ላይ ማተኮታቸውም አልቀረም።

የዳቮሱ ዓለምአቀፍ መድረክ ከሣምንት በፊት በተከፈተበት ወቅት እንደተጠበቀው ዋናው መነጋገሪያ ነጥብ ተጎታቹ የምዕራቡ ዓለም የኤኮኖሚ ዕድገትና ሳይለዝብ የቀጠለው የሥራ አጥነት መናር ችግር ነበር። በጉባዔው የመክፈቻ ንግግር ያሰሙት የጀርመኗ ቻንስለር አንጌላ ሜርከል ችግሩን ለመፍታት የፈጠራ አስተሳሰብ መዳበርና የሃሣብ ፉክክር የሰመረበት ማሕበራዊ የገበያ ኤኮኖሚ ስርዓት መስፈን እንደሚኖርበት አስገንዝበዋል።
ሜርከል በኤኮኖሚ ዕድገት ማቆልቆልና አምሥት ሚሊዮን በሚጠጋ ሥረ-አጥ ችግር ተወጥራ የምትገኘውን ጀርመንን በዚህ መንገድ መልሰው በአውሮፓ ቀደምት ከሆኑት ሶሥት አገሮች መካከል ለማሰለፍ ቆርጠው መነሣታቸውን ሳይናገሩም አላለፉም። የመድረኩ ተሳታፊዎች ምንም እንኳ ለጀርመኗ ቻንስለር ንግግር ክብደት ቢሰጡና አልፎ አልፎ አድናቆት ቢገልጹም የችግሩ መንስዔም ሆነ መፍትሄው በአጠቃላዩ የዓለም ኤኮኖሚ ትስስር በግሎባላይዜሺን ላይ ጥገኛ በመሆኑ መልሱ በብሄራዊ ደረጃ በሚወሰዱ ዕርምጃዎች መገኘቱ ሲበዛ ያጠያይቃል።
አለበለዚያ በአሢያ ሁለቱ ግዙፍ አገሮች ቻይናና ሕንድ የሚያደርጉት የተፋጠነ የኤኮኖሚ ዕድገትና በዚሁ መጠን ያዳበሩት በራስ መተማመን ምዕራቡን ዓለም ማስደንገጥ ባልያዘና የዘንድሮው መድረክ ዓቢይ መነጋገሪያ ባልሆነም ነበር። የእሢያው መንግሥታት በተለይም የሕዝባዊት ቻይና ፈጣን ዕድገት በዓለም ኤኮኖሚና ንግድ ላይ የቆየውን ሚዛን እየቀየረ በመሄድ ላይ መሆኑ የተሰወረ ነገር አይደለም። በኢንዱስትሪ ልማት የበለጸጉት መንግሥታት የገጠማቸው ፉክክር እየበረታ ሲሄድ ነው የሚታየው።

