1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የዛምቢያ የአፍሪቃ ዋንጫ ድል

ሰኞ፣ የካቲት 5 2004

በኤኩዋቶሪያል ጊኒና በጋቡን የጋራ አስተናጋጅነት ለሶሥት ሣምንታት ያህል የተካሄደው የዘንድሮው የአፍሪቃ እግር ኳስ ዋንጫ ፍጻሜ ውድድር ባለፈው ምሽት ሊበርቪል ላይ በዛምቢያና በአይቮሪ ኮስት ግጥሚያ ተፈጽሟል።

https://p.dw.com/p/142kr
ምስል picture-alliance/dpa

በኤኩዋቶሪያል ጊኒና በጋቡን የጋራ አስተናጋጅነት ለሶሥት ሣምንታት ያህል የተካሄደው የዘንድሮው የአፍሪቃ እግር ኳስ ዋንጫ ፍጻሜ ውድድር ባለፈው ምሽት ሊበርቪል ላይ በዛምቢያና በአይቮሪ ኮስት ግጥሚያ ተፈጽሟል። ጨዋታው 0-0 ካበቃ በኋላ በፍጹም ቅጣት ምት 8-7 ነበር የተፈጸመው። የአሸናፊው ቡድን ፈረንሣዊ አሰልጣኝ ሄርቭ ሬናርድ የቡድኑን የመንፈስ ጥንካሬ በማንሳት ሲያወድስ ድሉን ዛሬ ማለዳ ላይ አያሌ የዛምቢያ ዜጎች አደባባይ በመጉረፍ በደመቀ ሁኔታ አክብረውታል።

«ብዙ ልምምድና ዝግጅት ነው ያደረግነው። አናም ይህ የዚህ ጥረታችን ካሣ ነው። እርጋታና ጥንካሬው ከየት እንደመጣ ባላውቅም በጣም በጅቶናል። ተጫዋቾቹ ለቡድኑና እንዲሁም እርስብርሳቸው አንድ ነበሩ። ጥሩ የቡድን መንፈስ ነው የታየው»

ዛምቢያ ከ 19 ዓመታት በፊት 18 ተጫዋቾቿ በአውሮፕላን አደጋ ባለቁባት በጋቡን የዋንጫ ባለቤት ለመሆን መብቃቷ አሳዛኝ ትውስትን ቢቀሰቅስም አጽናኝና ታሪካዊም ጭምር ነው የሆነው። ፍጹም ቅጣት ምቶቹ እንደ ሟቾቹ ቁጥር 18 መሆናቸውም የአጋጣሚም ቢሆን የሚያስገርም ነበር። ለቡድኑ ያልተጠበቀ ጥንካሬ ምናልባት ይሄው ትውስት ዋናው ምክንያት ሳይሆን አልቀረም።

ለማንኛውም ዝቅተኛ ግምት ተሰጥቶት ከሊበርቪሉ የጋቡን የወዳጅነት ስታዲዮም የገባው የዛምቢያ ብሄራዊ ቡድን በአርባ ሺህ ተመልካች ፊት የጨዋታ ልዕልና ሲያሳይ የአይቮሪ ኮስት ዓለምአቀፍ ከዋክብት በአንጻሩ በፍርሃት መጠመዳቸው ተንጸባርቋል። በተለይም የቼልሢው ኮከብ ዲዲየር ድሮግባ በ 70ኛዋ ደቂቃ ላይ ያገኛትን ፍጹም ቅጣት ምት መሳቱ የዚሁ ውጤት ነበር።

ድሮግባ ክስድሥት ዓመታት በፊትም ከግብጽ ጋር በተደረገ ፍጻሜ ግጥሚያ እንዲሁ ፍጹም ቅጣት ምት በመሳት ለአይቮሪ ኮስት ሽንፈት ምክንያት መሆኑ የሚዘነጋ አይደለም። በነገራችን ላይ በትናንቱ ፍጻሜም ሌሎቹ የአይቮሪ ኮስት የእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ተጫዋቾች ኮሎ ቱሬና ጌርቪኞ የየበኩላቸውን ቅጣት ምት ስተዋል። በሌላ በኩል የዛምቢያ ድል እንዲያው በአጋጣሚ የተገኘ አልነበረም።

