1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የዓለም ኤኮኖሚ በ2003

ሐሙስ፣ ጥር 6 1996

ዩኤስ-አሜሪካ የኤኮኖሚ ግስጋሴው መሪ እየሆነች፣ እስያም የዕድገቱን መስመር እየተከተለች ስትገኝ፣ ያውሮጳው አካባቢ ግን የዝግመቱን ሂደት ማነቃቃት ተስኖት፣ በድህነት የተያዘው አዳጊው ዓለም ደግሞ የተሥፋው ውጋጋን ደብዞበት ነበር የታየው። ይህ ኤኮኖሚያዊ ገጽታ ነበር አሁን የተፈፀመው ጎርጎራዊው ዓመት 2003 የተንፀባረቀበት። በዛሬው ዝግጅታችን የዓለም ኤኮኖሚ ሂደት በ2003 እንዴት እንደነበር ነው መለስ ብለን የምንመለከተው፤ መልእክቱ የሚያካትታቸው፥ ሁ

https://p.dw.com/p/E0g3

��ት ከፊሎች ሲሆኑ፣ ዛሬ መጀመሪያው ነው የሚቀርበው።


ያሜሪካው ኤኮኖሚ መሪውን ሚና የሚይዝ እንደመሆኑ መጠን፣ እዚያ የሚደረገው ሁሉ በዓለም ኤኮኖሚ ላይ ተጽእኖ ያሳርፋል። “ዎል ስትሪት ሲያስነጥሰው የዓለም አክሲዮን ገበያዎች ያስላቸዋል” ይባላል--ይህም በ2003 መጀመሪያ ላይ እውን ሆኖ ነበር የተገኘው። ይኸውም፥ ፕሬዚደንት ጆርጅ ቡሽ በዚያው ወቅት ኢራቅን አስመልክተው ንግግር ካሰሙ በኋላ ስለ ኢራቁ ጦርነት አዝማሚያ የተፈጠረው አዲስ ሥጋት የአክሲዮኖች ዋጋ ከቶኪዮ እስከ ፍራን’ክፉርትና እስክ ኒውዮርክ ወደ ቁልቁለቱ መስመር እንዲያዘንብል ነበር ያደረገው። እንዲያውም፣ በቶኪዮ የአክሲዮን ገበያው መለኪያ ኒኬ-ኢንደክስ ከሃያ ዓመታት ወዲህ ታይቶ ወዳልታወቀ እጅግ ዝቅተኛ ደረጃ ተሽቆልቁሎ ነበር የተገኘው። በፍራንክፉርት ደግሞ፣ የአክሲዮን ገበያው መለኪያ “ዳክስ” ከሰባት ዓመታት ወዲህ እጅግ አነስተኛ ወደሆነው አሃዝ ነበር ያሽቆለቆለው። የኤኮኖሚው ግስጋሴ ሞተር ሆኖ የሚታየው ያሜሪካው ኤኮኖሚ ጉልህ ዕድገት ቢንፀባረቅበትም፣ የጦርነት ሥጋት አጥልቶበትም ነበር የታየው። በደካማው ዶላር፣ በከፍተኛው ሥራአጥነትና በመጣቂው የመንግሥት በጀት ጉድለት አንፃር ፕሬዚደንት ቡሽ የታያቸው መፍትሔ፥ ሰፊ አድማስ ያለውን የቀረጥ ቅናሽ የተመለከተ ነበር። “ይህ የቀረጥ ቅናሽ ለመላው የገቢ ቀረጥ ከፋዮች የሚበጅ ነው፣ ኤኮኖሚያችንንም እንደገና አፋጥኖ ለማንቀሳቀስ የሚረዳ ነው” ነበር ያሉት ፕሬዚደንት ቡሽ።

ግን፣ የኤኮኖሚ ሂደቱ ፍጥነት የተፈለገውን ያህል ሆኖ አልነበረም የተገኘው። ሊፈነዳ ተቃርቦ የነበረው የኢራቁ ጦርነት የደቀነው ሥጋት ወረት-አዋዮችንም ሆነ ሸማቾችን አደናገረ፣ በሚያዝያ ከተከናወነው ወታደራዊ ቅጽበት-ድል በኋላም ገበያው መነቃቃት እንደተሳነው ነበር የተገኘው፤ በተለይም በጦርነቱ ወጭ ምክንያት ያሜሪካው መንግሥታዊ በጀት ጉድለት ወደ ፬፻፷ ሚሊያርድ ዶላር ነበር የመጠቀው። ከዚሁ የበጀት ጉድለት ጎንለጎን፣ የሥራ አጦችም አሃዝ ነበር አብሮ ያሻቀበው። ፕሬዚደንት ቡሽ ያገኙት ወታደራዊው ድል ራሱ ለሥራ ቦታዎች ፈጠራ ያልበጃቸው መሆኑን ያስገነዘቡት ተቃዋሚዎቻቸው የቪዴዎም ዘመቻ ነበር ያካሄዱባቸው።

