1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የደቡብ ኮርዶፋን ድርድር

ሐሙስ፣ የካቲት 6 2006

ካርቱሞች፥ የጠላቶቻቸዉን ቁርጥር መቀነስ፥ የደከመ ምጣኔ ሐብታቸዉን መጠገን ይሻሉ።አማፂያኑ፥ጁባዎች ዉጊያ ሲገጥሙ የዲፕሎማሲ፥ የገንዘብ፥ የመሳሪያ ምንጫቸዉ ካናቱ ተበጥብጧል።ሌፍ እንደሚሉት የደቡብ ሱዳን ጦርነት ለደቡብ ኮርዶፋን «ሳይደግስ አይጣላም» አይነት ነዉ-የሆነዉ።ቢያንስ ለጊዜዉ።

https://p.dw.com/p/1B8E8
አል በሽርምስል Reuters

የደቡብ ሱዳን ተፋላሚ ሐይላት ተወካዮች አዲስ አበባ የሚያደርጉት የሠላም ድርድር እየተቋረጠ መጀመሩ በሚዘገብበት ባሁኑ ወቅት የሰሜን ሱዳን መንግሥትና የደቡብ ኮርዶፋን አማፂያን ተወካዮች እዚያዉ አዲስ አበባ ዉስጥ አዲስ ድርድር ለመጀመር መስማማታቸዉ ተነግሯል።የካርቱም መንግሥት እና በደቡብ ሱዳን ይደገፋል የሚባለዉ የSPLM-ሰሜን የተሰኘዉ አማፂ ቡድን ተወካዮች ዛሬ ያደርጉታል የተባለዉ ድርድር በአንድ ዓመት ዉስጥ የመጀመሪያዉ ነዉ።ታዛቢዎች እንደሚሉት ድርድሩ ባጭር ጊዜ ለዉጤት ይበቃል ተብሎ አይታመንም።ይሁንና ሁለቱ ወገኖች ለመደራደር መፍቀዳቸዉ ራሱ ደቡባዊ ኮርዶፋንን ላለፉት ሰወስት ዓመታት የሚያብጠዉን ጦርነት ለማስቆም ተስፋ ሰጪ ነዉ።

ዑመር ሐሰን አልበሽር እንደያኔዋ መላዋ ሱዳን ፕሬዝዳት፥ ጆን ጋራንግ እንደ ጠንካራዉ አማፂ ቡድን መሪ እንደ ጎሮጎሮሳዉያኑ አቆጣጠር በሁለት ሺሕ አምስት ናይሮቢ ኬንያ ላይ የሠላም ዉል ሲፈራረሙ ረጅሙ የአፍሪቃ የርስ በርስ ጦርነት አበቃ ያላለ ፖለቲከኛና ዲፕሎማት አልበረም።

በስምምነቱ መሠረት የሱዳን ለሁለት መገመስ ለቀድሞይቱ ሠፊ አፍሪቃዊት ሐገር ሕዝብ ሠላም፥ ብልፅግና ሁነኛ መፍትሔ እንደሚሆን የዋሽግተን-ለንደን-ፓሪስ ፖለቲከኞች፥ የኒዮርክ-ብራስልስ፥ የአዲስ አበባ-ካይሮ ዲፕሎማቶች በሚናገሩ፥ ሐሳቡን የሚቃወሙትን በሚቀጡ፥ በሚያስፈራሩበት መሐል ሱዳን ምዕራብ ግዛቷ በሌላ ጦርነት ትጋይጋይ ያዘች።ዳርፉር።

የደቡብ ሱዳን የቀድሞ አማፂዎች ጁባ ላይ አዲስ መንግሥት ባቆሙ ማግስት ደግሞ ሌሎች የሰሜን ሱዳን ግዛቶች በዉጊያ ይታመሱ ገቡ።ደቡብ ኮሮዶፋን እና ብሉ ናይል።ሥሙን ጁባ ላይ መንግሥት ካቆመዉ አማፂ ቡድን SPLM-ቀድቶ N (ሰሜን)ን ያከለዉ ቡድን ብዙዎች እንደሚያምኑት በጁባ መንግሥት ድጋፍ የካርቱም መንግሥትን መዋጋት የጀመረዉ በ2011 ነዉ።

የጦርነቱ ቀዳሚ ሰለባ ያዉ የዋሑ ሕዝብ ነዉ።በመቶ የሚቆጠሩ ሰዎች ተገድለዋል።በብዙ ሺሕ የሚቆጠሩ ደግሞ አንድም ተሰደዋል አለያም ተፈናቅለዋል።የጁባ ፖለቲከኞች ገና ለጠናካራ መንግሥትነት ሳይበቁ ሌላ ጦርነትን ማጋጋማቸዉ አነጋግሮ ሳያበቃ እራሳቸዉ ከጦርነት መዘፈቃቸዉ ወደ ደቡብ ሱዳን ተሰዶ ለነበረዉ ለኮርዶፋን ሕዝብ ሌላ ስቃይ ነዉ የሆነዉ።