Africa Cup Didier Drogba
ምስል picture-alliance/dpa

ቡድኑ ከዚህ የደረሰው በግማሽ ፍጻሜው ጋናንና በፍጻሜውም አይቮሪ ኮስትን የመሳሰሉ ቀደምት ሃገራት አሸንፎ መሆኑ ግምት ሊሰጠው ይገባል። ዛምቢያ በተለይም ብሄራዊ ቡድኗን በአውሮፕላን አደጋ ካጣች በኋላ መልሶ ለመነሳት በትልቅ ትዕግሥትና በቁርጠኝነት ተግታ ምስራቷ ነው ዛሬ ፍሬ እንድታይ ያደረጋት። እዚህ ላይ በተለይም የአገሪቱ እግር ኳስ ፌደሬሺንና ክለቦች በጣሙን ሊመሰገኑ የሚገባቸው ናቸው። የብሄራዊው ቡድን ተጫዋቾች በአብዛኛው በአገር ውስጥ የሚጫውቱ መሆናቸውም ሌላው አኩሪ ጉዳይ ነው።

በነገራችን ላይ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሺን ከዚህ ከዛምቢያ ዕርምጃ ብዙ ሊማር ይችላል። ለማንኛውም ዛምቢያ የትናንቱን ጨምሮ ለሶሥተኛ ጊዜ ከፍጻሜ ስትደርስ ለአፍሪቃ ዋንጫ ባለቤትነት ስትበቃ ግን ለመጀመሪያ ጊዜ መሆኑ ነው። ሌላዋ የዘንደሮው ውድድር አስደናቂ ተሳታፊ ማሊ ከትናንት በስቲያ ጋናን በለየለት ሁኔታ 2-0 በማሸነፍ ሶሥተኛ ስትወጣ አስተናጋጆቹ ሃገራት ኤኩዋቶሪያል ጊኒና ጋቡንም ጥሩ ጨዋታዎች በማሳየት እስክ ሩብ ፍጻሜው መድረሳቸው እጅግ የሚደነቅ ነው።

የውድድሩን አሸናፊዎች መለስ ብሎ ለማስታወስ ያህል የዘንድሮው የአፍሪቃ ዋንጫ ፍጻሜ 28ኛው ሲሆን ግብጽ ሰባቴ በማሸነፍ ቀደምቷ ናት። ከዚሁ ሌላ ጋናና ካሜሩን እያንዳንዳቸው አራቴ፣ ናይጄሪያና ዛኢር(የዛሬይቱ ዴሞክራቲክ ሬፑብሊክ ኮንጎ)ደግሞ ሁለት ሁለቴ ለድል በቅተዋል። ከዚያም አልጄሪያ፣ ኮንጎ ብራዛቪል፣ ኢትዮጵያ፣ አይቮሪ ኮስት፣ ሞሮኮ፣ ደቡብ አፍሪቃ፣ ሱዳንና ቱኒዚያ የአንዳንድ ጊዜ አሸናፊዎች ናቸው። የሚቀጥለው የአፍሪቃ ዋንጫ ፍጻሜ በመጪው ዓመት ደቡብ አፍሪቃ ውስጥ ይካሄዳል።

አትሌቲክስ

Leichtathletik WM 2011 Daegu Anna Chicherova
ምስል dapd

ባለፈው አርብ ምሽት በዚህ በጀርመን ዱስልዶርፍ ከተማ ውስጥ በተካሄደ ዓለምአቀፍ የአዳራሽ ውስጥ አትሌቲክስ ውድድር አገሬው የአሎሎ ውርወራ የዓለም ሻምፒዮን ዳቪድ ሽቱርል በሶሥተኝነት ተወስኗል። የአንዴው የሶሥት ጊዜ የዓለም ሻምፒየን አሜሪካዊው ክሪስቲያን ካንትዌል አሸናፊ ሲሆን ሁለተኛ የወጣው የፖላንዱ የኦሎምፒክ ባለድል ቶማሽ ማዬቭስኪ ነው።

በአምሥት ሺህ ሜትር ሩጫ ኬንያዊው ቶማስ ሎንጎሢዋ በዓለም ላይ ስድሥተኛውን ፈጣን ጊዜ በማስመዝገብ አሸንፏል። ኒክሰን ቼፕሴባ በ 1500 ሜትር ቀዳሚ ሲሆን ሌላዋ ኬንያዊት የኦሎምፒክ 800 ሜትር አሸናፊ ፓሜላ ጄሊሞ ደግሞ በ 1500 ሁለተኛ ወጥታለች። አንደኛ የወጣችው ገንዘቤ ዲባባ ነበረች። ይሁንና ሁለቱም አትሌቶች ቀድመው ወደ ውስጠኛው መስመር በመግባታቸው ውጤታቸው ዕውቅና አልተሰጠውም።

