1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

57.9 በመቶ የጦር መሣሪያ ንግድ የተካሄደው በአሜሪካን ኩባንያዎች ነው።

ሰኞ፣ ታኅሣሥ 2 2010

በዓለም ዙሪያ የጦር መሣሪያ ንግድ እያደገ ነው። መቀመጫውን ስቶክሆልም ስዊድን ያደረገው ዓለም አቀፍ የሰላም ምርምር ተቋም በምህፃሩ SIPRI ያወጣው ዘገባ እንደሚያሳየው የንግዱ ዋነኛ ተጠቃሚዎች በዩናይትድ ስቴትስ እና በምዕራብ አውሮጳ የሚገኙ የጦር መሣሪያ አምራች ኩባንያዎች ናቸው።

https://p.dw.com/p/2p9vC
Jemen Panzer
ምስል Getty Images/AFP/S. Al-Obeidi

ከጦር መሣሪያ ንግድ 57.9 በመቶው በአሜሪካን ኩባንያዎች ነው የሚካሄደው።


የጥይቶች ፣ ታንኮች እና ሰው አልባ የጦር አይሮፕላኖች(ድሮኖች) በአጠቃላይ የጦር እና ለወታደራዊ አገልግሎት ጥቅም ላይ የሚውሉ መሣሪያዎች ንግድ ከ5 ዓመታት ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ በጎርጎሮሳዊው 2016 እንደገና አድጓል ። ንግዱ ከቀደመው ከ2015 የ1.9 በመቶ ከ2002 ጋር ሲነጻፀር ደግሞ የ38 በመቶ እድገት አሳይቷል። የስቶክሆልም ዓለም አቀፉ የሰላም ምርምር ተቋም የሲፕሪ አዲሱ የዓለም የጦር መሣሪያ ኢንዱስትሪ ዘገባ እንደሚለው በ2016፣ የዓለማችን 100 ትላልቅ የጦር መሣሪያ አምራች ኩባንያዎች ከጦር መሣሪያ፣ ከጦር መሣሪያ መለዋወጫ እና ከወታደራዊ  አገልግሎት ቁሳቁሶች ሽያጭ 374.8 ቢሊዮን ዶላር አግኝተዋል። በተለይ የዩናይትድ ስቴትስ ኩባንያዎች የጦር መሣሪያ ምርትም ሽያጭም ጨምሯል። እንደ ሲፕሪ ዘገባ በዓመቱ የአሜሪካን ኩባንያዎች ሽያጭ በአራት ከመቶ ጨምሮ በአጠቃላይ ወደ 217.2 ቢሊዮን አድጓል። ይህ የሆነው ግን በአሜሪካን ወታደሮች የውጭ ስምሪት ምክንያት ብቻ ሳይሆን ሌሎች ሀገራትም ብዙ የጦር መሣሪያ አገልግሎት ቁሳቁሶችን በመሸመታቸው ነው እንደ ጥናቱ። የዓለማችን ትልቁ የጦር መሣሪያ አምራች የዩናይትድ ስቴትሱ ኩባንያ «ሎክሂድ ማርቲን» F-35 የተባሉትን የጦር አውሮጵላኖቹን እንደ ብሪታንያ ጣልያን ወይም ኖርዌይ ለመሳሰሉ ሀገራት በመሸጥ ብዙ ገንዘብ ዝቆበታል። ዋነኛ ደምበኛው ግን የዩናይትድ ስቴትስ አየር ኃይል ነው።  