1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የደቡብ አፍሪቃ የማሪካና ሰለባዎች

ሰኞ፣ መጋቢት 11 2009

የደቡብ አፍሪቃ መንግሥት በጎርጎሪዮሳዊዉ 2012 ዓ,ም በሀገሪቱ የማሪካና የማዕድን ማዉጫ ስፍራ ለተፈጸመዉ እልቂት ሰለባዎች የ92 ሚሊየን ዶላር ካሳ ለመስጠት መዘጋጀቱ ተሰምቷል። የዛሬ አራት ዓመት በዚህ ስፍራ የሥራ ማቆም አድማ ሲካሄድ ፖሊስ 34 ሠራተኞችን በጥይት ገድሏል፤ ብዙዎችን አቁስሏልl በመቶዎች የሚቆጠሩትንም አሥሯል።

https://p.dw.com/p/2ZaHs
Südafrika Polizeieinsatz Tötung Minenarbeiter 16.08.2012
ምስል AFP/GettyImages

S.Africa Marikana victems comp.* - MP3-Stereo

 ጉዳዩን የመረመረዉ አጣሪ ኮሚሽን የፖሊስ ተኩስ ያልተገባ እና በዚህ የተሳተፉም እንዲከሰሱ ምክረ ሃሳቡን አቅርቧል። ድርጊቱም ጭፍጨፋ ተብሎ ተፈርጇል። በጎርጎሪዮስ የዘመን ቀመር ነሐሴ ወር 16ኛዉ ቀን ነበር። ደመወዝ እንዲጨመርላቸዉ በመጠየቅ የሥራ ማቆም አድማ የመቱት በመቶዎች የሚቆጠሩ በፕላቲኒየም ማዕድን ማዉጫ ስፍራ የሚገኙ ማዕድን ሠራተኞች ተሰባስበዉ ይዘፍናሉ፤ ይደንሳሉ። ጭፈራቸዉ ጋብ ሲል በአካባቢዉ የሚገኘዉ የፖሊስ ኃይል ያን እንዲያቆሙ አስጠነቀቃቸዉ። እነሱ ግን አላቆሙም፤ ያኔ ፖሊስ ጥይቱን ያርከፈክፈዉ ጀመር፤ 34ቱን ገለደ፤ 78ቱ ደግሞ ቆሰሉ።

ረጅም የፍርድ ቤት ዉጣ ዉረድ ከተካሄደ፤ ከአራት ዓመታት በኋላ ፤ የፖሊስ ሚኒስትር ንኮስናቲ ናልኮ፤ የደቡብ አፍሪቃ መንግሥት በተፈጸመዉ ጭፍጨፋ ለተጎዱት ሰለባዎች ካሳ ለመክፈል መዘጋጀቱን አስታወቁ። ነገር ግን ክፍያዉ የሚፈጸመዉ ከሰለባዎቹ ጋር የሚደረገዉ የካሳ ስምምነት ሲያልቅ ብቻ እንደሚሆን ለሀገሪቱ የምክር ቤት አባላት ተናግረዋል።

«የሕግ ጉዳዮች የራሳቸዉን ጊዜ መዉሰድ እንደሚፈልጉ ታዉቃላችሁ። ከፕሮጀክት አስተዳደር አኳያ ሲታይም አንድ ሳምንት አይወስድም የተባለ ጉዳይ፤ በቀላሉ ከሳምንት በላይ የሚፈጅበት ሁኔታ አለ።»

መንግሥት ሊሰጥ ያዘጋጀዉ የ92 ሚሊየን ዶላር ካሳ፤ ቤተሰቦቻቸዉን ያጡ፤ እንዲሁም ጉዳት የደረሰባቸዉን የማዕድን ቁፋሮ ሠራተኞች እና በተጨማሪም ያለ አግባብ የታሠሩትን 652 አቤቱታ አቅራቢዎችን ይመለከታል። መንግሥት ለሰለባዎቹ ካሳ ለመክፈል ዝግጁ መሆኑን ማሳወቁ በብዙዎች ተወድሷል። ፓቱ ፓይሪ እልቂቱ በተፈጸመበት ዕለት በስፍራዉ ከነበሩ የማዕድን ቁፋሮ ሠራተኞች አንዱ ነዉ። መንግሥት ካሳ ለመስጠት መዘጋጀቱ ቢያስደስተዉም፤ ቃታ ስበዉ ብዙዎችን ለሞት እና ለጉዳት የዳረጉ ፖሊሶች ገና ባለመታሰራቸዉ ግን ማዘኑ አልቀረም።

Südafrikanischer Bergarbeiterstreik Gewalt und Tote in Marikana
የማዕድን ሠራተኞቹ ለተቃዉሞዉ ተሰብስበዉምስል Reuters

«ለፈጸሙት ዋጋ መክፈል ይኖርባቸዋል። መከሰስ አለባቸዉ፤ ምክንያቱም እነሱ ገድለዋል።»

ሌላዉ የማዕድን ቁፋሮ ሠራተና ቮዮ ማቃንዳ እንዲህ ያለዉ መጠነኛ የገንዘብ ካሳ በተለይ ለተገደሉት በቂ አይደለም ነዉ የሚለዉ።

«እነዚያን ሰዎች በዚህች ሀገር ማንም ሊተካቸዉ አይችልም። ሄደዋል። ለእያንዳንዳቸዉ በሚሊየን የሚቆጠር ራንድ ቢከፈል እንኳ፤ የሉም፣ አብረናቸዉ ልንሆን አንችልም። ቤተሰቦቻቸዉን ወስደዉ በእነሱ ቦታ እንዲሰሩ ሊተኳቸዉ ይገባል፤ እናም የምንፈልገዉን 12,500 ራንድ ለእነሱ ይስጧቸዉ።»

በፕሬዝደንት ጃኮብ ዙማ ጉዳዩን እንዲያጣራ በይፋ የተቋቋመዉ መርማሪ ኮሚሽን ለተፈጸመዉ ሁሉ ጥፋቱን ተቃዉሞን መበተን አልቻለም በተባለዉ የፖሊስ ስልት ላይ አድርጓል። ሆኖም ካሳ ይከፈል የሚል ምክረ ሃሳብ እስከማቅረብ ድረስ ግን አልገፋም።

ሸዋዬ ለገሠ/ ቱሶ ኩማሎ

ኂሩት መለሰ