«የግጭቱ ገፈት ቀማሾች ሠላማዊ ሠዎች ናቸዉ።በተለይም ጠንካራዉን የአዉሮፕላን ቦምብ ድብደባን ሽሽት ከተሰደዱት አብዛኞቹ ደቡብ ሱዳን ነበር የገቡት።አሁን ደቡብ ሱዳን ጦርነት ሲቀጣጠል ደግሞ ስደተኞቹ ያላቸዉ አማራጭ ወደ አደገኛዉ ቀያቸዉ መመለስ አለያም አደገኛዉን ጦርነት መጋፈጥ ነዉ።»

ይላሉ ጆና ሌፍ የአነስተኛ ጦር መሳሪያዎች ዝዉዉርን በሚያጠናዉ ድርጅት የሱዳኖች ጉዳይ ባለሙያ ናቸዉ።የካርቱም መንግሥት እና የኮርዶፋን አማፂያን ከዚሕ ቀደም አንዴ ጀምረዉ ያቋረጡትን ድርድር አሁን ለመጀመር የተስማሙት በይፋ እንደሚሉት የመከረኛ ሕዝባቸዉ መከራ አሳስቧቸዉ ሊሆን ይችላል።

ዋናዉ ምክንያት ግን በርግጥ ሌላ ነዉ።ካርቱሞች፥ የጠላቶቻቸዉን ቁርጥር መቀነስ፥ የደከመ ምጣኔ ሐብታቸዉን መጠገን ይሻሉ።አማፂያኑ፥ጁባዎች ዉጊያ ሲገጥሙ የዲፕሎማሲ፥ የገንዘብ፥ የመሳሪያ ምንጫቸዉ ካናቱ ተበጥብጧል።ሌፍ እንደሚሉት የደቡብ ሱዳን ጦርነት ለደቡብ ኮርዶፋን «ሳይደግስ አይጣላም» አይነት ነዉ-የሆነዉ።ቢያንስ ለጊዜዉ።

«በካርቱሙ የNCP ፓርቲ ዘንድ የመርሕ ለዉጥ የማድረግ ፍንጭ አይተናል።አሁን (ደቡብ ሱዳን) ያለዉ ሁኔታም ለዚሕ ድርድር መጀመር እግዛ አድርጓል ማለት ይቻላል።»

የሰሜን ሱዳን መንግሥት እና የኮርዶፋን አማፂያን ደም የተቃቡ አሁንም የሚዋጉ ጠላቶች ናቸዉ።በደቡብ ሱዳንኑ ጦርነት ግን ብዙዎች እንደሚያምኑት ሁለቱም ያንድ ወገን ደጋፊዎች ናቸዉ።የፕሬዝዳት የሳልቫ ኪር መንግሥትን።የሁለቱ ወገኖች ተወካዮች አሁን የሚያደርጉት ድርድር ዉጥንቅጡን የሱዳኖች ጦርነት ለማስቆም ብዙ ተስፋ የሚጣልበት አይደለም።ካለመደራደር ግን ብዙ ጊዜ ይሻላል።በተለይ ለደቡብ ኮርዶፋን ግዛት።

«ሁለቱም ወገኖች ለመደራደር መወሰናቸዉ ቀና እመርታ ነዉ።ይሁንና የዉጥረቱን ደረጃ ስናይ ሁለቱም ከባድ ማካካሻዎችን ሰጥተዉ ለመቀበል መዘጋጀት አለባቸዉ።ጦርነቱ በተለይ ደቡብ ኮርዶፋን ዉስጥ እንደቀጠለ ነዉ።ግጭቱን የማቆም አዝማሚያም አይታይም።ባጭር ጊዜ ይቆማል የሚል እምነትም የለኝም።ሥለዚሕ ከስምምነት ለመድረስ ሁለቱም ወገኖች በርካታ ጉዳዮችን መፍታት አለባቸዉ።»

ይላሉ ሌፍ።አሁን ከካርቱም መንግሥት ጋር ለመደራደር የተስማማዉ SPLM-ሰሜን ከዳርፉርና ከሌሎች አማፂያን ጋር ግንባር ፈጥሯል።በዚሕም ምክንያት ድርድሩ ሁሉንም ባለጉዳዮቾ የሚያሳትፍ እንዲሆን በመንግሥትም በአማፂያኑም ላይ ከዉጪም ከዉስጥም ግፊት እየተደረገ ነዉ።

Sudan Sudan People's Liberation Movement-North
የኮሮዶፋን ተፈናቃዮችምስል DW
Sudan Sudan People's Liberation Movement-North
የSPLM-N አማፂያንምስል DW

ነጋሽ መሐመድ

አርያም ተክሌ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