1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የዩክሬይን ተስፋና ሥጋት በአዲሱ ዓመት

ሰኞ፣ ታኅሣሥ 27 2007

ባለፈው ሳምንት ኀሙሰ ያባተው 2015 አዲሱ ጎረጎሪዮሳዊ ዓመት ለዩክሬይን ሕዝብ የባሰ የፈተና ጊዜ እንጂ የብልጽግና ዘመን ይሆናል ብሎ የሚያስብ አንድም ያገሪቱ ዜጋ የለም። ኤኮኖሚው ተንኮታኩቷል። ከሩሲያ ጋር መፋጠጡም ለድቀቱ የበኩሉን ድርሻ

https://p.dw.com/p/1EEp7
ምስል DW/K.Logan

አበርክቷል።ኤኮኖሚው፣7.5% ነው ያሽቆለቆለው።

የሀገሪቱ ገንዘብ ሕሪውንያም፣ ዋጋው፣በአንድ ዓመት ውስጥ ከዐርባ ከመቶ በላይ ነው የተቀነሰው።
ዘጠና ከመቶ ገደማ የሚሆኑ የዩክሬይን ዜጎች ኤኮኖሚአቸው መጥፎ ደረጃ ላይ
መድረሱን ያምናሉ።የዩክሬይን ተስፋና ሥጋት፥ በአዲሱ ጎረጎሪዮሳዊ ዓመት ---ኪቭ ውስጥ፣ የከተማይቱ ልዩ ምልክት ከሆነው፣በ፲፩ኛውክፍለ ዘመን ከተገነባው የቅድሥት ሶፊያ ካቴደራል ጥግ ነው፣ የገናው ገበያ የሚገኘው።አጠገቡ፣በማስጌጫ ብልጭልጭ
ነገሮች ያሸበረቀ ጥድ አለ።የካቴድራሉ ወርቃማ ጉልላት ደግሞ ከሩቅም ቢሆን አምሮ ደምቆ ይታያል።

ለብዙ ዓመታት በቤተ መዘክርነት ሲያገለግል ቢቆይም፣ የቅድሥት ሶፊያ ቤተክርስቲያን ፣ እ ጎ አ በ 1990 ዎቹ መግቢያ ላይ ለኦርቶዶካሳዊቱ ቤተክርስቲያን ተመልሷል። ምንም እንኳ ለአያሌ ዐሠርተ ዓመታት በዘለቀው ኮሙዩኒስታዊ አገዛዝ ሳቢያም ይሁን በሌላ ፤ 62 ከመቶ ገደማው የዩክሬይን ሕዝብ ለሃይማኖት ደንታቢስ ቢሆንም፤ 26,7 ከመቶው የኦርቶዶክስ ክርስትና እምነት ተከታይ ነው። 5,9 ከመቶው ካቶሊካውያን ሲሆኑ ፣ 0,9 ከመቶ ፕሮቴስታንት፤ 0,6 ከመቶው ደግሞ ሙስሊሞች ናቸው። በቅድሥት ሶፊያ ካቴድራል ዙሪያ በተቋቋመው ወቅታዊ የገና ገበያ፤ የቤተሰብ አባላት፣ ወጣቶች፣ ጡረተኞችና በዕረፍትላይየሚገኙወታደሮች፣ በመብራት በተሽቆጠቆጡትሱቆች

መኻልሲመላለሱይታያሉ። ገበያተኞች ፤ ወቅታዊውን ችግር ለጊዜውም ቢሆን በገናው ገበያ እየተዘጋጀ በሚሸጥ ባህላዊ ምግብና ለብ ባለ ወይን ለማረሣሣት ይሞክራሉ።

Proteste auf dem Maidan
ምስል picture-alliance/dpa/Maksimenko

ኦሌና ዱቢና የተባሉ ከባለቤታቸው ጋር በጥብቅና ሙያ የተሠማሩ ወይዘሮ ግን ችግሩ በምንም ዓይነት ሊደበቅ የሚችል አለመሆኑን ነው የሚናገሩት።

«እርግጥ በጣም መጥፎ ነው፣ ሁኔታው። ግን ይህ እንደሚያጋጥም ከመጀመሪያውም ሊተነበይ የሚችል ነበር። በጦርነት ላይ ነንና!»

