1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የደቡብ ሱዳን የነፃነት በዓልና ችግሮቿ

ሐሙስ፣ ሐምሌ 4 2005

«ማንኛዉም ፖለቲካዊ ለዉጥ ቢደረግ ተጠያቂ እንሆናለን ብለዉ ያስባሉ።ለዚሕም ነዉ የሕዝብ ጥያቄን የሚያነሳ፥ የሕዝብን ጉዳይ የሚናገርን የሚያፍኑት።እኛ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት እንዲመሠረት ጥሪ እያቀረብን ነዉ።አሁን የምናየዉ ግን የዲሞክራሲ ምሕዳሩ በጣም እየጠበበ ነዉ።»

https://p.dw.com/p/195k9
Dinka men covered in mud and cow dung perform a traditional dance at celebrations for South Sudan's second anniversary of independence in Juba, South Sudan, Tuesday, July 9, 2013. After decades of civil war with Sudan, South Sudan became the world's newest country July 9th, 2011 when it gained independence from the north. (AP Photo/Mackenzie Knowles-Coursin)
ጁባ አደባባይ-ፌስታምስል picture alliance/AP Photo

ደቡብ ሱዳን ከሰሜን ከሱዳን ተገንጥላ በይፋ ነፃ መንግሥት የመሠረተችበትን ሁለተኛ ዓመት በዓል ማክሰኞ አክብራ ዉላለች።ፕሬዝዳት ሳልቫ ኪር በዓሉን ምክንያት በማድረግ ባደረጉት ንግግር ለነፃነት ሲዋጉ የሞቱ ወገኖቻቸዉን አወድሰዋል።መንግሥታቸዉ ሙስናን ለመቆጣጠር አበክሮ እንደሚጥርም ቃል ገብተዋል።ይሑንና የደቡብ ሱዳን ሁለተኛ የነፃነት ዓመት በዓል የተከበረዉ በኪር መንግሥት የሚሠነዘረዉ ወቀሳና ትችት ባየለበት፥ የገዢዉ ፓርቲ ባለሥልጣናት መከፋፋለቸዉ በሠፊዉ በሚነገርበት ወቅት ነዉ።ሐናሕ ማክናይሽ የዘገበችዉን ነጋሽ መሐመድ እንደሚከተለዉ አጠናክሮታል።


ርዕሠ-ከተማ ጁባ በዋዜማዉ።ጋዜጣኛዋ-እንደያቻት።አስፋልት የለበሱት መንገደቿ ትንሽ ናቸዉ።ቢሆኑም ይጠረጋሉ።ከመንገዶቹ ግራና ቀኝ ያሉት ለጋ ዛፎች ተከርክመዋል።ሕንፃዎች ብዙ የሉም። ያሉት ግን አሸብረቀዋል።በዓል ነዉ።ያዉም-የነፃነት።በጦርነት የወደመችዉ፥ የወትሮዋ ጫካማ፥ ኋላ ቀር፥ መንደር ጁባ፥ ከጡብና አስፋልት መንገዶች ጋር መተዋወቅዋ፥ ሕንፃዎች ማሳነፅዋ እና የከተማ ወግ ማየትዋ የነፃነትዋ ትሩፋት፥ የመንግሥቷ ጥረት ዉጤት ነዉ።-እንደ ሹሞቿ እምነት።

ብዙዎች ግን የተለያዩ የቀድሞ አማፂ ሐይላን የሚያስተናብረዉ ገዢ ፓርቲ ለሕዝቡ ምንም የተከረዉ የለም ባዮች ናቸዉ።ሙስና አለቅጥ ተንሠራፍቷል።ዉዝግብ፥ ግጭት፥ ጦርነቱም ባሰ እንጂ አልበረደም።

ኦንዮቲ አዲጎ ንዪክዌክ-SPLM-DC በሚል የእንግሊዝኛ ምሕፃረ-ቃል የተሚጠራዉ ተቃዋሚ ፓርቲ መሪ ናቸዉ።የጁባ መንግሥት ከካርቱሞች ጋር የገጠመዉ ዉዝግብ በናረበት ወቅት እንደ ጎርጎሮሳዉያኑ አቆጣጠር ጥር ሁለት ሺሕ አስራ-ሁለት ካርቱሞችን የጎዳ መሥሎት የነዳጅ ዘይት ጎርጓዶችን ዘግቶ ነበር።የንዪክዌክ ፓርቲ እርምጃዉን ተቃዉሞታል።የተቃዉሞዉ ምክንያት ግልፅ ነዉ።ዘጠና-ስምንት ከመቶዉ የሐገሪቱ መንግሥት ገቢ ነዳጅ ዘይት ነዉ።ለሕዝቡ ግን ንዪክዌክ በቀደም እንዳሉት ነዳጅ ኖረም፥ አልኖረ ያዉ «በገሌ» አይነት ነዉ።

«ነዳጅ ዘይት ኖረም አልኖረ፥ መንግሥት የደቡብ ሱዳንን ሕዝብ ለመጥቀም ምንም የሠራዉ የለም።አሁን ወደ ሕሊናቸዉ ከተመለሱ ምንም እንዳልሠሩ፥ ለማሕበረሰቡ ምንም አይነት አገልግሎት እንዳልሰጡ ሁሉም ሰዉ እንደሚያዉቀዉ ያዉቃሉ።»

