1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የደምስ ቤት በ«የአባት ቃል»

ሐሙስ፣ ነሐሴ 26 2008

ግጥም ማለት ፤የተፈጥሮ ስጦታ እንጅ የትምህርት ገጸ-በረከት አይደለም። ማንኛዉም ሰዉ እዉቀት ሊኖረዉ ይችላል። ግን ከላይ ካልተሰጠዉ በስተቀር ግጥም መጻፍ አይችልም። የብዙዎች አስተያየት ነዉ።

https://p.dw.com/p/1JuRL
USA Buchcover Ye Abat Kal von Samson Demisse Tefera

የደምስ ቤት በ«የአባት ቃል»

የእለቱ እንግዳችንም የግጥም ተሰጥዖ እንዳለዉ ያወቀዉ ዛሬ ነፍስ አዉቆ ወልዶ ያደገበት ቤት በእንግድነት ሄዶ ሳለ የአስር ዓመት አዳጊ ሕጻን ሳለ ከአንድ ፎቶግራፍ ጀርባ የቋጠራትን ግጥም ድንገት ካገኘ በኋላ ነዉ።

«ኢትዮጵያን ፖየትሪ» በተሰኘ በፊስ ቡክ ድረ-ገጽ ላይ ከተለያዩ ዓለም ገራት የሚገኙ አዳጊ የሥነ-ግጥም ባለሞያዎችን ለኅብረተሰቡ በማስተዋወቅ እንዲሁም ገጣምያን ስራዎች በማሰባሰብ፤ የሥነ -ግጥም መድበልን እንዲያወጡ ምክር በመለገስና ብሎም በመሳተፍ የሚታወቀዉ ሳምሶን ደምሴ ተፈራ «የአባት ቃል» በሚል ርዕስ ሥነ-ግጥሞቹን አሰባስቦ በመጽሐፍ መልክ ለአንባብያን አቅርቦአል።

ምስል ከግጥም ጋር እያዋሃደ ብዕሩን ከወረቀት እንደሚያገናኝ «የአባት ቃል» የተሰኘዉን ገጣሚ ሳምሶን ደምሴ ተፈራን የመጀመርያ የሥነ-ግጥም መድብል ያየ ሁሉ ይናገራል፤ የብዙዎች አስተያየት ነዉ። በሰሜን አሜሪካ መኖር ከጀመረ ወደ 30 ዓመት የነዉ አቶ ሳምሶን ደምሴ ተፈራ በተለይ ለሥነ ግጥም ያለዉ ልዩ ፍቅር ገጣምያንን እየፈለገ እንዲተዋወቅ አዳጊ ገጣምያንንንም ሥነ ግጥሞቻቸዉ ታዳሚያን ዘንድ እንዲደርሱ ጥረት በማድረግ ይታወቃል። ከዓመታት ጀምሮ ሲጽፉና ሲያስቀምጥ ከነበረዉ አጠር አጠር ካሉ ሥነ ግጥሞቻቸዉ መካከል 192ቱን መረጥ መረጥ አድርገዉ 192 ገጽን በያዘዉ የአባት ቃል በተሰኘዉ የሥነ- ግጥም መድብል ለአንባብያን ያቀረቡት ገጣሚ ሳምሶን ደምሴ ተፈራ መድብሉ መታሠብያነቱ እንደስያሜዉ ለአባቱ እንደሆን ተናግሮአል።

በዋሽንግተን አካባቢ በበርካታ ማህበራዊ ጉዳዮች ላይ በመሳተፍም የሚታወቀት ገጣሚ ሳምሶን ደምሴ ተፈራ ፤ ረጅም ዓመታት በትምህርትና በሥራ መስክ ግዜዉን አሳልፎ በዚያዉ ሰሜን አሜሪካ መንግስት መሥርያ ቤት ተቀጥሮ በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂና ፕሮግራም ማኔጅመንት በከፍተኛ እርከን በማገልገል ላይ ይገኛል። ባለትዳርና የአንድ ወንድ ልጅ እና አንድ ሴት ልጅ አባትም ነው። በቨርጂኒያ ሰሜን አሜሪካ በተካሄደዉና ከ 400 በላይ ታዳሚያን በተገኙበት የሥነ-ግጥም መድበል ምርቃት ላይ ተጋባዦች በመድበሉ ዉስጥ ካሉት ሥነ-ግጥሞች መካከል አንብበዋል። ገጣሚ ሳምሶን ደምሴ ተፈራ ሰዉን ያለ አግባቡ ተናግረዉ ለሚያስከፉ ሰዎች የቋጠራት ግጥም «በልጣችሁ ተገኙ» ትላለች፤

USA Buchvorstellung Ye Abat Kal von Samson Demisse Tefera
አቶ ሳምሶን ደምሴ ተፈራምስል privat

