1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የዘገየው ፀረ ኤቦላ ርዳታ

ረቡዕ፣ ጥር 20 2007

በኤቦላ ወረርሽኝ አስተላላፊ ተኀዋሲ የሚያዘው ሰው ቁጥር በርግጥ እየቀነሰ መጥቶዋል። ይህ ግን ችግሩ በምዕራብ አፍሪቃ ቀንሶዋል ማለት አይደለም። በመሆኑም፣ የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በሽታውን በመታገሉ አኳያ ከዚሁ አካባቢ ጋር ትብብሩን ማጠናከር ይጠበቅበታል።

https://p.dw.com/p/1ESFi
GAVI Konferenz in Berlin 27.01.2015
ምስል Reuters/F. Bensch

በኤቦላ የተጠቃው ይኸው አካባቢ በዚሁ ሰበብ በኤኮኖሚው ላይ የደረሰበትን ጉዳት ለመቀነስ፣ እንዲሁም፣ ወደፊት ወረርሽኙ ከመከሰቱ በፊት አካባቢው ራሱን ለመከላከል ዝግጁ የሚሆንበትን ሁኔታ ለማመቻቸት የሚያስችለው ለረጅም ጊዜ የሚዘልቅ ርዳታ ያስፈልገዋል።

Ebola Sierra Leone Opfer Kind 12.11.2014 Freetown
ምስል AFP/Getty Images/F. Leong
GAVI Konferenz in Berlin 27.01.2015 Rede Merkel
ምስል Reuters/F. Bensch

በአዳጊ ሀገራት የሚገኙት ሕፃናት ጤንነት በተሻለ ዘዴ ለመጠበቅ የሚያስችሉ ክትባቶች ምርት ከፍ እንዲል ዘመቻ የጀመረው በምሕፃሩ ጋቪ በመባል የሚታወቀው ዓለም አቀፍ ህብረት ትናንት በበርሊን ካሄደው ጉባዔ የተሳካ ውጤት እንዳስገኘለት ተገለጸ። በጉባዔው የተሳተፉት ሀገራት እና ከ15 ዓመት በፊት በዳቦስ፣ ስዊትዘርላንድ ቋቋመው ህብረት ዓላማ ማሳኪያ በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት 7,5 ቢልዮን ዩኤስ ዶላር ርዳታ ለመስጠት ቃል ገብተውለታል። ጀርመንም በዚሁ ጊዜ ለህብረቱ 600 ሚልዮን ዩሮ እንደምትሰጥ አስታውቃለች። ለክትባቱ ርዳታ ለመስጠት በወቅቱ የታየው ይህ ዓይነቱ ተነሳሽነት ግንበኤቦላ ወረርሽኝ አስተላላፊ ተኀዋሲ የሚያዘው ሰው ቁጥር እየቀነሰ በሄደባት ምዕራብ አፍሪቃ አኳያ እጅግ እንደዘገየ ነው የተነገረው። ሁኔታውን ወደ ሲየራ ልዮን በመሄድ በቅርብ የተከታተሉት ድንበር የማይገድበው የሀኪሞች ድርጅት፣ የጀርመን ቅርንጫፍ የቀድሞ ዋና ስራ አስኪያጅ ሀኪም ፍራንክ ደርነር እንዳስረዱት፣ የርዳታው መዘግየት ክትባቱን የመሞከሩን ሂደት አዳጋች አድርጎታል።

« ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በኤቦላ ወረርሽኝ አኳያ ተገቢውን ምላሽ እስኪሰጥ ድረስ ብዙ ጊዜ ነበር የወሰደበት። ይህ በፖለቲካው ዘርፍ በታየው ቸልተኝነት ሰበብ ብቻ ሳይሆን፣ ይህን የመሰለ ወረርሽኝን ለመታገል የሚያስፈልገው ተሞክሮ ያለው የሰው ኃይል ተጓድሎም በመገኘቱ ጭምር ነው። »

