1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የዓለም ኤኮኖሚ መድረክ በዳቮስ

ረቡዕ፣ ጥር 21 2000

በኢንዱስትሪ ልማት የበለጸጉት መንግሥታት የዘንድሮው የዓለም ኤኮኖሚ መድረክ ጉባዔ ባለፈው ሣምንት እንደተለመደው በስዊትዘርላንድ መዝናኛ ስፍራ በዳቮስ ተካሂዷል። 38ኛውም የዓለም ኤኮኖሚ መድረክ ስብሰባ እንደወትሮው የኢንዱስትሪው ዓለም የኤኮኖሚ ዘርፍ ቀደምት ተጠሪዎች፤ ፖለቲከኞች፣ ከመንግሥት ነጻ የሆኑ ድርጅቶች ልዑካንና የኪነ-ጥበብ ሰዎችም የተሳተፉበት ነበር።

https://p.dw.com/p/E0cQ
ምስል AP

የዓመቱ የፊናንስ ገበያ ቀውስ በጋረደው መድረክ ከዓለም ኤኮኖሚ ሁለንተናዊ ይዞታ ባሻገር የነዳጅ ዘይት ዋጋና የምግብ ምርቶች መናር፣ የአካባቢ ተፈጥሮ ጥበቃ፣ ረሃብና ድህነት ዓበይቱ መነጋገሪያ አርዕስት ነበሩ። ለችግሮቹ ጭብጥ የመፍትሄ ሃሣቦችን ለማፍለቅ ተችሏል ወይ? በስዊትዘርላንድ ተራራማ መዝናኛ ስፍራ በዳቮስ በያመቱ የሚካሄደው ዓለምአቀፍ የመድረክ ጉባዔ የሃብታም ሃገራት ፖለቲከኞችና የምጣኔ-ሐብት ዘርፍ ተጠሪዎች የዓለምን የኤኮኖሚ ሁኔታ አንስተው የሚወያዩበትና ለችግሮቻቸው የመፍትሄ ሃሣቦችን የሚያንሸራሽሩበት ነው። የዓለም የኤኮኖሚ መድረክ እንደመባሉ መጠን ድሆች አገሮችን በቅርብ ያስተሳሰረ ባለመሆኑ “የሃብታሞች ክበብ” የሚባልበት ጊዜም አልታጣም።

ለዚህም ነው በአንጻሩ ታዳጊ አገሮችን በሰፊው የሚያቅፍ የዓለም ማሕበራዊ መድረክ ተፈጥሮ ከዓመት ዓመት የዳቮሱን ስብስብ ሲቃወም፤ ሲፈታተንና የራሱን አማራጭ ሲያቀርብ የቆየው። ወደ ዳቮስ መለስ እንበልና በዚህ ዓመቱ የዓለም ኤኮኖሚ መድረክ ጉባዔ በርካታ የመንግሥታት መሪዎችንና ቀደምት የኢንዱስትሪ ተጠሪዎችን ጨምሮ ከ 2500 የሚበልጡ ልዑካን ተሳትፈዋል። አምሥት ቀናት የፈጀው ስብሰባ የተካሄደው “ሃይልን ለጋራ ተሃድሶ” በሚል መርሆ ነበር። የዳቮሱ የዓለም ኤኮኖሚ መድረክ ቆርቋሪ ክላውስ ሽዋብ ስለዚሁ ሃይልን ስለማስተባበሩ ጽንሰ-ሃሣብ ሲናገሩ እንዲህ ይላሉ።

“በወቅቱ ልንወጣቸው የሚገቡ በርካታ ፈተናዎች ተደቅነውብን ነው የሚገኙት። ይህ ደግሞ በፊናንስና በአካባቢ ጥበቃ መሰል ዘርፎች የተወሰነ አይደለም። ታዲያ ችግሩን ልንወጣው የምንችለው ዓለም ተባብሮ ሊሠራ ሲችል ብቻ ይሆናል። ይህ እንግዲህ አንዱ ነጥብ ነው። ሁለተኛ የዓለማችን ሁኔታ እጅግ መቀየሩን መገንዘብ አለብን። ይህም ስለ ተሃድሶ ማሰብ ይኖርብናል ማለት ነው”