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እንደሚለዉ አስር ሚሊዮን ከሚጠጋዉ የደቡብ ሱዳን ሕዝብ አራት ነጥብ አምስት ሚሊዮኑ ዓለም አቀፉ ድርጅት የሚሰጠዉ የርዳታ ምግብ ጥገኛ ነዉ።አዲስ ከሚወለዱት አንድ ሺሕ ሕፃናት ሰባ አምስቱ አመት ሳይሞላቸዉ ይሞታሉ።ከተቀሩት ብዙዎቹ አምስተኛ አመታቸዉን አይሞሉም።

ፕሬዝዳት ሳልቫኪር የሚመሩት መንግሥት ሰባ-አምስት ባለሥልጣናት ብቻ አራት ቢሊዮን ዶላር መዝረፋቸዉን ፕሬዝዳንቱ ራሳቸዉ አምነዋል።ዘራፊዎቹ ገንዘቡን ወደ መንግሥት ካዝና እንዲያመልሱም ጠይቀዋል።ጥያቄዉ ግን የገዢዉን ፓርቲ ሹማምንት እብዙ ሥፍራ እየሰነጣጠረ ነዉ።

«ለዚሕም ነዉ አሁን በገዢዉ ፓርቲ ዉስጥ ብዙ ዉዝግብ የተነሳዉ።የመሪነት ሽሚያ የተቀሰቀሰዉ።አንዱ እኔ ከሌላዉ እሻላለሁ ይላል።በመሠረቱ ግን ሁሉም ለደቡብ ሱዳን ሕዝብ ምንም የፈየዱት የለም።»

ፕሬዝዳት ሳልቫ ኪር በቅርቡ በጥቂት በባለሥልጣኖቻቸዉ ላይ ዘምተዋል።የምክትል ፕሬዝዳት ሪክ ማቻርን ሥልጣን በሙሉ ገፈዉ ባዶ ቢሮ አስታቅፈዋቸዋል።ሁለት ሚንስትሮችንና ሁለት አገረ ገዢዎችን ሽረዋል።የኪር እርምጃ የፖለቲካ ታዛቢዎች እንዳሉት ፓርቲያቸዉ በቅርቡ ከሚያደረገዉ ጉባኤ በፊት ተቀናቃኞቻቸዉን ማፅዳት ነዉ።

የሲቢል ማሕበረሰብ ባልደረባ ኤድሞንድ ያካኒ እንደሚሉት ደግሞ የገዢዉ ፓርቲ አባላት ትክክለኛ ለዉጥ እንዲኖር አይፈልጉም።ለዉጥ ጠያቂዉንም ያፍኑታል።

«ማንኛዉም ፖለቲካዊ ለዉጥ ቢደረግ ተጠያቂ እንሆናለን ብለዉ ያስባሉ።ለዚሕም ነዉ የሕዝብ ጥያቄን የሚያነሳ፥ የሕዝብን ጉዳይ የሚናገርን የሚያፍኑት።እኛ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት እንዲመሠረት ጥሪ እያቀረብን ነዉ።አሁን የምናየዉ ግን የዲሞክራሲ ምሕዳሩ በጣም እየጠበበ ነዉ።»

የዲሞክራሲዉ ምሕዳር መጥበብ፥ የሠብአዊ መብት ረገጣ መባባስ ያካኒ እንደሚሉት የነፈጥ ታጋዮችን ወልዷል።ጆንግሌ ግዛት የመሸጉት አመፃን ከመንግሥት ጦር የገጠሙት ዉጊያ አንድ አብነት ናቸዉ እንደ ያካኒ።ደቡብ ሱዳን። የጎሳዎች ግጥጭ፥ ጦርነትም ብሶባታል።


ነጋሽ መሐመድ

Sudan People's Liberation Army (SPLA) soldiers take part in a parade during the 2nd anniversary of South Sudan becoming an independent state on the streets of Juba, July 9, 2013. REUTERS/Andreea Campeanu (SOUTH SUDAN - Tags: ANNIVERSARY POLITICS MILITARY)
ምስል Reuters
South Sudan's second independence anniversary. Young man suffering from malaria, lying on a bed in a Juba hospital. Copyright: Hannah McNiesh via Mark Caldwell, DW Englisch für Afrika
ወባ ጥሎታል-መታከሚያም ሐኪምም የለምምስል Hannah McNiesh
(From L-R) Ethiopian Prime Minister Hailemariam Desalegn, Somalia's President Hassan Sheikh Mohamud, South Sudan's Vice-President Riek Machar and President Salva Kiir pay their respects at John Garang's Mausoleum, during the celebration of the 2nd anniversary of South Sudan becoming an independent state, in Juba, July 9, 2013. REUTERS/Andreea Campeanu (SOUTH SUDAN - Tags: ANNIVERSARY POLITICS)
ጁባ አደባባይ ባለሥልጣናትምስል Reuters

ተክሌ የኋላ