1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የዘመነ-ቃዛፊ ፍፃሜ

ሰኞ፣ ነሐሴ 16 2003

ሐያሉ ዓለም ካደመባቸዉ ከረመ።አምስት ወር ግድም።ጊዜ ሲዘም በላይ በላዩ ነዉ።ታማኝ ባለሥልጣኖቻቸዉም ከዷቸዉ።ልጃቸዉ ምናልባትም ለአልጋ ወራሽነት ያጩት ዉድ ልጃቸዉ ተማረከ።ሠይፍ አል-ኢስላም።

https://p.dw.com/p/RhOH
ትሪፖሊምስል picture-alliance/dpa

«ሁሉም ጎሳ በሙሉ ትሪፖሊን ከጥቃት ለመከላከልና ለማፅዳት አሁኑ ወደ ከተማይቱ መዝመት አለባችሁ።አለበለዚያ ዋጋም የላቸሁ።የኢምፔሪያሊስት ባሪያና አገልጋይ ሆናችሁ ትቀራላችሁ።»

ኮሎኔል ሙዓመር ቃዛፊ።ትናንት።እርግጥ ነዉ አሁንም አንደበታቸዉ ይፎክራል።የአርባ ሁለት ዘመን ክንዳቸዉ ግን ዝሏል።ሕልቅታቸዉ ተፈጥርቋል።የቃዛፊ ፍፃሜ፥ ለፍፃሜያቸዉ የተከፈለዉ ዋጋና ምክንያቱ ያፍታ ቅኝታችን ትኩረት ነዉ።አብራችሁኝ ቆዩ።

ሐያሉ ዓለም ካደመባቸዉ ከረመ።አምስት ወር ግድም።ጊዜ ሲዘም በላይ በላዩ ነዉ።ታማኝ ባለሥልጣኖቻቸዉም ከዷቸዉ።ልጃቸዉ ምናልባትም ለአልጋ ወራሽነት ያጩት ዉድ ልጃቸዉ ተማረከ።ሠይፍ አል-ኢስላምም።ቃዛፊ ግን ትናንትም አለሁ ባይ ናቸዉ።ጠላቶቻቸዉን ያወግዛሉ።

«እዚሕ ነኝ።እመሐላችሁ ነኝ።ትሪፖሊ ዉስጥ ነኝ።ትሪፖሊ ትጋያለች።ዉሐና ኤሌክትሪክ አይኖርም።ኑሯቸዉ የመከራ ነዉ የሚሆን።ይገድሏችኋል።ሊቢያ ጋየች አልጋየች እነዚሕ ሰዎች ደንታም የላቸዉ።»

እንደ እዉነቱ ከሆነ ግን አሁን የቀራቸዉ ባብ አል-አዚዚያ ብቻ ነዉ።ከዚያ መንደራቸዉ የሚናገሩትን የሚፈፅም የሚታዘዛችዉ ቀርቶ የሚሰማቸዉም የለም።ትሪፖሊ በርግጥ እየነደደች ነዉ።የከተማይቱ ነዋሪ ግን በቃዛፊ ፍፃሜ ይፈነጥዛል።«ሕዝቡ እየፈነደቀ ነዉ።በየአካባቢዉ ባንዲራ እያዉለበለበ፥ እየጮኸ እየተደሰተ ነዉ።በነፃነት መተንፈሥ እንችላል።በነፃነት መናገር እንችላለን።እንደከዚሕ ቀደሙ የሚሰማንን ከመናገር ማንም አያግደንም።»

በ1969 (ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎሮጎሮሳዉያኑ አቆጣጠር ነዉ) የያኔዉ ሻለቃ ሙዓመር ቃዛፊ የመሯቸዉ የጦር መኮንኖች የንጉስ ኢድሪስን ዙፋናዊ አገዛዝ ሲያስወግዱ የዚያ ዘመኑ ሊቢያዊ ልክ እንዳሁኑ ትዉልድ በንጉሱ ዉድቀት ፌስታ ፈንድቆ ነበር።ልክ እንደዛሬዉ ትዉልድ በነፃነት የመናገር፥ የመንቀሳቀስ ሰብአዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶችን ተመኝቶ ተስፋ-አድርጎ ተስፋ ተሰጥቶም ነበር።ሁሉም ግን በነበር ቀረ።

አዲሱ ትዉልድ በድሕረ-ቃዛፊ አገዛዝ የተመኘዉ በነፃነት የመናገር፥ የመንቀሳቀስ ፍላጎት ምኞት ተስፋዉ እዉን መሆን አለመሆኑ አሁን ማወቅ-አለማወቅም አይቻልም።የሊቢያ ሕዝብ በአርባ ሁለተኛ አመቱም የቀዳሚዎቹን ምኞት ተስፋ መድገሙ ግን በርግጥ ሐቅ፥ ሐቁ-አደናጋሪ አነጋጋሪም ነዉ።