በእርግጥም የዛሬይቱ ዓለም ችግሮች የጋራ መፍትሄን የሚጠይቁ ናቸው። ይሁንና ጥያቄው ሃሣቡ ገቢር ሊሆን መቻሉ ላይ ነው። ለማንኛውም የዳቮሱ መድረክ ጉባዔ የተካሄደው ከሁሉም በላይ የአሜሪካ ባንኮች የብድር ፖሊሲ ክስረት ያስከተለው የምንዛሪ ገበያ ውዥምብር በዓለም ኤኮኖሚ ሂደት ላይ የደቀነው የቀውስ አደጋ በጋረደው ሁኔታ ነበር። እርግጥ ችግሩ ገፍቶ ዓለምአቀፍ የኤኮኖሚ ቀውስ በማስከተሉ ጉዳይ ያለው አመለካከት የተለያየ ነው። በአሜሪካ የአገሪቱ ብሄራዊ ኤኮኖሚ ራሱን የማዳን ብቃት አለው የሚለው አስተሳሰብ የሚያመዝን ሲሆን አውሮፓውያን በአንጻሩ ተጠራጣሪዎች ናቸው። የተፈራው እንዳይደርስ አጥብቀው ይሰጋሉ።

“አሜሪካን ሲያስነጥሳት የተቀረው ዓለም ጉንፋን ይይዘዋል’ የሚለው የቆየ አነጋገር ዛሬም በተወሰነ ደረጃ ትርጉሙን አላጣም። በሌላ በኩል የእሢያ የኤኮኖሚ ተጠሪዎች በዓለምአቀፍ ደረጃ ያሰጋው ቀውስ ለዕድገት ዕርምጃቸው መሰናክል ይሆናል ብለው አያስቡም። ይልቁንም በተለይ በተፋጠነ ዕድገት ላይ የሚገኙት ቻይናና ሕንድ የዓለም ኤኮኖሚን ለመደግፍ፤ እንዲሁም የአሜሪካንና የአውሮፓን ድክመት ለመሸፈን የሚያበቃ የበለጠ ክብደት እንደሚያገኙ ነው የሚያምኑት። የሕንድ የንግድ ሚኒስትር ካማል ናት እንዳሉት አገራቸው በዓለምአቀፉ የኤኮኖሚ ቀውስ ሳቢያ ጨርሶ አደጋ ይከተላል የሚል ስጋት የላትም።

ባለሥልጣኑ “የሕንድ የዕድገት ታሪክ በውስጥ ገበያ እንጂ በውጭ የንግድ ገበያ የሚንቀሳቀስ አይደለም። ስለዚህም ከዓለም ኤኮኖሚ የዕድገት መንኮራኩሮች አንዷ የሆነችው ሕንድ ምናልባት ሊከሰት የሚችልን ማቆልቆል ለመግታት የበኩላን ድርሻ ለማድረግ ትችላለች” ሲሉ ተናግረዋል። ቻይናም ቢሆን በዚህ በያዝነው 2008 ዓ.ም. ጀርመንን በመፈንቀል በዓለም ላይ ሶስተኛዋ ጠንካራ የኤኮኖሚ ሃይል እንደምትሆን ነው የሚጠበቀው። የአገሪቱ የኤኮኖሚ ዕድገት ባለፉት ዓመታት ከሞላ-ጎደል በተመሳሳይ መጠን ያለማቋረጥ ሲራመድ መጥቷል። በውጭ ተጽዕኖ በቀላሉ ይናጋል ብሎ የሚያስብም ብዙ የለም።
በአንጻሩ በአውሮፓ ከዓመታት ጋብታ በኋላ እንደገና መንሰራራት የያዘው ኤኮኖሚ የዕድገት አቅጣጫውን ይዞ መቀጠሉ እንደገና ማጠያየቁ አልቀረም። የጀርመን መንግሥት ለምሳሌ ቀደም ሲል ለያዝነው 2008 ዓ.ም. የተነበየውን የዕድገት መጠን በጥቂቱ ዝቅ አድርጎ ማረም ግድ ሆኖበታል። ዘንድሮም እንግዲህ በዕድገት ተሥፋ ተመልተው የቀጠሉት የእሢያው የዓለም ኤኮኖሚ መንኮራኩሮች ናቸው። ለነገሩ የዳቮሱ መድረክ እየተለወጠ በሄደው የኤኮኖሚ ሃይል አሰላለፍ ሲወያይ ዘንድሮ ለመጀመሪያ ጊዜ አይደለም። ሆኖም የወቅቱ የፊናንስ ቀውስ ለለውጡ ላቅ ያለ ክብደት ሰጥቶታል።