የሲፕሪ ጥናት በግልጽ እንደሚያሳየው ከአጠቃላዩ የዓለም የጦር መሣሪያ ንግድ 57.9 በመቶው በአሜሪካን ኩባንያዎች የተካሄደ ነው። በዚህ ንግድ የምዕራብ አውሮጳ ሀገራት ሁለተኛውን ቦታ ሲይዙ ሩስያ ደግሞ በ7.1 በመቶ ሦስተኛው ደረጃ ላይ ትገኛለች። ከአውሮጳ የኢጣልያ እና የ ፈረንሳይ ኩባንያዎች የጦር መሣሪያ ንግድ ዝቅተኛ ሲሆን ትልቁን ድርሻ የሚይዙት ብሪታንያ እና ጀርመን ናቸው። ለምሳሌ የጀርመኖቹ የታንክ አምራች ኩባንያዎች ክራውስ ማፌይ እና ራይንሜታል በ2016 ንግዳቸው ከተኮሰው ኩባንያዎች መካከል ተጠቃሾች ናቸው። ኦድ ፍለሮን በሲፕሪ የጦር መሣሪያዎች እና የወታደራዊ ወጭዎች መርሃ ግብር ሃላፊ ናቸው። በርሳቸው አስተያየት የጦር መሣሪያ ንግድ እድገትን አሁን ካሉት ጦርነቶች ጋር በቀጥታ ማያያዙ ይከብዳል። 
« ጦር መሣሪያዎች በብዛት መሸጣቸውን አሁን ከሚካሄዱት ጦርነቶች ጋር በቀጥታ ማገናኘቱ አስቸጋሪ ነው። በእርግጥ ጦርነቶች ሲካሄዱ በሁለቱ መካከል ትስስር ይኖራል። የተወሰኑ ዓይነት መሣሪያዎች ይበልጥ ተፈላጊ ሲሆኑ ይታያል፤ እንደ ሚሳይሎች ጥይቶች የመሳሰሉት። ለምሳሌ በመካከለኛው ምሥራቅ ስጋቱ አይሏል በምሥራቅ እና በሰሜን ምስራቅ እስያም ከፍተኛ ውጥረት አለ። ይህ ደግሞ ከጥቂት ጊዜያት ወዲህ የሚካሄድ ነው።»
ደቡብ ኮሪያ ለዚህ አንድ ምሳሌ ናት። በ2016 የደቡብ ኮሪያ ኩባንያዎች የጦር መሣሪያ ንግድ በ20.6 በመቶ ከፍ ማለቱን ዘግበው ነበር። ፍለሮን ደቡብ ኮሪያ በጎረቤትዋ በሰሜን ኮሪያ የኒዩክልየር ትንኮሳ ምንክያት ከፍተኛ ስጋት እንዳደረባት ይህም ወታደራዊ ወጪዋ እንዲጨምር ምክንያት መሆኑን ያስረዳሉ። በዚህ ንግድም የሀገሪቱ የጦር መሣሪያ አምራች ኩባንያዎች ተጠቃሚ ሆነዋል እንደ ፍለሮን። 
« የደቡብ ኮሪያ ኩባንያዎች ንግድ በከፍተኛ ደረጃ አድጓል። ይህ የሆነው ሀገሪቱ በምትገኝበት የፀጥታ ሁኔታ ምክንያት መሆኑ ግልጽ ነው። በዓለም አቀፉ ገበያም በንቃት እየተሳተፉ ነው። በአመዛኙ የጦር መሣሪያዎቻቸውን የሚያቀርቡት ወታደራዊ ወጭው በጣም ለጨመረው የደቡብ ኮሪያ የመከላከያ ሚኒስቴር ነው።»
የሲፕሪ ተመራማሪዎች ቻይናም ከዓለም ዋነኛ የጦር መሣሪያ አምራቾች አንድዋ ልትሆን ትችላለች የሚል እምነት አላቸው። ሆኖም ስለቻይና አስተማማኝ መረጃ ስላላገኙ አሀዛዊ መዘርዝሩ ውስጥ አላካተቱዋትም። በሌላ በኩል የሲፕሪ ዘገባ እንዳሳየው፣  የጦር መሣሪያ በመሸመት የሚታወቁት በርካታ የአፍሪቃ እና የደቡብ አሜሪካ ሀገራት በነዳጅ ዘይት ዋጋ መቀነስ ሰበብ ገንዘብ ስላነሳቸው በ2016 ብዙ መሣሪያ መግዛት አልቻሉም።

Israel trainiert Bundeswehr für Afghanistan
ምስል picture alliance / dpa
Symbolbild Deutschland Waffenexporte
ምስል Getty Images
Infografik Share of global arms sales 2016 ENG

ኂሩት መለሰ

አርያም ተክሌ