እዚሁ ጀርመን ውስጥ ትናንት በካርልስሩኸ በተካሄደ ሌላ የአዳራሽ ውስጥ ውድድር በወንዶች 1500 ሜትር ኬንያዊው ቤትዌል ቢርገን ሲያሸንፍ ገ/መድህን መኮንን ሶሥተኛ ሆኗል። በሶሥት ሺህ ሜትርም የኬንያው አውጉስቲን ቾጌ ሲያሸንፍ ሶሥተኛ የወጣው ኢትዮጵያዊው የኔው አላምረው ነበር። በሴቶች 1500 ሜትር ደግሞ ድሉ የገንዘቤ ዲባባ ሲሆን በሶሥት ሺህ ሜትር የሞሮኮ ተውዳዳሪ ማሪየም ሴልሱሊ አንደኛ፤ እንዲሁም መሰለች መልካሙ ሶሥተኛ ወጥታለች።

በጃፓን-ቺባ ትናንት በተካሄደ አገር-አቋራጭ ዓለምአቀፍ ሩጫ ውድድር ደግሞ ሶሥት ኬንያውያን ተከታትለው አሸንፈዋል። 12 ኪሎሜትሩን ርቀት በ 34 ደቂቃ ከ 59 ሤኮንድ ጊዜ በማቋረጥ አንደኛ የወጣው በዚያው በጃፓን ተቀማጭ የሆነው ቻርልስ እንዲራንጉ ነው። በሴቶች ስምንት ኪሎሜትርም ኬንያዊቱ ሱዛን ዋይሪሩ አሸንፋለች። በአሜሪካ ለመጀመሪያ ጊዜ ከዝነኛው ሜዲሰን ስኩዌር ጋርደን ውጭ በተካሄደው 104ኛ የሚልሮዝ አትሌቲክስ ውድድር የኬንያው ተወላጅ አሜሪካዊ ዜጋ በርናርድ ላጋት የአዳራሽ ውስጥ የ 5 ሺህ ሜትር ብሄራዊ ክብረ-ወሰኑን መልሶ ሊያስከብር በቅቷል።

ቡንደስሊጋ/የአውሮፓ ሊጋዎች

Fußball, 1. Bundesliga, Saison 2011/2012, 21. Spieltag, Borussia Dortmund gegen Bayer 04 Leverkusen
ምስል dapd

በስፓኝ ላ-ሊጋ ሬያል ማድሪድ በሻምፒዮንነት አቅጣጫ እየገሰገሰ ነው። ኮከቡ ክሪስቲያኖ ሮናልዶ በዘንድሮው የውድድር ወቅት ለስድሥተኛ ጊዜ በአንድ ግጥሚያ ሶሥት ጎሎችን ሲያስቆጥር ይህም ሬያል በአሥር ነጥቦች ልዩነት እንዲመራ በጅቷል። ሬያል ከ 22 ግጥሚያዎች በኋላ 58 ነጥቦች ሲኖሩት ለዚህ የበቃው ሌቫንቴን 4-2 በማሸነፍ ነው። ባርሤሎና በበኩሉ ግጥሚያ በኦሣሱና 3-2 ሲረታ ከሻምፒዮናው እየራቀ መሄዱን ቀጥሏል። ሶሥተኛው ቫሌንሢያ ነው።

በጀርመን ቡንደስሊጋ ውድድር ሶሥቱም ቀደምት ክለቦች በማሸነፋቸው በአመራሩ ላይ የተለወጠ ነገር የለም። ባየርን ሙንሺን ካይዘርስላውተርንን ማሪዮ ጎሜስና ቶማስ ሙለር ባስቆጠሯቸው ጎሎች 2-0 ሲያሸንፍ ያለፈው ወቅት ሻምፒዮን ዶርትሙንድም ጃፓናዊ ተጫዋቹ ሺንጂ ካጋዋ ባገባት ጎል ሌቨርኩዝንን 1-0 ረትቷል። ግላድባህም እንዲሁ ሻልከን 3-0 ሸኝቷል። ዶርትሙንድ በሁለት ነጥቦች ልዩነት ባየርንን አስከትሎ የሚመራ ሲሆን አሰልጣኙ ዩርገን ክሎፕ ቡድኑን ከልብ ነው ያመሰገነው።

«ከመጀመሪያው አንስቶ በሜዳችን ጥሩ ጨዋታ ነው ያሳየነው፤ ተጋጣሚያችን ጥሩ የመከላከል ችሎታ እንዳለው ሲታስብ። በዚሁ የተነሣ ታዲያ አርባ የጎል ዕድሎች አልታየም። እናም ቡድናችን በትዕግሥት መጠበቁ ሆኖለታል። በመሆኑም በሺንጂ ወርቃማ ጎል በሚገባ ነው የተካሰው»

