1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የዩክሬን ዉጊያ፤ የሐያላኑ ዉዝግብና የዓለም ፀጥታ

ሰኞ፣ የካቲት 2 2007

ዲፕሎማሲዉን ደጋግሞ ከመሞከር ይልቅ ከተፋላሚ ሐይላት አንዱን ለይቶ መቅጣት፤ሌላዉን ማስታጠቁ መፍትሔ ይሆን ይሆናል።መፍትሔዉ ሠላማዊ ሊሆን ግን አይችልም።ሐያላኑ ልዩነት፤አለመግባባታቸዉን «በጠመንጃ ሐይል» ለመፍታት እያሰቡ ወይም እየሞከሩ ለደካማዉ ዓለም ችግር ፍትሐዊ መፍትሔ አለን ቢሉ ፈርቶ እንጂ ወዶና አምኖ የሚቀበል መኖሩ አጠራጣሪ ነዉ

https://p.dw.com/p/1EYhu
ምስል picture-alliance/dpa/T. Hase

የሶሪያ ተፋላሚ ሐይላትን እንዲሸመግሉ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እና የአረብ ሊግ ሾመዋቸዉ የነበሩት የቀድሞዉ የዓለም ድርጅት ዋና ፀሐፊ ኮፊ አናን «ባለስድስት ነጥብ» ያሉትን ዕቅድ በነደፉ በስድስተኛ ወሩ ነበር ሥልጣን የለቀቁት።አናን፤ መጋቢት-2012 (ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎርጎሮሳዉያኑ አቆጣጠር ነዉ) ተሾመዉ ነሐሴ ላይ ሽምግልናቸዉን ለማቋረጣቸዉ የሰጡት ምክንያት «የፀጥታዉ ምክር ቤት ቋሚ አባላት፤ በሶሪያ ጉዳይ አግባቢ አቋም አልያዙም» የሚል ነበር።የዩክሬኑ ቀዉስ ሲቀጣጠል ደግሞ እኒያ ዓለምን ይመራሉ የሚባሉት ሐያል መንግሥታት ተፃራሪ አቋም መያዘቸዉን አረጋገጡ።ዘንድሮ ተካረዋል።ሰበብ፤ ምክንያት፤ሒደት ዉጤቱን በጨረፍታ እንቃኛለን።ላፍታ አብራችሁኝ ቆዩ።

አንጋፋዉ የዩናይትድ ስቴትስ ወግ አጥባቂ (ሪፐብሊካን) ፖለቲከኛ ጆን ማኬይን የሐገራቸዉን ጥቅም ለማስከበር ጠንካራ አቋም ያላቸዉ መሆኑ በርግጥ አያጠራጥርም።በተደጋጋሚ እንዳሉት ወይም እንዳደረጉት ግን የሐገራቸዉን መርሕ የሚቃወሙ ወገኖችን ሐሳብ ለመስማት፤ የተቃዋሚዎቹን የመቃወሚያ ሰበብ ምክንያት ለማስተንተን፤ ተቃዋሚዎቹ የሚወክሉትን ሕዝብ ፍላጎትና ብዛት ለማወቅ፤ ወይም ዓለም አቀፍ ሕግን ለማክበር ደንታ የላቸዉም።

ዛሬ የኪየቭን ቤተ-መንግሥት የሚቆጣጠሩት ሐይላት የአደባባይ ተቃዉሞ ሠልፈኛ በነበሩበት-ሐቻምና ይኽኔ ማይዳን አደባባይ ድረስ ወርደዉ ለሠልፈኞቹ ሙሉ ድጋፋቸዉን ለመግለጥ፤ ሕግም፤ፖለቲካም፤አላገዳቸዉም።

«የዩናይትድ ስቴትስ ሕዝብ» ከሠልፈኞቹ ጎን መቆሙን አረጋገጡ።ማኬይን ደጋግመዉ እንደሚሉት ለሶሪያ፤ ለሰሜን ኮሪያ፤ ለዩክሬን ወይም ለሌሎች ሐገራት ፖለቲካዊ ቀዉስ ይሁን ወታደራዊ ግጭት ወይም፤ ለኢራን የኑክሌር ዉዝግብ መፍትሔዉ አንድ ነዉ።ከሆነ በፖለቲካዊ ካልሆነ በጦር ሐይል-ጣልቃ መግባት።

