1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የደቡብ አፍሪካ አገራት የንግድ እድገት ተስፋ

ዓርብ፣ ነሐሴ 20 1997

በያዝነዉ ሳምንት በደቡብ አፍሪካ አገራት የልማት ህብረት በእንግሊዝኛ ምህፃረ ቃሉ SADC የወጣ ጥናት አባል አገራቱ በንግድ ዘርፍ እድገት ማምጣት የሚችሉበት ሁኔታ እየታየ መሆኑ ጠቅሷል። ጥናቱም ከታየዉ ለዉጥ ጎን ለጎን ዓይነተኛ እንቅፋት መኖሩ ቢያሳይም ጥናቱ ባጠቃላይ በአካባቢዉ ለሚገኙ የንግዱ ዓለም ሰዎች ጠቃሚ መረጃ መሆኑ ታምኖበታል።

https://p.dw.com/p/E0jX

ከዚህም ሌላ የዉጪ ባለሃብቶችም በትኩረት የሚያዩት እንደሚሆን ነዉ እምነታቸዉ። የSADC አባል አገራት የምጣኔ ሃብት ይዞታ ቅኝት የዓመቱ ሁለተኛ ዉጤት ይፋ የተደረገዉ በደቡብ አፍሪካ ዋና ከተማ ጆሃንስ በርግ ነበር።
ምንም እንኳን በደቡብ አፍሪካ ከሚገኙ አገራት የመልካም አስተዳደርና የርሃብ ችግር የሚያጠቃቸዉ ቢኖሩም በጥቅሉ በምጣኔ ሃብት ረገድ ተስፋ ሰጪ ለዉጥ መታየት መጀመሩ ነዉ በጥናቱ የቀረበዉ።
በቅኝቱም በ14አባል አገራት የሚገኙ 541 ኩባንያዎችን፤ እንዲሁም በዘጠኝ SADC አገራት የሚንቀሳቀሱ 333 የንግድ ተቋማትን ያካተተ ነበር።
የልማት ህብረቱ ፅህፈት ቤት እንዳስታወቀም ባለፈዉ የፈረንጆቹ ዓመት የተካሄደዉ የመጀመሪያ ጥናት እንደመንደርደሪያ ፕሮጀክት የተወሰደ ነዉ።
በዚህ ዓመት የተካሄደዉ ጥናትም ከመጋቢት ወር ጀምሮ ያለዉን የንግድ እንቅስቃሴ የመዘነ ዓመቱን ሙሉ የሚዘልቅ የመነሻ ቅኝት መሆኑ ታዉቋል።
የተደረገዉ ጥናት በተለይ በምጣኔ ሃብቱ ረገድ የእርሻ ምርትና የአገልግሎት ኢንዱስትሪዎች ላይ ትኩረቱን ያደረገ ነዉ።
በአሁኑ ጊዜም የተሻለ ዉጤት እያሳዩ የሚገኙት ዘርፎች በደቡብ አፍሪካ አገራት የሚገኙ የብረታብረት፤ የማሽንና የመኪና ማምረቻዎች መሆናቸዉን የSADC የንግድ ምክር ቤትና ኢንዱስትሪ አባላት ማህበር ይዘረዝራል።
ከህንድ ዉቅያኖስ የማዳጋስካር ደሴት ለረጅም ጊዜ በልማት ህብረቱ ሳትሳተፍ ቆይታ ባለፈዉ ወር በድጋሚ ህብረቱን ተቀላቅላለች።
ይህም ለአንዳንድ ምርቶች ማለትም እንደኬሚካሎች፣ መድሃኒቶችና ፕላስቲኮች ላሉት አይነተኛ ገበያ እንደሚያስገኝ ቢታሰብም አንዳንድ አምራች ኩባንያዎች በማዳጋስካር ስላለዉ የገበያ እድል የሚያዉቁት እንደሌለ የንግድ ምክር ቤቱ ገልጿል።