ይሁን እንጂ፣ በዓመቱ ፫ኛ ሩብ ላይ የኤኮኖሚው ግስጋሴ የተተካበት ሁኔታ እጅግ ድንገተኛ ሆኖ ነበር የተገኘው። ያሜሪካው ጠቅላላ ብሔራዊ ውጤት ዕድገት ከስምንት በመቶ በልጦ ለተገኘበት ሁኔታ በተለይ ከኢራቁ ጦርነት ጋር የተያያዘው ተጨማሪው የመንግሥት ወጭ ነበር ተጠያቂ የሆነው። ከኢራቁ ጦርነትና መልሶ ግንባታ ጋር የተያያው ፩፻፶ ሚሊያርድ ዶላር ተጨማሪ የመንግሥት ወጭ ለአሜሪካ እንዱስትሪ-ኩባንያዎች ብዙ አዳዲስ የሥራ ኮንትራቶችን አስገኘ፣ ይህና የቀረጡ ቅናሽ ተጨማምረው ለአሜሪካው ኤኮኖሚ ጨርሶ ያልታሰበውንና ያልተጠበቀውን እመርታ እውን አደረጉት። ከዚህም በላይ፣ የዶላር ድክመት ለኤክስፖርቱ ገበያ ጠቃሚ ሆኖ ተገኘ።

ግን፣ በሥራ ቦታዎች ፈጠራ ረገድ ተመሳሳይ አዎንታዊ ውጤት ሳይገኝ ቀረ። ሆኖም፣ ያመቱ ፍፃሜ በተቃረበበት በወርሃ ጥቅምት በሥራ ቦታዎችም ረገድ አነቃቂው ሁኔታ ታየ። ይኸውም፣ ከረዥም ጊዜ ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ ያሜሪካው ኤኮኖሚ አንድ-መቶ-ሺህ አዳዲስ የሥራ ቦታዎችን ለመፍጠር መብቃቱና የሥራ አጦችም ይዘት በስድስት በመቶ ዙሪያ ተገድቦ ሊቆይ መቻሉ ነው። ግን አሜሪካ ውስጥ በበጀት ጉድለት ድርርብ የተገኘው ኤኮኖሚያዊ ግስጋሴና የዶላር ተመን ውድቀት አደጋንም የሚደቅን ይሆናል። የዶላር ድክመት የኦይሮን ጥንካሬ እንደሚያስከትል የተገነዘቡት የኤኮኖሚ ጠበብት፣ በአሜሪካ አለቅጥ ከፍተኛው የመንግሥት በጀትና የንግድ ሚዛን ጉድለት የቀውስ ምንጭ እንደሚሆን በሥጋት ሲያሰላስሉት ነበር የቆዩት።

ጀርመን ውስጥ ጠቅላላውን የኤኮኖሚ ሁኔታ እየተከታተለ ዓመታዊ ጥናት የሚያቀርበውና አምስት አባላት የሚገኙበት የጠቢባን ቡድን ተጣማሪ የሆኑት ፕሮፌሰር አክሰል ቬበር የዶላርን ድክመትና የኦይሮን ጥንካሬ ሂደት አትኩረው በመመልከት እንዳስረዱት፣ የኦይሮ ተመን ለምሳሌ አሥር በመቶ ቢወጣጣ፣ የኤኮኖሚ ዕድገቱን ሂደት ነጥብ-ሁለት በመቶ የሚቀንሰውና በቀጣዩም ዓመት ይኸው የዕድገት ቅናሽ የሚደገም ይሆናል። ይኸው ስሌት በጀርመኑ ማዕከላይ ባንክ አሠራር ላይ የተመሠረተ ነው። የኦይሮ ተመን አለቅጥ እየተወጣጣ ከተገኘና የዶላርም ድክመት ከቀጠለ፣ ለምሳሌ ጀርመን ውስጥ የኤኮኖሚ እክል ሊሆን እንደሚችልም ነው ፕሮፌሰሩ ያስገነዘቡት። ሁኔታው በተለይም የኤክስፖርቱን ዘርፍ ነው ለጉዳት የሚያጋልጠው ሆኖ የሚታየው።