ሰንብቱ አሁንም እንደገና የክፋ የነበረው ለበርሊኑ ክለብ ለሄርታ ቢስሲ በርሊን ነው። ሄርታ በሽቱትጋርት 5-0 ተንኮታኩቶ ሲወድቅ ይህም በተከታታይ አምሥተኛ ሽንፈቱ ነበር። ይህ ደግሞ የዚያኑ ያህል በስራ ላይ ለቆየው ለክለቡ አዲስ አሰልጣኝ ለሚሻኤል ስኪበ በፍጥነት መባረር ምክንያት ሆኗል።

በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ማንቼስተር ሢቲይ ኤስተን ቪላን 1-0 በመርታት ጎረቤቱን ማንቼስተር ዩናይትድን በሁለት ነጥቦች ልዩነት መምራቱን ቀጥሏል። ማንቼስተር ዩናይትድም በበኩሉ ዌይን ሩኒይ ባስቆጠራቸው ጎሎች ሊቨርፑልን 2-1 ሲያሸንፍ ግጥሚያው እርግጥ አስከፊ ትውስትን ጥሎ ነው ያለፈው። ለዚሁም ምክንያቱ የኡሩጉዋዩ የሊቨርፑል አጥቂ ሉዊስ ሱዋሬስ ቀድሞ በዘረኛነት የዘለፈውን የማኒዩ ተጫዋች የፓትሪስ ኤቭራን ዕጅ አልጨብጥም ማለቱ ነበር።

ሱዋሬስ ከዚህ በፊት ጥፋቱን አምኖ በይፋ ይቅርታ መጠየቁ ሲታወስ የአሁኑን ዕጅ አልጨብጥም ለመሆኑ ምን አመጣው? አስፈላጊ ነገር አልነበረም። ለማንኛውም ቶተንሃም ኒውካስልን 5-0 አሸንፎ በሶሥተኝነቱ ሲቀጥል ቼልሢይ በኤቨርተን 2-0 ተረትቶ አራተኛ ነው። በኢጣሊያ ሴሪያ-አ ኤሲ ሚላን ኡዲኔዘን 2-1 አሸንፎ አመራሩን ሲጨብጥ ጁቬንቱስን በሁለት ነጥቦች ልዩነት ይመራል። እርግጥ ጁቬንቱስ የቦሎኛ ግጥሚያው በበረዶ የተነሣ ከተሸጋሸገ ወዲህ ገና ሁለት ቀሪ ጨዋታዎች ይኖሩታል። ሶሥተኛው ላሢዮ ነው።

በፈረንሣይ አንደኛ ዲቪዚዮን ፓሪስ-ሣንት-ዠርማን ከደካማው ክለብ ከኒስ ጋር 0-0 በመለያየት ሁለት ጠቃሚ ነጥቦችን ቢያጣም ሞንትፔሊየርን በአንዲት ነጥብ አስከትሎ መምራቱን ቀጥሏል። በኔዘርላንድ ሊጋ አይንድሆፈንና አልክማር ቀደምቱ ሲሆኑ በፖርቱጋል ሻምፒዮና ቤንፊካ ሊዝበን አመራሩን እንደያዘ ነው። በግሪክ ሱፐር-ሊጋም ፓናቴናኢኮስ ግንባር-ቀደም እንደሆነ ቀጥሏል።

FC Barcelona Teamfoto
ምስል AP

በተረፈ በአውሮፓ ሻምፒዮና ሊጋ ነገና ክነገ በስቲያ ወደ ሩብ ፍጻሜ ለማለፍ ጠቃሚ የመጀመሪያ ዙር ግጥሚያዎች ይካሄዳሉ። በነገው ምሽት በዚህ በጀርመን ባርሤሎና ከሌቨርኩዝን የሚገጥም ሲሆን የዓለም ድንቅ ተጫዋች ሊዮኔል ሜሢ በአገሪቱ የሰሞኑ የስፖርት አፍቃሪዎች ዓቢይ የውይይት ርዕስ ነው። በምሽቱ ሞስኮ ከሬያል ማድሪድና ናፖሊ ከቼልሢይም ይጋጠማሉ። በማግሥቱ ረቡዕ ደግሞ ኤሲ ሚላን ከአርሰናልና ኦላምፒክ ማርሤይ ከኢንተር ሚላን ዋነኞቹ ናቸው።

መሥፍን መኮንን

ሂሩት መለሰ