1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ሐሙስ፣ ታኅሣሥ 6 2009

የደቡብ ክልል መስተዳደር ምክር ቤት በጠራዉ አስቸኳይ ስብሰባ አዳዲስ ሹመቶችን በማፅደቅና በክልሉ ማኅበረሰቡ ያነሳቸዉ «መሠረታዊ ጥያቄዎች» ላይ በመወያየት እንደተጠናቀቀ የክልሉ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ኃላፊ ወ/ሮ ሂክማ ከይረዲን ለዶቼ ቬሌ ተናግረዋል።

https://p.dw.com/p/2UGvT
Konso
ምስል by-nc-sa/Terri O'Sullivan

SNNPR Cabinet Reshufle, Konso Affair - MP3-Stereo

ወ/ሮ ሂክማም የሴቶችና ሕጻናት ቢሮ ኃላፊ ሆኖ መሾማቸዉን በመግለጽ ምክር ቤቱ ለዘጠኝ አዳዲስ ካቢኔዎች ሹመት እንደሰጠ፣ ስድስቱ ደግሞ በነበሩበት እንዲቀጥሉ እንደተደረገና አምስት አመራሮችም ቦታ መቀያየራቸዉን አብራርቶዋል።

ማኅበረሰቡ ያነሳቸዉ «መሠረታዊ ጥያቄዎች» «ከመልካም አስተዳደር ጉድለት» ጋር ይያያዛል የሚሉት ወ/ሮ ሂክማ «ህዝቡ የሚያደምጠን አመራር አጥተናል» እስከ ማለት ደርሷልም ይላሉ። በደቡብ ክልል የኮንሶ ማኅበረሰብ በዞን የመደራጀት ጥያቄ በማቅረቡ ምክንያት በአካባቢዉ የፖለቲካም ሆነ ማህበራዊ አለመረጋጋቶች እንዳለ ስንዘግብ ቆይተናል። የኮንሶ ጉዳይ ምክር ቤቱ እንደተወያየበትና ችግሮቹም የመልካም አስተዳደር እጦት መሆኑን ወ/ሮ ሂክማ ይናገራሉ።

የኮንሶ አካባቢ ነዋሪ የሆኑት /የአባት ስማቸዉ እንዳይጠቀስ የፈለጉ/ አቶ ባሊ፤ በአካባቢዉ አሁንም የማኅበረሰቡ ደህንነት እንዳልተረጋጋና ሌሎች መሠረታዊ አገልግሎቶችም ሥራ መስጠት ማቆማቸዉን ይናገራሉ።

በደቡብ ክልል 56 ብሔር ብሔረሰቦች እንዳሉ የሚናገሩት ወ/ሮ ሂክማ ክልሉ ሁሉንም በብሔር አደራጅቶ እየሄደ እንዳልሆነ ተናግረዉ ኮንሶም በልዩ ወረዳነት በሰገን አካባቢ ህዝቦች ዞን ዉስጥ እንዲታቀፍ ተደርጓል ነዉ ያሉት። ዶቼ ቬሌ ቀደም ስል ያነጋገራቸዉ የማኅበረሰቡ አባላት በዞን ደረጃ ለመደራጀት የአገርቱ ሕገ መንግሥት ይፈቅድልናል በማለት ኮሚቴ ተዋቅሮ ጉዳዩን ሲከታተል እንደነበር መግለጻቸዉ ይታወሳል። «በዞን ካልተደራጀን ከክልሉ ህዝቦች ጋር መቀጠል የለብንም የሚሉ አሉ» የሚሉት ወ/ሮ ሂክማ፣ «ይህ ደግሞ የማህበረቡ ጥያቄ ሳይሆን የኮሚቴዎቹ ጥያቄ ነዉ» በማለት አጣጥለዋል።

በፌስቡክ በጉዳዩ ላይ ከተወያዩት የዶቼ ቬለ ፌስ ቡክ ገጽ ተከታታዮች መካከል፤ መንግስት ገሚሶቹ «የሕዝብ ጥያቄዎችን የሚያስተናግድበት አንጀት የለውም፣ ከቶውንም አልተፈጠረበትም፣ ለሀብት ዘረፋ መንገድ የሚያመቻችለት ከሆነ ግን ማንም አይቀድመውም» የሚል አስተያየት፤ ሌሎች ደግሞ «በኮንሶ ለተፈጠረዉ ችግር መንግሥት ችልተኝነትን መርጧል፣ ፊት በመቀያየር አምባገንነትን እያንሰረፋ ነዉ» በማለት አስተያየታቸዉን አጋርተዉል።

መርጋ ዮናስ

ሸዋዬ ለገሠ