እርግጥ በተፋጠነ ዕድገት ላይ የሚገኙት ቻይናና ሕንድ የምዕራቡን ዓለም ድክመት መሸፈን በመቻላቸው የሚጠራጠሩት ገና ብዙዎች ናቸው። ግን ጀርመናዊው የኢንዱስትሪ አማካሪ ሮላንድ በርገር እንደሚሉት ቢቀር ችግሩን ማርገቡ የሚጠበቅ ጉዳይ ነው። “አውሮፓ ውስጥ፤ በተለይም በጀርመን በነዚህ አዳጊ አገሮች ገበዮች የሚታየው ዕድገት ለኛ የእግዜር ስጦታ ነው ብዬ አስባለሁ። ለምን ቢባል እኛ በመዋዕለ-ነዋይ አቅርቦትና በመዋቅራዊ ግንባታ ረገድ ጠንካሮች ነን። ጥራት ያላቸውን አውቶሞቢሎችን የመሳሰሉ ምርቶችን በማቅረቡም ረገድ እንዲሁ!” ብለዋል።
ፈውስ ሰጪው መድሃኒት እንግዲህ እየተበራከተ መሄዱ አልቀረም። በዓለምአቀፉ ኤኮኖሚ ላይ የተደቀው አደጋ ቢከሰት ሸክሙ እንደቀድሞው በአንድ ትከሻ ላይ የሚያርፍበት ጊዜ አልፋል። በሌላ አነጋገር የሃይል አሰላለፉ ተቀይሯል ማለት ነው። በዳቮሱ መድረክ የተሰበሰቡ የፊናንስ ተጠሪዎችና የዓለም የገንዘብ ተቋማት ወኪሎች የባንኮችን አያያዝና ግልጽ አሠራር በማዳበሩ ሃሣብ መምከራችው የወቅቱ ችግር ግንዛቤ ማግኘቱን ያመለክታል። የዓለም ንግድንም በተመለከተ በዳቮሱ መድረክ ላይ የተገኙት የአውሮፓ፣ የአሜሪካና የሌሎች ሃገራት የንግድ ሚኒስትሮች በወቅቱ ተሰናክሎ የሚገኘውን የዓለም ንግድ ደምቦችን የማለዘብ ድርድር መልሶ በማንቀሳቀሱ ሃሣብ አንድነት አሣይተዋል። ሆኖም ይህ አሣሪነት የሌለው ስምምነት የዶሃውን ድርድር መልሶ ሕያው ለማድረግ መብቃቱ ባለፉት ዓመታት የታዩ ተመሳሳይ ሁኔታዎች ሲታሰቡ ሲበዛ የሚያጠራጥር ነው።

ፍትሃዊ የዓለም ንግድን ካነሣን አይቀር በድርድሩ መሰናከል ወይም መጓተት ይበልጡን የሚጎዱት ታዳጊዎቹ አገሮች ናቸው። የበለጸጉት መንግሥታት ለነዚሁ ገበዮቻቸውን በሚገባ ለመክፈት አለመፈለግና ገበሬዎቻቸውን በመደጎም ዋጋ ማጣጣላቸው በተለይም በታዳጊው ዓለም አርሶ-አደር ላይ ከባድ ተጽዕኖ አለው። ድህነትን ለመቀነስ የሚደረገውን ጥረት አንቆ የያዘ ጉዳይ ነው። የታዳጊው ዓለም ችግሮች ከንግዱ ባሻገርም ብዙ የተወሳሰቡ ናቸው። የአካባቢ ተፈጥሮ ይዞታ፣ የሕዝብ ቁጥር መናርና የፍጆቱም ማየል ፈታኞች እየሆኑ ሄደዋል። የምግብ ችግር ወደፊትም በሚሊያርድ ለሚቆጠር የዓለም ሕዝብ ፈተና ሆኖ እንደሚቀጥል ጨርሶ አያጠራጥርም።