አምና በየካቲት ፣ በመዲናይቱ በኪቭ በማይደን (ነጻነት) አደባባይ ሳምንታት የዘለቀው ተቃውሞ የመንግሥ ት ለውጥ ካስከተለ ወዲህ፤ ዩክሬይን 2014 ጎርጎሪዮሳዊውን ዓመት በምጥ ነው ያሳለፈችው።

ያሁኑ ፕሬዚዳንቷ፣ ፔትሮ ፖሮሼንኮ፤ በቅርቡ በሰጡት ዓመታዊ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ፣ «አገሪቱ እ ጎ አ ከ 1945 ዓ ም ወዲህ ፣ በ 70 ዓመታት ውስጥ፣ ከመንታ መንገድ አንዱን በመምረጥ ብርቱ ፈተና ውስጥ የገባችበት ፤ ለእርሷ ብቻ ሳይሆን፤ ለአውሮፓና ለመላው ዓለም አስቸጋሪ ዘመን ሆኖ አልፏል » ነው ያሉት። ፕሬዚዳንቱ በአዲሱ 2015 ጎርጎሪዮሳዊ ዓመትም ሕዝቡ ሰቁን ጠበቅ አድርጎ ችግሩን ይጋፈጥ ባይ ናቸው።

በብሔራዊው ገንዘብ ዋጋ እጅግ ማሽቆልቆል መጎዳታቸውን ከሚገልጹት ዩክሬናውያን መካከል ፣ የቭገን ጋሉዚንስኪ የተባሉት የኪቭ ኑዋሪ ፣ ለይተው የሚወቅሱት ፣ የሚከሱት አላጡም።

«ማዕከላዊው ባንክ በሚከተለው የገንዘብ አያያዝና አመራር ዘይቤ ያልረኩት ጥቂቶች አይደሉም፤ በተለይ በማዕከላዊ ባንክ ገዥዋ ቫሌሪያ ጎንታሬቫ አያያዝ! እንደሚመስለኝ ፣ የገንዘብ ቀውስ ማጋጠም እንደጀመረ ወዲያውኑ መባረር ነበረባቸው።»

ካለፈው ዓመት ሰኔ ወር አንስቶ የማዕከላዊው ባንክ ገዢ የሆኑት ጎንታሬቫ ፤ መንግሥት የደረሰበትን ዕዳ የመክፈል አሳሳቢ የገንዘብ ችግር ለመቋቋም ተቀማጩን ከግምጃ ቤት አውጥቶ ለመስጠት ተገዷል ነው ያሉት። በመሆኑም ተቀማጩ ገንዘብ በ 10 ቢሊዮን ዶላር ቀንሷል። የብሔራዊው ገንዘብ ዋጋ ዝቅ እንዲል መደረጉም ቀውሱን ሊገታው እንዳልቻለ እንዲህ ሲሉ ነበረ የበኩላቸውን ምላሽ በሩሲኛ ቋንቋ የሰጡት።

«መሠረተ -ልማቱ በእርግጥ ሲከሽፍ፣ ሲወድም፣ ኢንዱስትሪአችንም መሥራት ፣ማምረት ሲያቅተው፣ በነጻ ገበያ የገንዘብ ልውውጥ ፣ ጥሩ ዋጋ አገኛለሁ ብሎ ማሰብ፣ ሕልም ነው»።

Treffen Putin & Hollande & Merkel & Poroschenko ARCHIV Oktober 2014
ምስል picture-alliance/dpa/A. Nikolsky

የማይዳኑ አብዮት ድል ተቀዳጅቷል ቢባልም፤ መሪር ጽዋ መጎንጨት ግድ ነው የሆነው። ቁጥራቸው ከ 4,700 በላይ የሚገመት ዩክሬናውያን ሕይወት ጠፍቷል፤ ደሴት አከል ምድር ክሪም(ክራይሚያ)ም በሩሲያ ተጠቅሏል። ከቀዝቃዛው ጦርነት ፍጻሜ ወዲህ፣ ዩክሬይን ለሩሲያና ምዕራቡ ዓለም እጅግ መቃቃር ሰበብ ሆናለች።

ባለፈው መስከረም በሚንስክ፤ ቤላሩስ በተፈረመው ውዝግብ ማስወገጃ ውል መሠረት ፤ ከጥቂት ቀናት በፊት የኪቭ ባለሥልጣናትና ከኪቭ ያፈነገጡት የምሥራቁ የአገሪቱ ከፊል ተጠሪዎች በመቶ የሚቆጠሩ የጦር ምርኮኞች ልውውጥ ለማድረግ መብቃታቸው የሚታወስ ነው። ውዝግቡን ለዘለቄታው ለመፍታት ባለመቻሉ ፤ የዲፕሎማሲው ጥረት እንደቀጠለ ነው። ፕሬዚዳንት ፔትሮ ፖሮሼንኮ፣ ጥር 7 ቀን 2007 ዓ ም ካዛኽስታን ውስጥ ከሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላዲሚር ፑቲን፣ እንዲሁም ከፈረንሳይና ከጀርመን መሪዎች ጋር ተገናኝተው ለመወያያት በዝግጅት ላይ ይገኛሉ።

ተክሌ የኋላ

ልደት አበበ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