1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የየመን ጦርነት እና እልቂት

ነጋሽ መሐመድ
ሰኞ፣ መስከረም 30 2009

ሰዎቹ ፖለቲከኛ፤ ወታደር፤ነጋዴ፤አስተማሪ፤ የመንግስት ሙያተኛ ወይም የቤት ሰራተኛ ይሆኑ ይሆናል።ቅዳሜ ከዚያ አዳራሽ የሰባሰባቸዉ ግን ለቅሶ ነበር።ሁለት አዉሮፕላኖች መጡ።ካዳራሹ ዉጪ የነበረዉ ሰዉ ሽቅብ ከማንጋጠጡ፤ አካባቢዉ ተደበላለቀ

https://p.dw.com/p/2R5k2
Jemen Begräbnis von Abdul Qader Helal Bürgermeister von Sanaa
ምስል Reuters/K. Abdullah

የየመን ጦርነት እና እልቂት

 የሪያድ ነገስታት የዛሬ ሁለት ዓመት ግድም «በሰወስት ወር» እናጠናቅቀዋለን ያሉት ዉጊያ ዓመት ከመንፈቅ አለፈዉ።የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የየመን ተፋላሚ ሐይላትን ለማስታረቅ ያረቀቀዉ ሰነድ ለነበር ታሪክ ከተዘጋ ወራት አለፉት።የመን ዕለት በዕለት ትጠፋለች።ዜጋዋ ተራ በተራ ያልቃል።ሐኪም ቤት፤ መኖሪያ ቤት፤ የገበያ አዳራሽ በቦም ሚሳዬል-ይወድማሉ።ቅዳሜ ተረኛዋ ሰነዓ፤ ወዳሚዉ ለቅሶ ቤት፤ ሟች፤ ቁስለኞች ለቀስተኞች ነበሩ።ሐገሩ ጭቆና፤ግፍ በደል፤ ድሕነት አስመርሮት የተሰደደዉ ኢትዮጵያዊም ለየመን የዉጊያ ቆሌ ጭዳ እየሆነ።የየመን ጦርነትና ጥፋት ያፍታ ዝግጅታችን ትኩረት ነዉ።

የሶሪያዉ ዉጊያ እና የዋሽግተን-ሞስኮዎች ዉዝግብ ያጠላበት የየመኑ ጦርነት የሚያደርሰዉ ጥፋት ዛሬም ካፍታ ዜናነት ባለፍ የዓለም መገናኛ ብዙሐን ትኩረት አልሳበም።የመኖች ግን በርግጥ ያልቃሉ።ባለፈዉ ቅዳሜ ሰነዓ ላይ የደረሰዉን ጥፋት ያየ አንድ የከተማዋ ነዋሪ  «በሩሲያ የሚደገፈዉ የሶሪያ መንግሥት ጦር አሌፖ ላይ ያደረሰዉ ጥቃት ቢሆን ኖሮ» አለ ለፈረንሳዩ ዜና አገልግሎት «ዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ ምን እንደሚል አስብ።» ይላሉ።
የሁቲ አማፂያን የመሠረቱት መንግሥት የጤና ሚንስትር ጋዚ ኢስማኢል ተጠያቂዉ ማን ሆነና ዕይነት ጥያቄዊ መልስ አላቸዉ
                             
«በየመን እና በሕዝቧ ላይ ለደረሰዉ ለዚሕ አሳዛኝ ጥፋት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትን ተጠያቂ እናደርጋለን።»
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አንድ ሥራዉ አልተጓደለም።ሟች ቁስለኛ ይቆጥራል።ድርጅቱ በቅርቡ እንዳስታወቀዉ ሳዑዲ አረቢያ መራሹ ጦር የመንን በጦር ጄት መደብደብ ከጀመረ ከሐቻምና መጋቢት ጀምሮ የተገደሉት ሰዎች ቁጥር ዘጠኝ ሺሕ ነዉ።ከ3 ሚሊዮን የሚበልጥ ተሰድዷል።
ይሕ ቁጥር ባለፈዉ ቅዳሜ ሰነዓ ዉስጥ የተገደሉትን አይጨምርም።ሰዎቹ ፖለቲከኛ፤ ወታደር፤ነጋዴ፤አስተማሪ፤ የመንግስት ሙያተኛ ወይም የቤት ሰራተኛ ይሆኑ ይሆናል።ቅዳሜ ከዚያ አዳራሽ የሰባሰባቸዉ ግን ለቅሶ ነበር።ሁለት አዉሮፕላኖች መጡ።ካዳራሹ ዉጪ የነበረዉ ሰዉ ሽቅብ ከማንጋጠጡ፤ አካባቢዉ ተደበላለቀ።ወዲያዉ ሌላ ሚሳዬል።ሌላ ትርምስ።
                                        
የሰነዓዉ ተባባሪ ዘጋቢያችን ግሩም ተክለ ኃይማኖት እንደታዘበዉ ጥቃቱ የተጠና ይመስላል።
                          

Jemen Luftangriffe in Sanaa mit Dutzenden Toten und Verletzten
ምስል Getty Images/AFP/M. Huwais

ለቀስተኛዉ ካዳራሹ የታደመዉ የሁቲ አማፂያን ከፍተኛ ባለሥልጣን አባት በመሞታቸዉ ነበር። የቀድሞዉ ፕሬዝደንት የዓሊ አብደላ ሳላሕ ልጆችን ጨምሮ የሁቲና የደጋፊዎቻቸዉ የፖለቲካ ማሕበራት ከፍተኛ ባለሥልጣናት፤ የጎሳ መሪዎችም ነበሩ።
                              