ወርዶ የሚያዋርድ - ንቆ የሚያናንቅ

አድፎ የሚያቆሽሽ - ቢያፀዱት የማይለቅ

ቢገጥማችሁ ድንገት - መሠሪ ክፉ ሰዉ

ዘለፋ የሚያበዛ - ስብዕና የጎደለዉ

በልጣችሁ ተገኙ - ወደታች ሳትወርዱ

ይንከበለል እሱ - በጉልቻ አመዱ

እሳት እየተፋ ነዶ - እየከሰመ

በተዘጋ ሀሳቡ ሰርክ በጨለመ።

በዝግጅቱ ላይ የተገኘችዉ በክብር እንግድነት አርቲስት ዓለም ፀሐይ ወዳጆ ተጋባዥ ነበረች። የምርቃቱ ሥነ-ስርዓትን የመድረክ መሪ በመሆን የምረቃዉን ሥነ-ስርዓት ያደመቀዉ ታዋቂዉ ገጣሚና ጋዜጠኛ ኢሳያስ ልሳኑ ስለገጣሚ ሳምሶን ደምሴ ተፈራ የግጥም ሥራዎች፤ ዉብነት በተለይ ገጣሚዉ በሥራዉ ያለዉን ታታሪነትና ትጉህነቱን እንደሚያደንቅለት ተናግሮአል።

USA Buchvorstellung Ye Abat Kal von Samson Demisse Tefera
ምስል privat

በግጥም ስብስብ ውስጥ ድንበር ተሻጋሪና ፍቅር አዘል ሥራዎች ይታያሉ፤ደቡብ አፍሪቃን ተሻግሮ ስለኔልሰን ማንዴላ የተጻፉ፤ ፀሐፊው ባለበት አሜሪካ የታዋቂዋን ገጣሚ ማያ አንጄሎ ሥራ የሚያወድስበት፤ ጎረቤት አገር ተጉዞ ስለገጣሚው የልጅነት እግር ኳስ ትዝታ የሚወደውን የአስመራ ኤሌክትሪክ ቡድን "ምን አለ"? በሚል ናፍቆት ያነሳበትም ነዉ። የደምስ ቤት አፃፃፍ የተቋጠረዉ የግጥም ዓይነት በምረቃ ሥነ ስርዓት መድረኩም ቀርቦ ነበር።

ምን አለ?

የልጅነት ቀልቤን ፤ የእግርኳስ ህልም ራቤን ፤

ሳልሰናበት ያለፍኩት፤ ትላንቴን ምስላቸውን እንደተውኩት

በፍቅራቸው እንደጮህኩት ፤ ከአይነ ህሊናዬ የማይጠፉ

ታሪክን በጥበብ ፍቅር የፃፉ ፤ ትዝታ ጉዴን ቀሰቀሱ፤

አይኖቼም በናፍቆት አለቀሱ ፤ ያለፉትን በአየር ላይ ተረድቼ

ከተረፉት ተጫውቼ ፤ ምን አለ? ምን አለ?

ኤልፓ፤ቀይ ባህር እየተባለ ፉክክሩ በቀጠለ....

ምን አለ? ከአስመራ አዲስ ሩቅ አይደለ።

USA Buchvorstellung Ye Abat Kal von Samson Demisse Tefera
ምስል privat

የአባት ቃል የግጥምን ካነበቡ መካከል በሰሜን አሜሪካ በሰዉ ኃብት ማለትም በ«ሂዉማን ካፒታል» መስክ በአማካሪነት ሥራ የሚተዳደሩት ዶክተር ጋቤ ሃምዳም አስተያየታቸዉን ከሰጡን መካከል አንዱ የመጽሐፍ ምረቃ ሥነ-ስርዓት ታዳሚ ነበሩ።

ታዋቂ ገጣምያን በሥነ-ግጥሙ ዓለም ልጃችን የሚሉት ሳምሶን ደምሴ ተፈራ ፤ በሰጠን ቃለ- ምልልስ መጀመርያ በኢትዮጵያ የሚገኙና በማኅበራዊ መገናኛ ያሰባሰባቸዉ ሥነ-ገጣምያን የግጥም መድብሉ ለአንባብያን እስኪደርስ ላደረጉለት ጥረት፤ እንዲሁም የመጽሐፉ የፊትና የኋላ ሽፋንን ላዘጋጁለት ሚሌና ጋሻዉ፤ የከበረ ምስጋናን መስጠት እንደሚፈልግ አፅኖት ሰጥቶ ተናግሯል። ገጣሚ ሳምሶን ግጥም የቋጠረባትን መድብሉን ይዞ ግጥም በጃዝ፤ግጥም በመሰንቆ፤ ሌላም ሌላም የሚል ስያሜ ያላቸዉን የሥነ-ግጥም ቤተሠቦች ለማሰባሰብ በቅርቡ ወደ ሸገር እንደሚያቀና ገልጾልናል። መድበሉ ባህልን ቋንቋን ወግን ብሎም ሥነ-ጽሑፍን በማስተማሩ ረገደ ተመንደግ ይበል የሚያሰኝ ሥራ የቀረበበት ይመስለናል። ሙሉ እንብሩን የድምፅ ማድመጫዉን በመጫን ይከታተሉ።

አዜብ ታደሰ

አርያም ተክሌ