Deutschland Münchner Sicherheitskonferenz 2015 MSC Angela Merkel CLOSE
ምስል Reuters/M. Rehle

ሐቻምና ዩክሬን ዉስጥ መንግሥታቸዉና ተባባሪዎቹ በተዘዋዋሪ፤ እሳቸዉ በግልፅ የጀመሩት ፖለቲካዊ ጣልቃ ገብነት ዉል ስቶ ዩክሬንን ማመሰቃቀሉን በርግጥ ጠንቅቀዉ ይረዳሉ።ጦርነትን ግን አንድም በቴሌቪዥን አለያም ተማርከዉ እንጂ፤ ተዋግተዉም፤ አዋግተዉም አያቁትም።በሰባ ዘጠኝ ዓመታቸዉም ዘንድሮ-ባለፈዉ ሳምንት ማብቂያ ሙኒክ-ጀርመን ላይ ተሰይሞ ለነበረዉ የዓለም የፀጥታ ጉባኤ ሩሲያን ለማበርከክ የኪየቭ መንግሥት ጦርን ማስታጠቅ አለብን አሉ-ማኬይን።

«አንዳዶች ዩክሬን ሩሲያን በጦር ሐይል አታሸንፍም ይላሉ።ይሕ የተሳሳተ ጥያቄ ነዉ።ትክክለኛዉ ጥያቄ፤-ዩክሬናዉያን ሐገራቸዉን የወረረዉ የሩሲያ ሐይል ወታደራዊ ወጪን እንዲጨምር ካደረጉት፤-ፑቲን፤ ለሕዝባቸዉ የለም እያሉ (የካዱትን) ጦርነት እስከ መቼ ይቀጥሉበታል?-የሚለዉ ነዉ።ለዚሕም ነዉ ለዩክሬን የመከላከያ ጦር መሳሪያ ማስታጠቅ ያለብን።»

የማኬይን አስተሳሰብ የሚያቀነቅኑት የቀድሞዉ የዩናይትድ ስቴትሱ ፕሬዝዳንት ጆርጅ ዳብሊዉ ቡሽ ኢራቅን ለመዉረር በሚጋበዙበት ዘመን ከቶኒ ብሌሯ ብሪታንያ በስተቀር በጸጥታዉ ጥበቃ ምክር ቤት ዉስጥ ድምፅን በድምፅ የመሻር ሥልጣን ያላቸዉ መንግሥታትም ሆኑ፤ ጀርመንን የመሳሰሉ ሐብታም ሐገራት ወረራዉን ተቃዉመዉት ነበር።

የመንግሥታትን ብቻ ሳይሆን የአብዛኛዉን ዓለም ሕዝብ ተቃዉሞ፤ ምክርና ማስጠንቀቂያ ንቀዉ፤ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትን ደንብ ጥሰዉ ኢራቅን የወረሩት የያኔዎቹ የዋሽግተንና የለንደን መሪዎች ከጥፋት፤ ምሥቅልቅል፤ ኪሳራ፤ ሽንፈት ሌላ ለየሐገራቸዉ፤ለኢራቅ፤ ይሁን ለዓለም ሠላም ያተረፉት የለም።አንድ ጊዜ አል-ቃኢዳ፤ ሌላ ጊዜ የሺዓ አክራሪ፤ በቅርቡ ደግሞ ISIS፤ እየተባለ ያን ምድር እስከዛሬ ድረስ የሚያሸብር፤ የሚያተራምሰዉ፤ ሐያሉ ዓለምን ካንዱ ጦርነት ሌላ ወደ ጦርነት የሚያባትለዉ የእልቂት ፍጅት እቶን ባንድ ወይም በሌላ ጎኑ በ2003 ኢራቅ ስትወረር መለኮሱን አለመቀበል በርግጥ ግብዝነት ነዉ።ከዚያ ዓለመማር ደግሞ ዳግም ጥፋት።