ተመራማሪዎች የዓለም የእርሻ ምርት በተለይም የዕህል ዋጋ በዓለምአቀፉ ፍጆት ማየልና በታክስ መጨመር፤ በአንጻሩም በምርቱ ማቆልቆል ሳቢያ እያደገ እንደሚሄድ ይተነብያሉ። የዓለም ባንክ ፕሬዚደንት ሮበርት ዞሊክም የመሠረታዊ ምግብ ምርቶች ዋጋ በብዙ አገሮች፤ በተለይም በአፍሪቃ እጅግ እየናረ መሄድ አስጊ እንደሆነ ነው ያስገነዘቡት። ዞሊክ ለምግብና ለኤነርጂ ከፍተና ዋጋ የተጋለጡ ያህል ሃገራት መኖራቸውንም ጠቅሰው በነዚሁ ላይ ያለመ የመቋቋም ጥረት ማስፈለጉን አስረድተዋል። ለምሳሌ በቆሎንና ስኳርን የመሳሰሉት ተክሎች ባዮ ነዳጅን ለማምረት መጠቀሚያ መሆናቸው የዋጋውን ሸክም በጣሙን ነው ያከበደው።

በዳቮሱ መድረክ ጉባዔ ይህ ብቻ ሣይሆን የውሃ እጥረት የደቀነው አደጋም ግንባር-ቀደም ጉዳይ ሆኖ መቅረቡ አልቀረም። በተባበሩት መንግሥታት መረጃ መሠረት ዛሬ በዓለም ላይ ንጹህ የመጠት ውሃ ማግንት የማይችለው ሕዝብ አንድ ሚሊያርድ ገደማ ይጠጋል። እስከ 2050 ዓ.ም. ድረስ በአምሥት ዕጅ ሊጨምር እንደሚችልም ነው የሚገመተው። የድርጅቱ ዋና ጸሐፊ ባን-ኪ-ሙን ከመድረኩ ስብሰባዎች በአንዱ ላይ ባሰሙት ንግግር “ንጹህ ውሃ ለሁሉም ማዳረስ-ይህ ዛሬ በዓለማችን ላይ ተደቅኖ የሚገኘው ትልቁ ፈተና ነው። እስከቅርብ ድረስ በቂ ውሃ አለ፤ ለዕለታዊ ኑራችንም ሆነ ለኤኮኖሚያችን አደጋ የለም ብለን እናምን ነበር። እርግጥ ውሃ እንዳይባክን የሚደረጉ ጥረቶች አሉ። በአጠቃላይ ግን ጉዳዩ እስካሁን ተገቢውን ትኩረት አግኝቷል ለማለት አይቻልም” ሲሉ ነው ያስገነዘቡት።

የኤነርጂና የምግብ ፍጆት መጨመር፤ እንዲያም ሲል የዋጋው መናር ድህነትን የመቀነሱን ጥረት ሁሉ የባሰ የሚያከብድ ነው። የዳቮሱ መድረክ ተሰብሳቢዎች ቢቀር ጭብጥ ችግሮችን አንስተው ተወያይተዋል። ተግባራዊ ሂደቱ ወደፊት ምን እንደሚሆን መመዘን ባይቻልም በተወሰነ ደረጃ ጠቃሚ ነበር ለማለት ይቻላል። በዛም አነሰ ተሰብሳቢዎች ለውጥ ፈላጊ ሆነው መገኘታቸው አልተሰወረም። በአጠቃላይ “ሃይልን ለጋራ ተሃድሶ” የሚለው መርህ ሁሉንም ያስተሳሰረ ነበር።