እንግዲህ፣ ዩኤስ-አሜሪካ ውስጥ አምስት በመቶ የደረሰው ዓይነቱ ከፍተኛ የመንግሥት በጀት ጉድለት አውሮጳም ውስጥ ቢከሰት ከባድ ቀውስ የሚፈጠር ይሆናል። ይኸውም፣ የአውሮጳው ኅብረት አባል-ሀገሮች በማስትሪኽት/ኔደርላንድ በተፈራረሙትና ባፀደቁት ውል መሠረት፣ የጋራውን ሸርፍ/ማለት የኦይሮን ርጉእነት ለመጠበቅ የመንግሥት በጀቱ ጉድለት ከጠቅላላው ብሔራዊ ውጤት ከ፫ በመቶ እንዳይበልጥ የማድረግ ኃላፊነት አለባቸው። ግን፣ የሚገርመው፣ የማስትሪኽቱ ውል ያጠበቃቸው መስፈርቶች አብሮ-ደራሲና ጠባቂ ስትባል የነበረችው ጀርመን ራሷ በ፪ሺ፫ ሂደት መጀመሪያይቱ አባል-ሀገር በመሆን የበጀቷን ጉድለት ከ፫ በመቶ አብልጣ የተገኘችበት ድርጊት ነው። ከጀርመን ቀጥላ ፈረንሳይም ነበረች የማስትሪኽቱን መሥፈርት ማሟላት ተስኗት የተገኘችው። መሥፈርቱን ያላሟላው አባል-መንግሥት ከፍተኛ መቀጫ መክፈል ነበረበት፣ ግን የጀርመን ገንዘብሚኒስትርና የፈረንሳይ አቻቸው በፖለቲካው ክርክር አማካይነት ማዕቀቡን ለማስቀረት ችለዋል። ይኸው ከማዕቀብ ለመዳን የተቻለበት ሁኔታ በፓሪስና በበርሊን ከፍተኛውን የእፎይታ ስሜት ነበር የፈጠረው። ሁለቱም ሀገሮች--ጀርመንና ፈረንሳይ-- የበጀቱን ጉድለት ለመግታት የተቻለውን ርምጃ ሁሉ እንዳንቀሳቀሱ ያስገነዘቡት ጀርመናዊው ገንዘብሚኒስትር ሃንስ አይኸል ስለጉዳዩ የሰጡት አስተያየት “አንዲት አባል-ሀገር--እንደጀርመንና እንደፈረንሳይ-- ሁሉን መመሪያና ግዴታ ፈጽማ ሳለ፣ አሁን ጥፋተኛ የምትደረግበትን ውሳኔ አንድ የጀርመን ገንዘብሚኒስትር ሊቀበለው አይችልም፣ በሌላው በኩል ግን ለሚቀጥሉት ዓመታት አለቅጥ ከገዘፈው የበጀት ጉድለት ለመላቀቅ የትኛው ፖለቲካ-መርሕ ትክክል እንደሚሆን ልንስማማበት እንፈልጋለን” የሚል ነበር።

ግን ይኸው የገንዘብ-ሚኒስትር ሃንስ አይኸል አቋም የሁሉንም ድጋፍ ያገኛል ማለት አይደለም። የጀርመንን አቋም ከተቃረኑት ወገኖች መካከል በተለይ የሚጠቀሱት፥ የአውሮጳው ኅብረት የሸርፍ ጉዳዩች ተጠሪ ፔድሮ ሶልቬሽ፣ እንዲሁም የፊንላንድ፣ የኔደርላንድ፣ የእስጳኝና የነምሳ ገንዘብ-ሚኒስትሮች ናቸው። ጀርመንና ፈረንሳይ ያመራሩን ሚና መያዝ ካለባቸው፣ በራሳቸውም ዘንድ የለውጡን ርምጃ በእውነት መፈፀም እንደሚገባቸው ነበር ሂሰኞቹ ያስገነዘቡት።

የሆነ ሆኖ፣ አብዛኞቹ አውሮጳውያት ሀገሮች--የማስትሪኽቱን የበጀት አያያዝ መሥፈርት የፈፀሙትም ጭምር--ለፈጣኑ የኤኮኖሚ ዕድገት እንቅፋት የሆኑትን የመዋቅር ችግሮች እንዲጋተሩ ግዴታ ነበር የሆነባቸው። በብዙ ሀገሮች ውስጥ በተለይም በማኅበራዊው ዘርፍ በኩል የተደቀኑት የመዋቅር ችግሮች ናቸው ለኤኮኖሚው ግስጋሴ እክል የሆኑት። መንግሥታቱ በጡረታ አበሉ ሥርዓት፣ በሥራአጥነት አበሉ ዋስትና፣ በጤና ጥበቃው ዋስትና እና በጠቅላላው ማኅበራዊ ኑሮ ሥርዓት ረገድ የሚጥሩለት የለውጡ ርምጃ በኅብረተሰቡ ዙሪያ ብርቱ ተቃውሞ ነው የሚደቀንበት፤ ስለዚህም ነው የተሐድሶው ለውጥ በየጊዜው መፋጠን የሚሳነው። ይኸው ሁኔታ ነው የአውሮጳው ኤኮኖሚ ሂደት ከዩኤስ-አሜሪካው ኋላ የሚያዘግም እንዲሆን የሚያደርገው።