በጥናቱ ከተካከቱት 41.2 በመቶ የሚሆኑት በሰጡት ምላሽም በስራ ቦታ HIV ኤድስን ለመከላከል የሚል መርሃ ግብር እንደዘረጉ ሲገልፁ 62 በመቶ የሚሆኑት ደግሞ በሽታዉ በድርጅታቸዉ ላይ ተስፅኖ ማድረሱን ብቻ አምነዋል።
በዓለም ዙሪያ ሲታይ ከአፍሪካ አህጉር በተለይ በስፋት በHIV የተጠቃዉ ክፍል የደቡብ አፍሪካ አገራት የሚገኙበት መሆኑን መረጃዎች ይጠቁማሉ።
በእነዚህ አገራት ምንም እንኳን በምጣኔ ሃብቱ ረገድ ተስፋ ሰጪ ለዉጥ አለ ቢባልም በቁጥር ደረጃ 19የሚደርሱ መሰናክሎችም ጎን ለጎን ታይተዋል።
ከእነዚህ መካከልም በዋናነት የሚጠቀሰዉ በዉጪ ምንዛሪ ላይ የሚታየዉ የዋጋ መዋዠቅ እንደሆነ ነዉ የናሚቢያ የንግድ ምክርቤትና ኢንዱስትሪ ተጠሪ ዳግላስ ሬዝነር የገለፁት።
በናሚቢያ የምጣኔ ሃብት ፓሊሲ የምርምር ዘርፍ ከፍተኛ ተመራማሪ ክሪስቶፍ ስቶርክም የሬዝነርን ቃል በማስተጋባት ማብራሪያ ሰጥተዋል።
የዉጪ ምንዛሪ ዋጋ መዋዠቅ ደካማ የመግዛት አቅም ያለዉ ገንዘብ ያላቸዉን እንደ አንጎላ፤ ኮንጎና ዚምባቡዌ ያሉትን አገራት ብቻ ሳይሆን የተሻለ አቅም አላቸዉ የሚባሉትን የደቡብ አፍሪካና የናሚቢያን ገንዘብም የሚጎዳ ነዉ።
በተጨማሪም ደግሞ ነጋዴዎ የየአገራቸዉን ገንዘብ ይዘዉ ወደ ጎረቤት አገራት በሚጓዙበት ጊዜ በሄዱበት አገር ገንዘብ መንዝረዉ ለመጠቀም እንደሚቸገሩ ነዉ የተገለፀዉ።
የዛምቢያ የንግድ ምክር ቤትና ኢንዱስትሪ ተጠሪ ጀስቲን ቺሱሉ እንደገለፁት ከዛምቢያ ወደዚምባቡዌ ለገበያ የሄደ የዛምቢያ ኩዋቻ በዚምባቡዌ ህጋዊ መገበያያ ባለመሆኑ የዉጪ ምንዛሪ ማግኘት አይችልም።
ይህም ወደ200ሚሊዮን የሚደርሱ ቤተሰቦችን ለሚያስተዳድሩት በሺ የሚቆጠሩት የደቡብ አፍሪካ አገራት ድንበር ዘለል ነጋዴዎች ከፍተኛ ችግር ሆኗል።
ለዚህ መፍትሄ ሊሆን የሚችለዉ በአካባቢዉ በጋራ የሚያገለግል መገበያያ ገንዘብ መጠቀም ቢታመንበትም ሃሳቡ ምናልባት በአዉሮፓዉያኑ 2016ዓ.ም. ተግባራዊ ሊሆን እንደሚችል ነዉ በቦትስዋና ዋና ከተማ ጋቦሮኒ የሚገኘዉ የSADC ፅህፈት ቤት ያስታወቀዉ።
አስቸጋሪ የጉምሪክ አስራሮችና ወደየአገራቱ መግቢያ ቪዛ አሰጣጥ ሁኔታም በልማት ህብረቱ አገሮች መካከል ላለዉ የንግድ ግንኙነት አይነተኛ እንቅፋቶች መሆናቸዉ ተገልጿል።
ለጋራ ጥቅም ሲባልም አስቸኳይ መፍትሄ የሚያሻዉ የንግዱ ዘርፍ ችግር መሆኑን ጥናቱ ጠቁሟል።