Münchener Sicherheitskonferenz 2015 Joe Biden
ምስል Reuters/Michaela Rehle

የጀርመንዋ መራሒተ-መንግሥት ወይዘሮ አንጌላ ሜርክል ባለፈዉ ሳምንት ማብቂያ ለሙኒኩ ጉባኤ እንደነገሩት አብዛኞቹ የአዉሮጳ መንግሥታት ለዩክሬን ቀዉስ የነ ጆን ማኬይን ወታደራዊ መፍትሔ አልተቀበሉትም።

«ይመልከቱ፤-ይሕ ግጭት በወታደራዊ ሐይል አይፈታም የሚል ፅኑ እምነት አለኝ።በዚሕም ምክንያት ጥረታችን በዲፕሎማሲዉ ላይ እንዲያተኩር ወስነናል።አብሮም የአትላንቲክ ማዶ-ለ-ማዶ (መንግሥታት) በሩሲያ ላይ በጋራ ማዕቀብ መጣላቸዉና ለማጠናከር መስማማታቸዉ አስደሳች (ትብብራቸዉን) የሚያሳይ ነዉ።»

አብዛኞቹ የአዉሮጳ መንግሥታት ለዩክሬን መንግሥት ጦር ዘመናይ ጦር መሳሪያ በማስታጠቅ ሩሲያን ማዳካም የሚለዉን የአሜሪካኖችን ሐሳብ የተቃወሙት ሜርክል እንዳሉት ግጭቱ በጦርነት ይፈታል ብለዉ ሥለማያምኑ ብቻ ብይደለም።ከአስራ-ሁለት ዓመት በፊት ኢራቅ ከተፈፀመዉ ሥሕተት ሥለተማሩ ብቻም አይደለም።የጦርነትን መጥፎ ዉጤት ኖረዉ፤ተዉልደዉ፤ አድገዉ፤ የጀርመኑ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ፍራንክ ቫልተር ሽታይን ማየር እንዳሉት ደግሞ ከታሪክ ተምረዉትም ጭምር እንጂ።

Deutschland Münchner Sicherheitskonferenz 2015 MSC Sergei Lawrow
ምስል Reuters/M. Dalder

«ለኛ ለአዉሮጳዉያን፤ ምንም እንኳን አሁን ግጭት ቢኖርብንም፤ መልከዓ ምድራዊ አቀማመጣችንና ታሪካዊ ተሞክራችን (ያስተማረን) ትልቅ ሥፍራ አለዉ።የአዉሮጳ ፀጥታና ደሕንነት ዋስትና የሚኖረዉ ከሩሲያ ጋር እንጂ ሩሲያን በመቃረን አይደለም።(ይሕ ) የአንድ ወገን ብቻ አይደለም።የሩሲያ መፃኤ-ተስፋም የሚሠምረዉ ከዉሮጳ ጋር እንጂ አዉሮጳን በመቃረን እንዳልሆነ ሞስኮ ግልፅ ሊሆንላት ይገባል።»

የፖለቲካ ተንታኞች እንደሚሉት የፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማ መስተዳድር የዩክሬን መንግሥትን እናስታጥቅ የሚለዉን የነሴናተር ጆን ማኬይን አቋም እስካሁን አልደገፈም።የጀርመንና የፈረንሳይ መሪዎች ከመሸ ከፓሪስ፤በርሊን፤ከኪየቭ ሞስኮ የመባተላቸዉ ሰበብ ምክንያት የኦባ መስተዳድር ለተቃዋሚዎቹ ግፊት ከመንበርከኩ በፊት ሰላማዊ መፍትሔ ለማግኘት ነበር።

መራሒተ መንግሥት አንጊላ ሜርክልና ፕሬዝዳንት ፍራንሷ ኦሎንድ ድርድር ዉጤት ሳይታወቅ ብራስልስ የገቡት የዩናይትድ ስቴትሱ ምክትል ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን እንዳሉት ግን መስተዳድራቸዉ ከዲፕሎማሲዉ ይልቅ ጦር መሳሪያ ማስታጠቁን የሚደግፍ ነዉ-የመሰሉት።