ለመሆኑ የቻይና የምጣኔ-ሐብት ጥንካሬ እስከምን ድረስ ነው? የሩቅ-ምሥራቃዊቱን አገር የኤኮኖሚ ሃይል በጥቂት ዓመታት ውስጥ ከበለጸጉት መንግሥታት ለማስተካከል ቆርጠው ከተነሱ ሰንበት ያሉት ቻይናውያን በዘልማድ አርቆ ባስተዋለ ስልታዊ የአሠራር ብቃት የሚታወቁ ናቸው። ሰለዚህም የዳቮሱ መድረክ ከመከፈቱ በፊት በጊዜው አዲስ የኤኮኖሚ ሰንጠረዝ ይዘው ብቅ ማለታቸው ብዙም አያስደንቅም።
ይፋ በወጣው አዲስ መረጃ መሠረት የሕዝባዊት ቻይና አጠቃላይ ብሄራዊ ምርት ባለፈው 2005 ዓ.ም. 9.9 በመቶ ዕድገት አሣይቷል። የኢንዱስትሪው ምርት እንዲያውም 11 በመቶ! ቻይና በአልግሎት ሰጪው ዘርፍም እየገፋች በመሄድ ከታሰበው በላይ ዕድገት ማሣየቷን ቤይጂንግ ባለፈው ታሕሣስ ወር ያወጣችው ከፍ ብሎ የታረመ መረጃ አመልክቷል። በዚሁ የቻይና ብሄራዊ ኤኮኖሚ በዓለም ላይ ወደ አራተኛው ደረጃ ከፍ ሊል መብቃቱ ነው የሚነገረው።
በነገራችን ላይ ይህን ሁለንተናዊ ዕርምጃ ዕድገቱ ባለፉት ዓመታት በአንድና ሁለት ከመቶ ተወስኖ የቆየው ምዕራቡ ዓለም ሊደርስበት ቀርቶ ሊያልመው እንኳ አይችልም። ቢሆንም በሌል በኩል በቻይና እየተፋጠነ የሚታየው ዕድገት ተጋኖ መታየቱ አልቀረም የሚሉ ወገኖችም አልታጡም። ለምሳሌ ያህል በሻንግሃይ የዓለም ንግድ ድርጅት አማካሪ ቢሮ ባልደረባ ፔንግ ጁን ዕድገቱን የሚጠቁሙት አሃዞች የሕብረተሰቡን ሃቅ የሚሸፋፍኑ ናቸው ይላሉ።

“በአገራችን ሁለት መቶ ሚሊዮን ሕዝብ የሚኖረው ከአንድ ኤውሮ ባነሰች የዕለት ገቢ ነው። የአንድ የቻይና ገበሬ የዓመት ገቢ ከ 300 ኤውሮ አይበልጥም። በዚህች ገቢውም መላ ቤተሰቡን ማስተዳደር አለበት።” እርግጥም ሕዝባዊት ቻይና ሻንግሃይን በመሳሰሉ ባሸበረቁ ዘመናዊ ከተሞች ተቀማጭ ለሆኑት የውጭ ኢንዱስትሪ ተጠሪዎች ስውር በሆነ ጥልቅ የኑሮ ልዩነት የተከፈለች አገር ናት። በየከተማው መዳረሻ ወጣ ብለው በሚገኙ ስፍራዎች የአንድ ቤተሰብ ሶሥት ትውልድ ሰላሣ ካሪሜትር በሆነች ቤት ተጣቦ መኖሩ የተለመደ ነው።

የገጠሩና የከተማው የኑሮ ደረጃ ልዩነት የሰማይና የምድርን ያህል የተራራቀ የሆነባቸው አካባቢዎችም ጥቂቶች አይደሉም። ይህ የሕብረተሰብ ክፍል ታዲያ በኢንዱስትሪ ልማት በበለጸጉ አገሮች የሚሰሩ የውጭ ምርቶችን ለመግዛት አቅም አይኖረውም። እንግዲህ ቻይና እንደ ምዕራቡ ዓለም የተጣጣመ ዕድገትን ለማስፈን ገና ብዙ ይቀራታል ማለት ነው። በሌላ በኩል የሚሊዬነሩ ባለጸጋ ቁጥር በዓለምአቀፍ ደረጃ ተመሳሳይ በሌለው ፍጥነት ሲጨምር ነው የሚታየው።

ሰማይ ጠቀስ ሕንጻዎች እስትንፋስ በሚያሳጣ ፍጥነት ይገነባሉ። ፖርሼን፤ ቢ.ኤም.ደብሉዩ.ን፣ ዳይምለር-ክራይስለርንና አውዲን የመሳሰሉት ታዋቂ ዓለምአቀፍ የአውቶሞቢል ኩባንያዎች በአገሪቱ የሚሸጧቸው ተሽከርካሪዎች ቁጥር እጅግ ጨምሯል። ዓለምአቀፉ የአየር በራራ ኢንዱስትሪ በዓለም ላይ በቅርቡ የሕዝባዊት ቻይናን ያህል የምርት ማቅረብ ኮንትራት የሚገኝበት ቦታ እንደማይኖር ይገምታል። በኤሌክትሮኒኩ ጥበብ ዘርፍ ላይ ካተኮርንም በቻይና ዛሬ 110 ሚሊዮን ዜጎች የኢንተርኔት ተገልጋዮች ናቸው። የሞባይል ስልክ ተጠቃሚዎችም ብዛት ያንኑ ያህል ይሆናል። በዓለም ላይ አሜሪካ ብቻ ናት ከዚህ የበለጠ ተሳትፎ የሚታይባት።

