1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሱዳኑ ሽም ሽር ሌላ መዘዝ ያስከትላል

ረቡዕ፣ ሐምሌ 20 2008

ሁለቱ ጠበኞች እንደወዳጅ ተጨባብጠዉ የድሮ ስልጣናቸዉን በአዲስ መንግሥት ሥም በያዙ ማግሥት ሐምሌ መጀመሪያ ላይ እንደገና ተጠሉ። ታማኞቻቸዉ እንደገና ዉጊያ ገጠሙ።የሌላ ዉጊያ መሰናዶዉም ቀጥሏል።

https://p.dw.com/p/1JWlV
ምስል Reuters/J. Solomun

[No title]

የደቡብ ሱዳን ፕሬዝደንት ሳልቫ ኪር የሐገሪቱን ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዝደንት ሪየክ ማቻርን ሽረዉ ሌላ ፖለቲከኛ መሾማቸዉ ወትሮም ያልተረጋገዉን የሐገሪቱን ሠላም ይበልጥ እያወከዉ ነዉ።ኪር ምክትላቸዉን በሌላ የተኩት ማቻር ላለፉት ሁለት ሳምንታት ከርዕሠ-ከተማ ጁባ ጠፍተዋል ወይም ተሠዉረዋል በሚል ሰበብ ነዉ።የኪርን እርምጃ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እና የደቡብ ሱዳን ፖለቲከኞችን በማስታረቁ ሒደት የተሳተፉ መንግስታት እየተቹት ነዉ።የደቡብ ሱዳኑ ግጭት፤ ዉጊያ እና በሰላማዊ ሰዎች ላይ የሚፈፀመዉ በደል እንደቀጠለ ነዉ።ነጋሽ መሐመድ ዝርዝር ዘገባ አለዉ።

ደቡብ ሱዳን ከሰሜንዋ እንድትገነጠል፤ ከፊልም ተዋኞችዋ እስከ ዲፕሎማቶችዋ፤ ከጦር አማካሪዎችዋ እስከ ምጣኔ-ሐብት ባለሙያዎችዋ አበክረዉ የጣሩ፤ ዓለምን ያስተባበሩት- ዩናይትድ ስቴትስ፤ የጁባ ፖለቲከኞች እንዲስማሙ በማዕቀብ ታስፈራራለች። ለአዲሲቱ ሐገር ሕዝብ ቀለብ-ሠፋሪ፤ ለሰላሟ-ዘብ ቋሚ ያዘመተዉ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ያስጠነቅቃል። የአካባቢዉ መንግሥታት እንዳቸዉ ከሌላቸዉ ጋር እየተሻኮቱም የጁባ ፖለቲከኞች ሠላም እንዲያወርዱ ይመክራሉ፤ ይሸመግላሉ።

ደሐ፤ኋላቀር፤ የጎስቋሎቿ ሐገር እንደ ደጋፊ፤ አስጠንቃቂ፤ መካሪ ሸምጋዮችዋ ብዛት፤ የሠላሟ ጥፋት፤ የሚያልቅ ሕዝቧ ብዛት ገደብ ማጣቱ ነዉ-እንቆቅልሹ-ከነፃነት በፊት።በኋላም።ሁለት ከፍተኛ መሪዎችዋ በመጣላታቸዉ ምክንያት ከሁለት ዓመት በላይ በተደረገዉ ዉጊያ በአስር ሺሕ የሚቆጠር ሰላማዊ ሕዝብ አልቋል።ሚሊዮኖች ቆስለዋል፤ተገርፈዋል፤ ተደፍረዋል፤ ተርበዋል።ብዙ ሚሊዮኖች ተሰደዋል።ብዙ ቢሊዮን ዶላር የሚገመት ሐብት፤ ንብረት፤ ሰብል ወድሟል።

Südsudan Flüchtlinge an der Grenze Uganda-Südsudan
ምስል Getty Images/AFP/I. Kasamani

