1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የዞን 9 የድረገፅ ጸሐፍት ችግር እና የጉዞ እገዳ

Eshete Bekeleሐሙስ፣ ኅዳር 9 2008

የዞን ዘጠኝ የድረ-ገጽ ጻሕፍት አባል የሆነው ዘላለም ክብረት የድንበር የለሽ የጋዜጠኞች ተሟጋች ድርጅት ሽልማትን ለመቀበል ወደ ፈረንሳይ ለመጓዝ ሲሞክር ተከለከለ። በእስር ቆይተው ከተፈቱት ጋዜጠኞችና የድረ-ገጽ ጻሕፍት መካከል ፓስፖርቶቻቸው ያልተመለሰላቸው ወደ ቀድሞ የስራ ገበታቸው መመለስ የተከለከሉ መኖራቸውንም አስታውቀዋል።

https://p.dw.com/p/1H95j
Äthiopien Zone9 Blogger Gruppe
ምስል Zone9

[No title]

ከድንበር የለሽ የጋዜጠኞች ተሟጋች ድርጅት "የዓመቱ ምርጥ ጦማሪ" ሽልማት የተበረከተላቸው የዞን ዘጠኝ ጦማሪያን አባል ዘላለም ክብረት ከአገር እንዳይወጣ ታገደ። ጦማሪያኑ ኅዳር 8 ቀን 2008 ዓ.ም. ባወጡት መግለጫ ዘላለም ክብረት በሽልማት ፕሮግራሙ ለመሳተፍ ወደ ፈረንሳይ ለመጓዝ «ቦሌ አየር ማረፊያ ቢገኝም ባልታወቀ ምክንያት ከአገር መውጣት ተከልክሎ ፓስፓርቱንምተቀምቷል፡፡» ሲሉ አስታውቀዋል። በውሳኔው ተደናግጠናል ያሉት በድንበር የለሽ የጋዜጠኞች ተሟጋች ድርጅት የአፍሪቃ ክፍል ኃላፊዋ ክሊያ ካህን ከጸጥታ ኃይሎች የተሰጠ አሳማኝ ምክንያት አለመኖሩን ይናገራሉ።

«የሰጡት አንዳች አሳማኝ ምክንያት የለም። ከዞን ዘጠኝ ጦማሪያን ጋር ታስረህ ስለነበር መጓዝ አትችልም ብቻ ነው ያሉት። እስካሁን ድረስ ዘላለም ፓስፖርቱ አልተመሰለትም። ነገር ግን ወደ ፖሊስ በመሄድ ያመለከተ ሲሆን ምርመራ እንደሚደረግ ተነግሮታል። ነገር ግን በምን ምክንያት ከጉዞ እንደተከለከለ አንዳችም ምክንያት አልተሰጠውም።»

ከአንድ አመት ከሁለት ወር እስከ አንድ አመት ከአምስት ወር ድረስ በእስር የቆዩትና በ2007 ዓ.ም. መገባደጃና በ2008 ዓ.ም. መጀመሪያ የተፈቱት ጋዜጠኞችና ጦማሪያን መካከል ከአንዱ በቀር ክሳቸው ተቋርጧል። ጦማሪ በፍቃዱ ሃይሉ በዋስትና ላይ ሆኖ የቀረበበትን “አመጽ የማነሳሳት ክስ” እንዲከላከል ተወስኗል። በዋስትና ላይ ከሚገኘው ጦማሪ በፍቃዱ ሃይሉ በስተቀር በሌሎቹ ላይ የጉዞ ገደብ አልተጣለም። ክሊያ ካህን ከጦማሪዎቹ መካከል አሁንም ፓስፖርታቸው ያልተመለሰላቸው መኖራቸውን ይናገራሉ።

«በተላለፈው ውሳኔ መሰረት የጉዞ ገደብ አልተደረገባቸውም። ዘላለም ክብረትን ጨምሮ በሐምሌ ወር ከእስር የተፈቱት ጦማሪያን ፓስፖርታቸው ተመልሶላቸዋል። ሌሎቹ ጦማሪያን ግን እስካሁን ድረስ ፓስፖርቶቻቸው አልተመለሰላቸውም። ይህ የጉዞ ገደብ ስለመሆኑ በግልጽ የሚታወቅ ነገር የለም። እርምጃው ህጋዊ መሰረት ያለው ስለመሆኑ የምናውቀው ነገር የለም። ህጋዊ መሰረት ያለው ከሆነ እንኳ ፓስፖርቶቻቸውን የያዙት ባለስልጣናት እርምጃቸውን የሚገልጽ ደብዳቤ አሊያም ፍትሃዊ ውሳኔ ማቅረብ አልቻሉም።»

Äthiopien Zone9 Blogger Gruppe
ምስል Zone9

የዞን ዘጠኝ ጦማሪያን «የዓመቱን ምርጥ ጦማሪ ሽልማት» ያሸነፉት ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት በተገደበባት ኢትዮጵያ ላበረከቱት አስተዋጽዖ መሆኑን በድንበር የለሽ የጋዜጠኞች ተሟጋች ድርጅት የአፍሪቃ ክፍል ኃላፊ የሆኑት ክሊያ ካህን ተናግረዋል። ጦማሪያኑ «ሃሳብን ለመግለጽ ነጻነት ላበረከቱት» ከዓለም አቀፉ የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች ድርጅት(CPJ) ሁለተኛ ሽልማት በሚቀጥለው ሳምንት የተበረከተላቸው ቢሆንም በፕሪግራሙ ላይ ለመታደም ስለመቻላቸው እርግጠኛ አለመሆናቸውን በመግለጫቸው አስታውቀዋል።

ጦማሪያኑ ባወጡት መግለጫ አቤል ዋበላ፤ዘላለም ክብረት እንዲሁም ጋዜጠኛ ኤዶም ካሳዬ «ከእኛ ቁጥጥር ውጪ በሆነው መንገድ ተገደን ከአንድ አመት በላይ እስር ቤት መቆየታችን የእኛ ጥፋትአንደሆነ ተቆጥሮ» ወደ ስራ ገበታችን መመለስ ተከልክለናል ሲሉ አስታውቀዋል። በመግለጫው « ህግ መንግስታዊ መብታችን የሆነውእና ምንም ህጋዊ ገደብ ያልተቀመጠበት በነጻነት የመንቀሳቀስ መብታችን እንዲመለስልን» ያሉት ጦማሪያን «አሁንም እስረኞች ነን» ብለዋል።

እሸቴ በቀለ

አዜብ ታደሰ