ዓለም አቀፍ የዜና ምንጮች እስካሁን ድረስ የሟቹን ቁጥር አንድ መቶ አርባ እንዳሉት ነዉ።የሪያዱ ወኪላችን ስለሺ ሽብሩ እንደሚለዉ አዳራሹ የተመታዉ ሆን ተብሎ እንደሆነ የሳዑዲ አረቢያ ጋዜጦችም ፍንጭ ሰጥተዋል።
                     
ጥቃቱ የሁቲ አማፂያን መሪዎች ባንድ አዳራሽ እንዳሉ ለመፍጀት ያለመ-መሆን አለመሆኑ ለየመኖች ትርጉም የለዉም።በተለይ ትናንት ጥቃቱን ለማዉገዝ ሰነዓ አደባባይ የወጣዉ ሕዝብ እንደሚለዉ ሐዘን በተቀመጡ ሰዎች ላይ የተፈፀመ ዘግናኝ ወንጀል ነዉ።
                          
«ይሆናል ተብሎ የማይታሰብ ዘግናኝ ወንጀል ነዉ።የሐዘን አዳራሽ ይደበድባሉ ብሎ ማንም አያስብም።ለቅሶ የተቀመጠ ሕዝብን መግደል---እንዴት?»
ጥያቄ እንጂ መልስ የለም።ሳዑዲ አረቢያ መራሹ ጦር ሰላማዊ ወይም ያልታጠቁ ሰዎች የተሰበሰቡ ወይም የሚኖሩበትን አካባቢ በጦር ጄት ሲደበድብ የቅዳሜዉ የመጀመሪያዉ አይደለም።በጦርነቱ ከተገደሉት ዘጠኝ ሺሕ ሰላማዊ ሰዎች ከግማሽ የሚበልጡት የተገደሉት በተባባሪዎቹ ሐገራት የጦር ጄቶች ድብደባ ነዉ።
ትምሕርት ቤት፤ ሐኪም ቤት፤ መኖሪያ አካባቢ በቦምብ ወይም በሚሳዬል ሲመታ የሚፈጠረዉን የመገናኛ ዘዴዎች ያንድ ሰሞን ጫጫታን ለማቀዝቀዝ ሁሌም እንደሚደረገዉ ሁሉ የቅዳሜዉ ድብደባ የጫረዉን ጩኸት ለማስከንም፤  የሪያድ ነገስታት «እናጣራለን» እያሉ ነዉ።ጂዳ የሚኖረዉ ጋዜጠኛ ነብዩ ሲራክ የታዘበዉ አለ።
                            
የሁቲ አማፂያንና የተባባሪያቸዉ የቀድሞዉ ፕሬዝደንት የዓሊ አብደላ ሳላሕ ጦር በሳዑዲ አረቢያ ላይ አፀፋ ጥቃት ለመሰንዘር ጊዜ አልወሰደም።ሳዑዲ አረቢያን በሚሳዬል ለመምታት ሞክረዋል።ዛሬም ደግመዉታል።
                                 
ከጥቂት ወራት በፊት የተፋላሚ ሐይላት ተወካዮች ኩዌት ዉስጥ መደራደር ሲጀምሩ በሰላም ያበቃል የሚል ተስፋ ተጥሎበት የነበረዉ ጦርነት አሁን ይበልጥ የተጋጋመ ነዉ የመሰለዉ።የሰነዓዉ ተባባሪ ዘጋቢያችን ግሩም ተክለ ሐይማኖት እንደሚለዉ የሰላም ድርድር ብሎ ነገር መነገር ካቆመ ወራት ተቆጥረዋል።የዘመቻ ክተት ነዉ-የሚሰማዉ።በኢራን ይደገፋሉ የሚባሉትን የሁቲ አማፂያንን ለማጥፋት ሳዑዲ አረቢያና ተከታዮቹ የጀመሩት የዓየር ድብደባ የተባባሪዎቹን ሐገራት በተለይም የአስተባባሪዋን የሳዑዲ አረቢያን ምጣኔ ሐብት እየተፈታተነ ነዉ።ሳዑዲ አረቢያ ለጦርነቱ ከ5.3 ቢሊዮን ዶላር በላሽ ከስክሳለች።
                 
የመን ላይ የደረሰዉ የመሠረተ ልማት አዉታር ዉድመት ከ14 ቢሊዮን በላይ ተገምቷል።ጥፋቱ ለስደተኞች በተለይ ሰብሳቢ መንግሥት ለሌላቸዉ ኢትዮጵያን ስደተኞች መድረሱ ሌላዉ አሳዛኝ ክስተት ነዉ።ድሕነትና ጭቆናን የሸሹ ኢትዮጵያዉያን ከባሕር ከተረፉ፤ አጋቾች-ይጫወቱባቸዋል። ካጋቾች ካመለጡ አሸባሪዎች፤ ከነዚሕ ከተረፉ በጦርነቱ መሐል የጥይት ሰለባ ይሆናሉ።                               
ግሩም ያክልበታል።ጦርነቱ ቀጥሏል።ጥፋቱም። እኛ ይብቃን። 

Yemen Sanaa Saleh al-Samma hinter Schusssicherem Glas
ምስል Reuters/K.Abdullah
Jemen Selbstmordanschlag in Aden
ምስል Reuters/F. Salman

ነጋሽ መሐመድ

ሸዋዬ ለገሰ