የንጉስ ኢድሪስ ዙፋን በተገረሰሰበት ወቅት ሥልጣን ያዢዎችም፥ ከሥ’ልጣን ተባባራሪዎችም ሊቢያዉያን ነበሩ።የቃዛፊን አገዛዝ የደገፉ-የተቃዋሙት፥ ለቃዛፊ ዉድቀት የተዋጉት ግን ሊቢያዉያን ብቻ አይደሉም፣- የዓለም ሐያላን ጭምር እንጂ።ምክንያቱ ከፈረንሳዩ ፕሬዝዳት ኒካላይ ሳርኮዚ-እስከ ብሪታንያዉ ጠቅላይ ሚንስትር ዴቪድ ካሜሩን፥ ከዩናይትድ ስቴትሱ ፕሬዝዳት ባራክ ኦባማ እስከ ኢጣሊያዉ ጠቅላይ ሚንስትር ሲልቪዮ ቤርሎስኮኒ ያሉ የአለም ሐያል ሐብታም ሐገራት መሪዎች በተደጋጋሚ እንዳሉት የሊቢያን ሕዝብ ከቃዛፊ ጥቃት መከላከል ነዉ።

Bürgerkrieg in Libyen Erfolg der Rebellen ARCHIV
በቃምስል dapd

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታዉ ጥበቃ ምክር ቤት ባሳለፈዉ ዉሳኔ መሠረት የኮሎኔል ሙዓመር ቃዛፊ መንግሥትን ጦር መደብደብ የጀመሩት የእነዚሕን ሐገራት ጦር ተክቶ ሊቢያን የሚደበድበዉ የሰሜን አትላንቲክ የጋራ መከላከያ ጦር ቃል ኪዳን ድርጅት ኔቶ ባለሥልጣናት በተደጋጋሚ እንዳሉትም የድብደባዉ አላማ የሊቢያን ሕዝብ ከቃዛፊ ጦር ጥቃት መከላከል ነዉ።

በኔቶ ጦር የአየርና የሚሳዬል ድብደባ የሚታገዙት የሊቢያ አማፂ ሐይላት የርዕሥ-ከተማ ትሪፖሊን አብዛኛ አካባቢዎች መቆጣጠራቸዉ እንደተነገረ ትናንት የኔቶ ጦር ቃል አቀባይ ኦና ሉንጌስኩ የቃዛፊ ስርዓት እየተንኮታኮተ ነዉ አሉ።

«እንደሚመስለኝ ዛሬ ማታ የምናየዉ የሥርዓቱን መንኮታኮት ነዉ።ኮሎኔል ቃዛፊ እራሳቸዉ በጀመሩት ጦርነት ሕዝባቸዉን ማሸነፍ የሚችሉበት መንገድ እንደሌለ ፈጥነዉ ቢገነዘቡ ለሁሉም የተሻለ ነዉ።ይሕ ከሆነ የሊቢያ ሕዝብ ወደሚፈልገዉና ወደሚገባዉ ዲሞክራሲ መሸጋገር ይችላል።ሽግግሩን ሳይዘገዩ ፈጥነዉ ሊጀምሩት ይችላሉ።»

የሊቢያ ሕዝብ ከቱኒዝያና ከግብፅ ጎረቤቶቹ ተምሮ በአርባ ሁለት ዘመን ገዢዉ ላይ የጀመረዉን የአደባባይ ሕዝባዊ አመፅ ወደ ነፍጥ ዉጊያ የቀየረዉን ወገን ማንነት የሐያሉ የጦር ድርጅት ቃል አቀባይ አንድም ዘንግተዉታል፥ ሁለትም ሆን ብለዉ አጣመዉታል።ያም ሆኖ ቃል አቀባይዋ እንዳሉት የቃዛፊ ሥርዓት አብቅቶለታል።የቃዛፊ ሥርዓት አብቆቶለታል ማለት ደግሞ የቃዛፊ ጦር በሊቢያ ሕዝብ ላይ የሚያደርሰዉ ጥቃት የለም ማለት ነዉ።

የቃዛፊ ጦር በሕዝብ ላይ የሚያደርሰዉ ጥቃት ከሌለ «ሠላማዊ ሕዝብ ለመከላከል» ያለመዉ የኔቶ ተልዕኮ አበቃ ማለት ነዉ።የብሪታንያዉ ጠቅላይ ሚንስትር ዴቪድ ካሜሩን ግን በኔቶ ቃል አቀባይ መግለጫ ምናልባት በአመክንዮዉ አይስማሙም።

«የኔቶ ሰፊ ተልዕኮ፥ ማለት ሰላማዊ ሠዎችን ከጥቃት የመካላከሉ ተልዕኮ አስፈላጊ እስከሆነ ድረስ ይቀጥላል።»