«ሥለዚሕ ለዩክሬን ፀጥታ (ማስከበሪያ) ድጋፍ መስጠታችንን እንቀጥላለን።ጦርነትን ለማበረታት አይደለም፤ዩክሬን ራስዋን እንድትከላከል እንጂ።ግልፅ ልሁን፤ ለዩክሬን ወታደራዊ መፍትሔ ይኖራል ብለን አናምንም።የዚያኑ ያክል ግልፅ ልሁን፤ሩሲያዎች አሁን የሚያደርጉትን የማድረግ መብት የላቸዉም።የተከበረ ሠላም መገኘት አለበት ብለን እናምናለን።ከዚሕም በተጨማሪ የዩክሬን ሕዝብ እራሱን የመከላከል መብት አለዉ ብለን እናምናለ።»

አደናጋሪዉ መልዕክት የዓለም ብቸኛ ልዕለ ሐያል ሐገር የዩክሬንን ጦርነት ለማጋም እንጂ በሠላማዊ መንገድ ለመፍታት ግልፅ መርሕ የላትም የሚል አስተያየት ማስከተሉ አልቀረም።ዩናይትድ ስቴትስ ዩክሬንን በግልፅ ካስታጠቀች ደግሞ ሩሲያን ወደ ግልፅ ጦርነት ይስባል የሚል ሥጋት አሳድሯል።የጀርመንዋ መራሒተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል ትናት ወደ ዋሽግተን መጓዛቸዉ የሥጋቱን ንረት ጠቋሚ ነዉ።ሜርክል ከፕሬዝዳንት ባራክ ኦቦማ ጋር ዛሬ የሚያደርጉት ዉይይት ሥጋቱን መቀነስ አለመቀነሱ በርግጥ አልታወቀም።

Deutschland Münchner Sicherheitskonferenz 2015 MSC Petro Poroschenko
ምስል Reuters/M. Rehle

የዉይይቱ ዉጤት ሞስኮዎችን እኩል የሚያወግዙ፤ እኩል የሚቀጡ፤የሚያገልሉት የአትላቲክ ማዶ-ለማዶ ወዳጆችን ልዩነት ለማጥበብ ወሳኝም ነዉ።የዩናይትድ ስቴትሱ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ጆን ኬሪ ግን ወትሮም ልዩነት የለም ባይ ናቸዉ።

«ለሁሉም ላረጋግጥ፤ ክፍፍል የለም፤ መለያየትም የለም።ሰዎች የሆነ ክፍፍል ለመፍጠር እንደሚሞክሩ ሰምቻለሁ።(ይሁንና) አንድ ነን።በቅርብ ተባብረን እየሠራን ነዉ።ይሕ ፈተና በወታደራዊ ሐይል እንደማይፈታ ሁላችንም እናምናለን።በዲፕሎማሲያችን እንደተባበርን ነን።»

ኬሪ ልዩነቱን ለመሸፋፈን መሞከራቸዉ በርግጥ የዲፕሎማሲዉ ወግ ነዉ።የሸፋፈኑትን ለመግለጥ ግን የምክትል ፕሬዝዳንት ጆ ባይደንን መልዕክት ከመከለስ፤ አለያም የሜክርልን ጉዞ ከማጤን ባለፍ አስተንታኝ አያስፈልግም።

ኮፊ አናን ከሁለት ዓመት በፊት በሶሪያ ጉዳይ አንድ አቋም አልያዙም ያሏቸዉ የሞስኮ-ዋሽግተን፤ብራስልስ ሐያላን በዩክሬን ጉዳይ በግልፅ መፃረራቸዉ ከተመሰከረ ሁለኛ ዓመቱን ያዘ።ሴናተር ጆን ማኬይንና ተባባሪዎቻቸዉ የሚገፏቸዉ የአሜሪካ ፖለቲከኞች ለዩክሬን መንግሥት ጦር መሳሪያ እናስታጥቃለን ማለታቸዉ ደግሞ በአዉሮጳና በአሜሪካ መካክል የልዩነት መስመር መተለሙ እየፈጋ ነዉ።የሩሲያዉ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ሰርጌይ ላቭሮቭ ልዩነቱን ለማጩዋጩዋሕ፤ የአዉሮጳ ሕብረትን የዋሽግተኖች ተቀፅላ ለማድረግ ጊዚ አላጠፉም።