ሁሉ ጥፋት ዉድመት ሁለቱ መሪዎች ከጦርነቱ በፊት ይዘዉት የነበረዉን ሥልጣን እንደያዙ እንዲቆዩ ለማድረግ እንደነበረ የነሐሴዉ ስምምነት መስካሪ ነበር።ያም ሆኖ ስምምነቱ ጥፋቱን ለማቆም አልተከረም።ሁለቱ ጠበኞች እንደወዳጅ ተጨባብጠዉ የድሮ ስልጣናቸዉን በአዲስ መንግሥት ሥም በያዙ ማግሥት ሐምሌ መጀመሪያ ላይ እንደገና ተጠሉ። ታማኞቻቸዉ እንደገና ዉጊያ ገጠሙ።የሌላ ዉጊያ መሰናዶዉም ቀጥሏል።

«ከሁለቱም ወገኖች የጦርነት ዝግጅትና ጥሪ እንሰማለን። አዳዲስ ወታደሮችም እየተመለመሉ ነዉ።ሁኔታዉ ልክ 2013 ጦርነት ሲጀመር የነበረዉ አይነት ይመስላል።»

ይላሉ ጀርመናዊቱ የምሥራቅ አፍሪቃ የፖለቲካ ተንታኝ አኔተ ቬበር።ደግሞ በተቃራኒዉ ቬበር እንደሚሉት ነገሮችን የወትሮዉ ለማስመሰል ሹም ሽር መደረጉ በጠመንጃዉ ጩኸት መሐል ከዚያዉ ከጁባ ይሰማል።

«በዚሁ መሐል ደግሞ እንዲያዉ የተረጋጋ የመንግሥት እንቅስቃሴ ያለ ይመሥል፤ ሪያክ ማቸር፤ በቀድሞ ተደራዳሪያቸዉ መተካታቸዉን ሰማን።»

የፕሬዝደንት ሳልቫ ኪር ደጋፊዎች እንደሚሉት ፕሬዝደንቱ እርምጃዉን የወሰዱት ሪያክ ማቻር ከሐምሌ አጋማሽ ጀምሮ በመወሰወራቸዉ።

በአዲስ አበባ የደቡብ ሱዳን አምባሳደር ጄምስ ፒትያ ሞርጋን እንደሚሉት ደግሞ ተቃዳሚ ምክትል ፕሬዝደንቱ ከራሳቸዉ በሌላ እንዲተካ የጠየቁት የራሳቸዉ የማቻር ፓርቲ ባለሥልጣናት ናቸዉ።

Südsudan Opposition Soldaten
ምስል picture-alliance/dpa/P. Dhil

«ከሐምሌ አስራ-ሁለት ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ ዶክተር ሪየክ ማቸር ከሪፐብሊኳ ፕሬዝደትና ጁባ ከሚገኙ ከራሳቸዉ ፓርቲ አባላት ጋር የነበራቸዉን ግንኙነት አቋርጠዋል።ይሕ ጁባ የሚገኙ የፓርቲያቸዉ አባላት ማቻርን የሚተካ አማራጭ እንዲፈልጉ አስገደዳቸዉ። በዚሕም ምክንያት SLA-IO ጄኔራል ታባን ዴን ጋይ የደቡብ ሱዳን ሪፐብሊክ ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዝደንት እንዲሆኑ አጭቷቸዋል።»

ከተቃዋሚዎች የሚሰማዉ ግን ተቃራኒዉ ነዉ።የማቻር ወገኖች እንደሚሉት ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዝደንቱ ከጁባ ገለል ያሉት ከተቃጣባቸዉ የግድያ ሙከራ ሸሽተዉ ነዉ።

ታዛቢዎችም በዚሕ ይስማማሉ።ፕሬዝደንቱ ማቻርን የከዱትን ታባን ዴን ጋይን የሾሙት ማቻር ያሉበትን 48 ሰዓት ዉስጥ እንዲያሳዉቁ ካስጠነቀቁ፤ የታባን ዴን ጋይን መክዳት ካረጋገጡ በኋላ ነዉ።የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዛሬ እንዳስታወቀዉ ሹም ሽሩ ባለፈዉ ነሐሴ የተደረገዉን የሠላም ዉል የሚፃረር ነዉ።

ነጋሽ መሐመድ

አርያም ተክሌ