ሕዝባዊት ቻይና ምዕራባውያን ኩባንያዎችን በመግዛት ወይም ከፊል ድርሻ በመያዝ ጥራት ያላቸው ተፎካካሪ ምርቶችን በማቅረብ ወደፊት እየገሰገሰችም ነው። ለምሳሌ ያህል ሌኖቮ የተሰኘው ኩባንያዋ የ IBM -ን የኮምፒዩተር ዘርፍ በመግዛት ዛሬ በዓለም ዙሪያ በዚህ ንግድ ዘርፍ ሶሥተኛ ለመሆን በቅቷል። ይህ የኩባንያው መሥራች የሊዩ ቹዋንዢ ስልታዊ ዘዴ ደግሞ ዛሬ በርከት ላሉ የቻይና አምራች ኢንዱስትሪዎች አርአያ እየሆነ ነው።

ቹዋንዢ ዓላማቸውን ሲያስረዱ “የሌኖቮ ዓላማ ረጅም ዕድሜ ያለውና ዕድገቱ ያልተቋረጠ ትርፍን ማረጋገጥ ነው። ለዚህም ያለው ብቸኛ መፍትሄ ቴክኖሎጂውን በራስ ማሳደግና የተሃድሶ ብቃትን ማረጋገጥ ይሆናል። እንዲህ ሲሆን ብቻ ነው ከማገገም ወደ መዳረብ ተሸጋግረን ቀደምት ቦታ ልንይዝ የምንችለው።” ይላሉ። ቹዋንዡ የምርት ብቃትን ማዳበርን ከታይዋን፤ የምርት ዕድገት ዘይቤንም ከአሜሪካ እንማራለን ሲሉም አያይዘው አስረድተዋል።

ታዲያ ምዕራቡ ዓለም በቻይና ዕድገትና ሰፊ የዓለም ንግድ ድርሻ ድንጋጤ ላይ መውደቁ አልቀረም። ቻይና በበለጸጉት መንግሥታት ዘንድ በቀላሉ የማትታይ መሆኗን ቢቀር የዓለም ንግድ ድርጅት የጨርቃ ጨርቅ ምርት ኮታ ከዓመት በፊት ካከተመ ወዲህ የተፈጠረው ሁኔታ አጉልቶ አሣይቷል። ዛሬ የቻይና አልባሣት የምዕራቡን ገበያ እያጥለቀለቁ ነው። በቻይና የተሰሩ ጫማዎች ድርሻ እንዲያውም በሰባት ዕጅ መጨመሩን ነው ምዕራባውያን መረጃዎች የሚጠቁሙት።

