1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የዞን ዘጠኝ ጦማሪዎች የፍርድ ቤት ውሎ

ረቡዕ፣ ነሐሴ 13 2007

በኢትዮጵያ የጸረ-ሽብርተኝነት አንቀጽ ክስ ቀርቦባቸው በእስር ላይ የሚገኙት አራት የዞን ዘጠኝ ጦማሪዎች ዛሬ ፍርድ ቤት ቀረቡ። በአራቱ ጦማርያን ላይ ብይን ለመስጠት የተሰየመው ችሎት ለነሐሴ 18 ፣2007 ዓም አዲስ ቀጠሮ ሰጥቷል።

https://p.dw.com/p/1GHzf
Symbolbild Blog Blogging Internet
ምስል Fotolia/Claudia Paulussen

[No title]

በኢትዮጵያ የፀረ-ሽብር ህግ ክስ የቀረበባቸው በፍቃዱ ሐይሉ፤ናትናኤል ፈለቀ፤አቤል ዋበላና አጥናፉ ብርሃኔ ላይ ጥፋተኛ መሆን አለመሆናቸው ላይ ብይን ለመስጠት ዛሬ የተሰየመው ፍርድ ቤት «ብይኑን የመስራት ሂደቱ ተጀምሯል።» በማለት እንደተገለጸላቸው ጠበቃ አምሃ መኮንን ተናግረዋል። ይሁንና «ሰነዱ በርካታ ከመሆኑ አንጻር ለዛሬ ማጠናቀቅ እንዳልተቻለ ነው የተገለጸልን » ያሉት ጠበቃ አምሃ ሐሀ ለነሐሴ 18 ቀን 2007 ዓ.ም. አዲስ ቀጠሮ መሰጠቱን አረጋግጠዋል።

በእነ ሶልያና ሽመልስ የክስ መዝገብ በፌደራል አቃቤ ህግ የሽብር ክስ መስርቶባቸው ከአንድ አመት በላይ በእስር ከቆዩት ጦማሪዎችና ጋዜጠኞች መካከል ተስፋለም ወልደየስ፤ አስማማው ሃይለጊዮርጊስ ፤ኤዶም ካሳዬ ፤ ዘላለም ክብረትና ማህሌት ፋንታሁን ሐምሌ አንድና ሐምሌ 2 ፣ 2007 ዓም ተፈተዋል ። የኢትዮጵያ መንግስት ባለስልጣናት የሶስቱ ጋዜጠኞችና የሁለቱ ጦማሪዎች ክስ መነሳቱን ለመገናኛ ብዙሐን ቢናገሩም የተፈቱበት ሂደት ግን አነጋጋሪ መሆኑ አልቀረም። ጦማሪዎቹና ጋዜጠኞቹ የቀረበባቸው ክስ «በተመሳሳይ የህግ አንቀጽ» የቀረበ በመሆኑ አሁን በእስር ያሉት መፈታት ይገባቸዋል ሲሉ ጠበቃ አምሃ መኮንን ተናግረዋል።

‘የሽብር ተግባርን ማቀድ ማሴር ማነሳሳትና መፈጸም’ እና‘ህገ መንግሰታዊ ስርአቱን በሃይል መናድ‘ የሚሉ የህግ አንቀጾች ተጠቅሶባቸው የነበሩትና በድንገት የተፈቱት አምስቱ ተካሳሾች ስጋት አለብን ሲሉ ይደመጣል ። «አቃቤ ህግ ክሱን ካነሳ በኋላ ለወንጀሉ የተቀመጠው የይርጋ ጊዜ ከማለቁ በፊት በማናቸውም ጊዜ ሊያንቀሳቅስ እንደሚችል ህጉ ስልጣን ይሰጣል።» የሚሉት የጦማሪዎቹ ጠበቃ አምሃ መኮንን «መንግስት ክሱን ያነሳው በተከሳሾቹ ላይ በቂ መረጃ እንደሌለ ስላመነ» እንደሆነ ያስረዳሉ። ከዚህ በኋላም የተለየ ማስረጃ በሌለበት ሁኔታ በተፈቱት ጦማሪዎችና ጋዜጠኞች ላይ ክሱ ሊቀጥል እንደማይችል ተናግረዋል።

እሸቴ በቀለ

ሒሩት መለሰ