1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የደቡብ ሱዳን ድርድር

Eshete Bekeleዓርብ፣ ነሐሴ 1 2007

የደቡብ ሱዳን ተፋላሚ ኃይላት 1 ዓመት ከ8 ወር የዘለቀውን ውጊያ ማስቆም ያስችላል ተብሎ ተስፋ የተጣለበትን የሰላም ንግግር ትናንት አዲስ አበባ ውስጥ እንደገና ጀምረዋል ።በዚሁ የሰላም ንግግር ላይ ከአደራዳሪው የምሥራቅ አፍሪቃ የልማት በይነ መንግሥታት ባለሥልጣን ኢጋድ በተጨማሪ የአውሮፓና የዩናይትድ ስቴትስ ተወካዮች ተገኝተዋል ።

https://p.dw.com/p/1GBoZ
Südsudan Friedensverhandlungen Addis Abeba
ምስል DW/G. T. Hailegiorgis

[No title]

ለ20 ወራት የዘለቀውን የደቡብ ሱዳን የርስ በርስ ጦርነትና ቀውስ ለማብቃት ከአንዳች የሰላም ስምምነት እንዲደርሱ በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ጫና የበረታባቸው የደቡብ ሱዳን ተፋላሚ ሐይሎች አሁን በአዲስ አበባ በማካሄድ ላይ የሚገኙት ድርድር የመጨረሻ ነው ተብሏል። የምስራቅ አፍሪቃ የልማት በይነ-መንግስታት ዋና አደራዳሪ አቶ ስዩም መስፍን በውድድሩ ጅማሮ ተደራዳሪዎቹ የደቡብ ሱዳን ህዝቦች እጣ ፈንታ ላይ ጉልህ ሚና የሚኖረው ውሳኔ ላይ የሚደርሱበት ጊዜ ነው ሲሉ መናገራቸውን ኤ.ኤፍ.ፒ. ዘግቧል።

Symbolbild Gewalt Südsudan
ምስል picture-alliance/dpa/M. Knowles-Coursin

የምስራቅ አፍሪቃ የልማት በይነ-መንግስታት (ኢጋድ)በሚመሰረተው የሽግግር መንግስት ውስጥ ለፕሬዝዳንት ሳልቫ ኪር ከፍ ያለ ድርሻ ለሪየክ ማቻር ደግሞ በግሬተር አፐር ናይል ግዛት ምክር ቤት አብላጫ መቀመጫ የሚሰጥ የስልጣን ክፍፍል አቅርቦ ነበር ተብሏል። የአደራዳሪዎቹ ሃሳብ ተቀባይነት ሳያገኝ ቀርቶ ተፋላሚ ሃይላቱ ደቡብ ሱዳንን የጦር አውድማ አድርገዋት 20 ወራት ተቆጠሩ።

ፕሬዝዳንት ሳልቫ ኪር እና ተቀናቃኛቸው ሪየክ ማቻር በምስራቅ አፍሪቃ የልማት በይነ-መንግስታት፤ ዩናይትድ ስቴትስ፤ ብሪታኒያ፤ ኖርዌይ፤ የአውሮጳ ህብረት፤ የተ.መ.ድ. ፤የአፍሪቃ ህብረት እና ቻይና አማካኝነት በነሐሴ 11 ቀን ከመጨረሻ ስምምነት እንዲደርሱ ቀነ ገደብ ተሰጥቷቸዋል። ከአዲስ አበባው ድርድር የደቡብ ሱዳን መንግስት ግን በአዲስ አበባው ድርድር መጀመር ቀደም ብሎ አዲስ አገር በቀል የሰላም ሃሳብ ይዘን መጥተናል እያሉ መሆኑን ተሰምቷል።«ድርድሩ ከተጀመረ ጀምሮ ሰበቦች እያበዙ ከድርድሩ ለመውጣት ጥረት ሲያደርጉ ነበር።» የሚሉት የምስራቅ አፍሪቃ የፖለቲካ ተንታኙ አቶ አቤል አባተ አሁን አለን የሚሉት አዲስ አገር በቀል የሰላም ስምምነት ከአዲስ አበባ የውይይት መድረክ ሙሉ በሙሉ የማፈንገጥ ምልክት ሊሆን እንደሚችል ይጠረጥራሉ። ከፕሬዝዳንት ሳልቫ ኪር መንግስት በኩል የቀረበው ‘አገር በቀል የሰላም ሃሳብ’በሪየክ ማቻርና የተቃዋሚ ሃይሎች ዘንድ ምን አይነት ተቀባይነት እንዳለው ለማወቅ ጊዜ ይፈጃል።

በምስራቅ አፍሪቃ ህብረት ንግግር ያደረጉት የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማ ነሐሴ 11 ቀንን የደቡብ ሱዳን ባለስልጣናት ከስምምነት እንዲደርሱ በሌሉበት ማስጠንቀቂያ ሰጥተዋል። ማስጠንቀቂያ ግን ለደቡብ ሱዳናውያኑ ተፋላሚ ሃይላት አዲስ አይደለም። ካሁን ቀደም እንኳ አሜሪካ፤የአውሮጳ ህብረትና የተባበሩት መንስታት ድርጅት ከማስጠንቀቂያ አልፈው በስድስት የጦር መኮንኖች ላይ ማዕቀብ ጥለው ነበር።የተቀየረ ነገር ባይኖርም። የደቡብ ሱዳንን ጉዳይ በአንክሮ ለሚከታተሉት አቶ አቤል አባተ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ለደቡብ ሱዳን ተፋላሚ ሃይላት የሰጠው ማስጠንቀቂያ ለውጥ ያመጣል የሚል እምነት የላቸውም።

Südsudan Waffenstillstand 01.02.2014 Addis Abeba
ምስል Reuters/T. Negeri

የምስራቅ አፍሪቃ የልማት በይነ-መንግስታት ባቀረበው የሰላም ስምምነትመሰረት ለ 30 ወራት የሚቆይ የሽግግር መንግስት የሚመስረት ሲሆን ሳልቫ ኪርም ይሁኑ ሪየክ ማቻር በስልጣን ይቆያሉ። ከሁለት ወራት በኋላ ለሚካሄደው ምርጫ የመወዳደር መብትም አላቸው። የአዲስ አበባው ውይይት ግን ገና ከጅማሮው ጥላ አጥሎበታል። በውይይቱ መክፈቻ ንግግር ያደረጉት የደቡብ ሱዳን መንግስት ተወካይ በአደራዳሪዎቹ የቀረቡ የስልጣን ክፍፍሎችን ተችተው መንግስታቸው በነዳጅ ሃብት በበለጸገው የአፐር ናይል ፤ዩኒቲና ጆንጊሌ ግዛቶች አስተዳደርን ለሪየክ ማቻር ወገን ለመስጠት የቀረበውን ሃሳብ ፈጽሞ እንደ ማይቀበል ተናግረዋል። የሪየክ ማቻር ወገን ተደራዳሪ በበኩላቸው አሁን በስልጣን ላይ የሚገኘው መንግስት ህጋዊ አይደለም ሲሉ መናገራቸውን ሬውተርስ ዘግቧል።

ጌታቸው ተድላ ኃይለ ጊዮርጊስ

እሸቴ በቀለ

ነጋሽ መሐመድ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