ሕዝባዊት ቻይና ውስጥ በአሁኑ ጊዜ ከቤት ዕቃ አንስቶ ጥራት እስካላቸው አልባሣት፤ ከአውቶሞቢል እስከ ምርት መሣሪያዎች ተኮርጆ የማይሰራ ነገር የለም። እርግጥ ጥራቱ በተለያየ ደረጃ የሚታይ ቢሆንም! ቻይና ለማንኛውም ከምዕራቡ ዓለም ዕድገት ለመስተካከል በያዘችው ዕቅድ ስኬት እንደምታገኝ ጨርሶ አትጠራጠርም። የምጣኔ-ሐብት ጉዳይ አማካሪ የሆኑት ፔንግ ጁን እንደሚሉት “የቻይና አጠቃላይ ብሄራዊ ምርት በ 2014 ዓ.ም. የአሜሪካን ሊያክል የሚችል ነው። እርግጥ ከአገሪቱ 1.3 ሚሊያርድ ሕዝብ ቁጥር አንጻር ሲታይ ነፍስ ወከፉ ገቢ ዝቅ ያለ ይሆናል።” በጁን ዕምነት በሚቀጥሉት ዓመታት ለቻይና ታላቁ ችግር የሚሆነው መንግሥት ማሕበራዊውን ውጥረት መቋቋም መቻሉ፣ ግዙፍ የኤነርጂ ፍላጎቱን ማሟላቱና አስከፊውን የተፈጥሮ ብክለት በቁጥጥር ሥር ማዋል መብቃቱ ነው። ለነገሩ የቻይና ባለሥልጣናት ዕድገትን ያስቀድሙ እንጂ በዚህ በኩል ለጉዳዩ ትኩረት መስጠታቸው አልቀረም።

ለማንኛውም ለምዕራቡ ዓለም በኤኮኖሚው ዘርፍ ቻይናንና ሕንድን የመሳሰሉት አገሮች በሚያደርጉት የተፋጠነ ዕድገት ከያቅጣጫው ብርቱ ፉክክር ነው የገጠመው። በዳቮሱ የኤኮኖሚ መድረክ በኢንዱስትሪ ዕድገት የበለጸገውን ዓለም ተጠሪዎች የሚያጽናና ሆኖ የተገኘ ነገር ቢኖር ቻይና የዓለምን ገበዮች በምርቶቿ የማጥልለቋን ያህል ይበልጥ ገዢ አየሆነች መሄዷ ነው። ዘመናዊ የቴክኖሎጂ ጥበብን ታስገባለች፤ ሕዝቧ የምዕራቡን ዓለም ምርቶች መግዛቱም በሰፊው ጨምሯል።

በዳቮሱ መድረክ አኳያ ሌላው ዓቢይ ትኩረት የተሰጠው ጉዳይ የዓለም ንግድ ስርዓት ይዞታ ነበር። የዓለም ንግድ ድርጅት ጉባዔ ከአንድ ወር በፊት ሆንግኮንግ ላይ ያካሄደውን ጉባዔ መለስተኛ በሆነ፤ ታዳጊ አገሮችን እምብዛም ባላረካ አስታራቂ ስምምነት መፈጸሙ ይታወሣል። ምናልባት ሊባል የሚቻል ነገር ቢኖር ጉባዔው ለዶሃው የድርድር ዙር መቀጠል ጨርሶ በሩ እንዳይዘጋ አድርጓል ነው።

የዓለም ንግድ ድርጅት ጠቅላይ አስተዳዳሪ ፓስካል ላሚይ ለጉባዔው ባሰሙት ንግግር ከጠበቅነው የተሻለ ጥቂት ዕርምጃ አድርገናል፤ ቢሆንም ችግሩ ጊዜ የማይሰጥ አጣዳፊ ጉዳይ ነው ሲሉ ነበር ውጤቱን ለዘብ ባለ መልክ ያስገነዘቡት። የዶሃው’ የድርድር ዙር እስከያዝነው ዓመት መጨረሻ መጠናቀቅ እንደሚኖርበት በዳቮሱ መድረክ ላይ ተነግሯል። ይህም ማለት የዓለም የእርሻና የኢንዱስትሪ ምርት ንግድ ስርዓት ቀረጥን በመቀነስና ገበዮችን በመክፈት እንዲለዝብ አስፈላጊው ውል መስፈን ይኖርበታል ማለት ነው።

እርግጥ በሆንግኮንጉ ጉባዔ ለረጅም ጊዜ ሲያወዛግብ የቆየው ችግር ወደ ጎን ተገፋ እንጂ አልተወገደም። በመሆኑም በኢንዱስትሪ ልማት በበለጸጉት መንግሥታትና በታዳጊ አገሮች መካከል ያለው የጥቅም ልዩነት በቀላሉ መወገዱ የሚያጠያይቅ ነው።