ከዚህ በተጨማሪ እንደ ፍራንክ ደርነር ገለጻ፣ ወረርሽኙ የተከሰተባቸው የጊኒ፣ ላይቤሪያ እና ሲየራ ልዮን ደካማ መሠረተ ልማትም ሌላ እክል የደቀነ ሌላ ችግር ነው።

« ግልጽ መሆን ያለበት ጉዳይ የምንናገረው በዓለም እጅግ ችላ ስለተባሉ እና ረጅም የርስ በርስ ጦርነት ስለተካሄደባቸው ሀገራት የጤና ጥበቃ አውታር ነው። የነዚህ ሀገራት የጤና ጥበቃ አውታር ገና የኤቦላ ወረርሽኝ ከመከሰቱ በፊትም በጣም የተዳከመ ነው። እንዲያውም፣ ወረርሽኙ የሶስቱን ሀገራት የጤና ጥበቃ አውታር ይበልጡን ጎድቶታል፣ የሌለ ያህል ይቆጠራል ለማለት ይቻላል። »

Kenia leerer Strand 2005
ምስል AP

በዓለም አቀፍ የጤና ጥበቃ ድርጅት ዘገባ መሠረት፣ በወረርሽኙ አስተላላፊ ተኀዋሲ እስካሁን 8,700 ሰዎች ሞተዋል። 22,000 ደግሞ በተኀዋሲው ሳይያዙ አልቀሩም ተብለው ተጠርጥረዋል። ወረርሽኙ በሀገራቱ የግብርና ዘርፍ እና በኤኮኖሚ ላይ ከፍተኛ ጉዳት ማድረሱን የዓለም ባንክ የምዕራብ አፍሪቃ ጉዳይ ተከታታይ ቬራ ሶንግዌ አስታውቀዋል።

Ebola Schnelltest Firma Senova
ምስል Senova

« ከጠቅላላ ምርታቸው ወደ ሁለት ከመቶ የሚጠጋው ቀንሶዋል። የዋጋ ግሽበቱ እስከ ሶስት፣ አራት ከመቶ ከፍ ብሎዋል። በላይቤሪያ የማዕድን ዘርፍ 20,000 ሰው ስራውን አጥቶዋል። ተቋማት እየዘጉ ነው። በኤቦላ ያልተጎዱ ጋምቢያን የመሳሰሉ ሀገራት እንኳን የቱሪስቱ ቁጥር ከ40 እስከ 60 ከመቶ ቀንሶዋል። ይህ ትልቅ ክስረት ነው። የኤቦላ ተፅዕኖ ደቡብ አፍሪቃን እና ኬንያንም እንደነካ ተመልክተናል።

ሁኔታዎች እስኪሻሻሉ ድረስ ገና ብዙ ወራት እንደሚያስፈልግ የዓለም ጤና ጥበቃ ድርጅት ፕሬዚደንት ማርግሬት ቻንግ በመግለፅ ወደፊት ኤቦላን የመሳሰሉ ወረርሽኞችን በተሻለ መንገድ ለመቋቋም ሀገራት ትብብራቸውን ማጠናከር እንደሚኖርባቸው አሳስበዋል፣ ይህ ብቻውን በቂ እንዳልሆነ የገለጹት ፍራንክ ደርነር በወረርሽኙ በሚጠቁ ሀገራት ውስጥ በሚገባ የሚሰራ የተጠናከረ፣ በቂ ተሞክሮ ያላቸው ባለሙያዎች የሚያጠቃልል የጤና ጥበቃ አውታር ሊኖር እንደሚገባ አስታውቀዋል። የዓለም ባንክ ባልደረባ ቬራ ሶንግዌ ደግሞ በወረርሽኙ የተጠቁት የምዕራብ አፍሪቃ ሀገራት ስር ነቀል መዋቅራዊ ለውጥ ማድረግ እንደሚኖርባቸው ነው ያመለከቱት።

ፊሊፕ ዛንድነር/አርያም ተክሌ

ነጋሽ መሀመድ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