«እንዳለመታደል፤ የዩክሬን ቀዉስ በየደረሰበት ደረጃ ሁሉ የአሜሪካ ባልደረቦቻችን እና በነሱ ተፅኖ ሥር ያለዉ የአዉርጳ ሕብረት የሚወስዱት እርምጃ ሁሉ ግጭቱን የሚያባብስ ነዉ።የአዉሮጳ ሕብረት የሩሲያን ተሳትፎ አልቀበልም ብሎ ዩክሬንን የምጣኔ ሐብት ትብብር ክበብ አካል ሲያደርጋት የሆነዉ ይኸዉ ነበር።ለመፈንቅለ መንግሥቱ፤ ከዚያ በፊት ደግሞ ለፀረ-መንግሥት ሠልፉ ቀጥተኛ ድጋፍ ሲደረግም ይኸዉ ተፈፅሟል።የኪየቭ ባለሥልጣናት ብሔራዊ ድርድር ከማድረግ ይልቅ፤ሥለተቃወሟቸዉ ብቻ የራሳቸዉን ዜጎች በአሸባሪነት ሲወነጅሉ፤ መጠነ ሠፊ ወታደራዊ ዘመቻ ሲከፍቱና ፅንፈኛ ብሔረተኞችን ሲደራጁ የምዕራብ ወዳጆቻችን በተደጋጋሚ በቸልታ ማለፋቸዉም ግጭቱን አባብሶታል።»

የሞስኮ ዉግዘት ማስጠንቀቂያ በምዕራባዉያን የሚደገፉትን የዩክሬን ፖለቲከኞች ከአደባባይ ተሠላፊነት ወደ ሐገርገር ገዢነት ከመለወጥ አልገታም።የሚገዟት ሐገር ግን ገሚስ ግዛቷ የተቆርሰባት፤ የገሚስ ጎኗ ሕዝብ የሚያልቅባት፤ጥቅል ሕልዉናዋ የተመሰቃአለባት መሆኑ እንጂ ጭንቁ።

Deutschland Münchner Sicherheitskonferenz 2015 Steinmeier, Fabius und Kerry
ምስል Jim Watson/AFP/Getty Images

ምዕራባዉያን መንግስታት በሩሲያና ተባባሪዎችዋ ላይ የጣሉት ማዕቀብ የሩሲያን ምጣኔ ሐብት መጉዳቱ በርግጥ አላጠያየቀም። የሞስኮ ዉግዘት ማስጠንቀቂያ የዩክሬን የአደባባይ ሰልፈኞቹን ቤተ-መንግሥት ከመዶል እንዳልገታ ሁሉ የምዕራባዉያን ዛቻ ፤ማስጠንቀቂና ማዕቀብምየሩሲያን እርምጃ አላስቆመም።

ዘግይቶ የተጀመረዉ ድርድር ዲፕሎማሲም ቢያንስ እስካሁን ለዉጤት አልበቃም።ዲፕሎማሲዉን ደጋግሞ ከመሞከር ይልቅ ከተፋላሚ ሐይላት አንዱን ለይቶ መቅጣት፤ሌላዉን ማስታጠቁ መፍትሔ ይሆን ይሆናል።መፍትሔዉ ሠላማዊ ሊሆን ግን አይችልም።ሐያላኑ ልዩነት፤አለመግባባታቸዉን «በጠመንጃ ሐይል» ለመፍታት እያሰቡ ወይም እየሞከሩ ለደካማዉ ዓለም ችግር ፍትሐዊ መፍትሔ አለን ቢሉ ፈርቶ እንጂ ወዶና አምኖ የሚቀበል መኖሩ አጠራጣሪ ነዉ። ነጋሽ መሐመድ ነኝ ቸር ያሰማን።

ነጋሽ መሐመድ

ተክሌ የኋላ