የቃዛፊን ወንበር ለመረከብ ሰዓታት፥ ቢበዛ ዕለታት የሚቆጥሩት የሊቢያ ብሔራዊ የሽግግር ምክር ቤት ሊቀመንበር ሙስጠፋ አብዱል ጀሊል ከዋናኛ ደጋፊያቸዉ ከካሜሩን አባባል ጋር ይቃረናሉ።አቡድልጀሊል እንደሚሉት ቡድናቸዉ የቃዛፊን ሐይል ድል ካደረገ የኔቶም ተልዕኮ አበቃ።

«የኔቶ ሐላፊነት ሕዝቡን ከጥቃት መከላከል ነዉ።ቃዛፊ ተወግደዉ እኛ ሥልጣን ሥንይዝ የኔቶ ተልኮም ያበቃል።»

የቃዛፊ ፍፃሜ እንዴትነት በቅጡ ሳይለይ ገና ካሁኑ ለቃዛፊ ፍፃሜ በንድነት የሠሩ፥ ጦራቸዉን ያዘመቱ ያዋጉት ሐይላት ካንድነታቸዉ ይልቅ ልዩነታቸዉ መታየቱ የመሠረታዊ ዓላማ ፍላጎታቸዉ እንዴትነት ዳግም አጠያያቂ አድርጎታል።በፓሪሶች ጎትጓችነት፥ በለንደን፥ ዋሽንግተኖች አበረታችነት የዓለም ሐያላን ሊቢያን የሚደበድብ ጦር ለማዝመት ሲወስኑ ብዙዎች በጣሙን የሰወስተኛዉ ዓለም ታዛቢዎች ብዙ ጠይቀዉ ነበር።

የጥያቄዉ መሠረት የአለም አድራጊ ፈጣሪዎች በየፈላጭ ቆራጭ ገዢዎቹ ለዘመናት የሚማቅቀዉ የሚሊዮነ-ሚሊዮናት አፍሪቃዊ ሕዝብን መከራ ለማስወገድ ለዲፕሎማሲዉ ወግ እንኳን ቃላት ለመተንፈስ የሚያቅማሙት ሐያላን ለሊቢያ ሕዝብ ጦር የማዝመታቸዉ ሰበብ ከእዉነተኛ ምክንያት መቃረኑ ነበር።የባሕሬን ሕዝባዊ አመፅ በነ-ሳዑዲ አረቢያ ጦር መደፍለቁን የደገፉት፥የየመን ሕዝብን ያደባባይ ጩኸት የዘነጉት፥ የፍልስጤሞችን የዝንተ-ዓለም የነፃነት ጥያቄ ያዳፈኑት፥ የሚሊዮን አፍሪቃዉያንን የዲሞክራሲ ጥያቄ እንዳልሰሙ ያለፉት ለሊቢያ ሕዝብ ያን ያሕል የመነጨነቅ መጠበባቸዉ በርግጥ አጠያያቂ ነበር-ነዉም።

Flash-Galerie Libyen Tripolis unter Kontrolle der Aufständischen Freude in Bengasi
ፌስታምስል dapd

ጀርመናዊዉ የሊቢያ ጉዳይ አዋቂ አልፍሬድ ሐከንስበርገር እንደሚሉት ግን የሐያሉ ዓለም ትክክለኛ ዓላማና ፍላጎት ብዙ ምርምር የሚጠይቅ አይደለም።አንድና ግልፅ ነዉ።ነዳጅ።

«የኔቶ አባል ሐገራት ሊቢያ ዉስጥ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ለመመሥረት በበጎ ፍቃደኝነት አልተነሳሱም።ለጥቅማቸዉ ሲሉ ነዉ።ለነዳጅ ሐብት እና አካባቢዉን በበላይነት ለመቆጣጠር።ያም ሆኖ ዋነኛዋ ተጠቃሚዋ ምናልባት ለአማፂያኑ ዙሪያ መለስ ድጋፍ የሰጠችዉ ቀጠር ሳትሆን አትቀርም። አማፂያኑም እንደተናገሩት እነሱን የረዳ ወደፊት በሚደረገዉ የነዳጅ ሽያጭ ዉል ቅድሚያ ያገኛል።»

ኮሎኔል ሙዓመር ቃዛፊ በመሩት መፈንቅለ መንግሥት የጠፋ ሕይወት አልነበረም።በአርባ ሁለት ዘመነ-ሥልጣናቸዉ ብዙ ተቀናቃኞቻቸዉን ማጥፋታቸዉ ይነገራል።የቃዛፊ ሥርዓት ለማጥፋት ባለፉት ስድስት ወራት በተደረገዉ ጦርነት ግን ሃያ-አምስት ሺሕ ሕዝብ አልቋል።ከሰባት ሺሕ በላይ ቆስሏል።አምስት ሺሕ የደረሰበት አይታወቅም።ኔቶ ካለፈዉ መጋቢት አጋማሽ ጀምሮ ሊቢያን ስድስት ሺሕ ጊዜ ደብድቧል።ብቻ የቃዛፊ---ሥርዓት እየተቆራረሰ ወደ መቃርብር-ይጓዝ ይዛል።ሲያልቅ አያምር።
ነጋሽ መሐመድ

አርያም ተክሌ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