1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የዓለም ኤኮኖሚ መድረክ በላቲን አሜሪካ

ረቡዕ፣ ሚያዝያ 7 2001

በላቲን አሜሪካ ላይ ያተኮረ የዓለም ኤኮኖሚ መድረክ ጉባዔ ባለፈው ምሽት ብራዚል ሪዮ-ዴ-ጃኔይሮ ላይ ተከፍቷል። ሶሥት ቀናት በሚፈጀው የመድረክ ጉባዔ አርባ ገደማ ከሚጠጉ ሃገራት የተጓዙ 500 የፖለቲካ ባለሥልጣናት፣ የኤኮኖሚው ዘርፍ ተጠሪዎችና የምጣኔ-ሐብት ባለሙያዎች እየተሳተፉ ነው።

https://p.dw.com/p/HXed
ምስል DW

የላቲን አሜሪካ መንግሥታት መሪዎች፣ የኤኮኖሚ ዘርፍ ተጠሪዎችና የሙያው ጠበብት ብራዚል-ሪዮ ላይ ለአካባቢው በተዘጋጀ ልዩ የዓለም ኤኮኖሚ መድረክ ጉባዔ ተሰብስበው ዓለምአቀፉ የፊናንስ ቀውስ ላስከተለው ችግር የበኩላቸውን መፍትሄ እያፈላለጉ ነው። ከቅርቡ የቡድን-ሃያ ዓቢይ ጉባዔ በኋላ የተከፈተው የሶሥት ቀናት ስብሰባ በተለይም ለዓለምአቀፉ ቀውስ የአካባቢውን ምላሽ ለመስጠት ጠቃሚ የውይይት መድረክ እንደሚሆን ይታመናል። በዛሬው ምሽት የብራዚሉ ፕሬዚደንት ሉላ-ዳ-ሢልቫና ሌሎች የአካባቢው መንግሥታት መሪዎች በመድረኩ ላይ ተገኝተው ንግግር የሚያሰሙ ሲሆን በተለያዩ ንዑስ ኮሚቴዎች አማካይነት ችግሩን ጥለቅ ብሎ የመመርመሩ ተግባር በሰፊው እንደሚጀምር ነው የሚጠበቀው።

መድረኩን በማዘጋጀቱ በኩል አስተዋጽኦ ያደረገው የብራዚል ንግድ አራማጅ ወኪል የአፔክስ ሃላፊ አሌሣንድሮ ቴክሢየራ “በዓለምአቀፉ ቀውስና ይሄው በላቲን አሜሪካ ላይ ባሳደረው ተጽዕኖ መወያየቱ ያለውን ጥቀሜታ ጠንቅቀን እናውቃለን” ሲሉ ነው የስብሰባውን ክብደት ያስገነዘቡት። በዕውነትም ዓለምአቀፉ የፊናንስ ቀውስ በአካባቢው ላይ ያስከተለው ችግር በቀላሉ የሚገመት አይደለም። የተባበሩት መንግሥታት የላቲን አሜሪካና ካራይብ የኤኮኖሚ ኮሚሢዮን በአሕጽሮት ECLAC ባለፈው ሣምንት ባቀረበው ዘገባ እንዳመለከተው ቀውሱ በአካባቢው ላይ ብርቱ ተጽዕኖ ይኖረዋል ተብሎ ነው የሚጠበቀው።
በተጨማሪ በአካባቢው በቅርቡ የታየው የውጭ መዋዕለ-ነዋይ ማቆልቆልም ቀጣይነት እንደሚኖረው ተመልክቷል። ኮሚሢዮኑ ባለፈው 2008 ዓ.ም. ቀደም ካለው 2007 ሲነጻጸር ከ 184 ወደ 89 ቢሊዮን ዶላር የቀነሰው የመዋዕለ-ነዋይ አቅርቦት በዚህ ዓመትም በተጨማሪ 50 ከመቶ መጠን እንደሚወድቅ ነው የሚተነብየው። በተመሳሳይ ጊዜ የላቲን አሜሪካ የውጭ ንግድም በዘጠኝ ከመቶ ቀንሷል። ችግሩን ለመታገል ብዙ ጥረት ይደረግ እንጂ የኤኮኖሚው ተኮማትሮ መቀጠል የማይቀር ነገር እየሆነ ነው።
በሌላ በኩል የላቲን አሜሪካ አገሮች በቀውሱ የሌላውን ያህል አልተጎዱም የሚሉና ችግሩን በተሻለ ሁኔታ ለመወጣት እንደሚችሉ የሚያምኑ ወገኖችም አልታጡም። ከነዚሁ አንዱም በዓለም ላይ ታላቁ የመድህን ገበያ የሆነው የሎይድስ-ኦፍ-ለንደን ሊቀ-መንበር ፒተር ሌቨን ሲሆኑ አካባቢው ችግሩን በተሻለ ሁኔታ ለመወጣት እንደሚችል ነው የሚናገሩት። ያም ሆነ ይህ ሌቨን ያሉትም ከሆነ በመጀመሪያ ጭብጥ የመፍትሄ ሃሣብ መገኘትና ገቢር ሊሆን መቻል ይኖርበታል።

የሪዮው ስብሰባ በአሜሪካ መንግሥታት ጉባዔ ለመሳተፍ መድረኩ ባበቃ በማግሥቱ በፊታችን አርብ ወደ ትሪኒዳድና ቶባጎ ለሚሻገሩት የላቲን አሜሪካ ፕሬዚደንቶች የጋራ ፖሊሲ ነጥቦችን ይዘው መሄድ እንዲችሉም መልካም አጋጣሚ ነው። የዩናይትድ ስቴትሱን ፕሬዚደንት ባራክ ኦባማን የሚጠቀልለው የመንግሥታት መሪዎች ጉባዔ ለምዕራባዊው የምድራችን ክፍል ችግሮች መፍትሄ ለማግኘት በሚያደርጉት ጥረት ይህ የፖሊሲ መጣጣም ጠቀሜታ ይኖረዋል። እርግጥ የላቲን አሜሪካው የዓለም ኤኮኖሚ መድረክ ሃላፊ ኤሚሊዮ ሎዞዮ እንዳሉት ከቀውሱ ለመላቀቅ በሚደረገው ጥረት የአካባቢው ልዩ ባሕርያትም ሊተኮርባቸው ይገባል።

“የላቲን አሜሪካ ችግር አብዛኛው የእኩልነት እጦት የሚከሰትበት የድሃ-ድሃ ክፍለ-ዓለም ሆነን አይደለም። እርግጥ ቀውስ ላይ ነው የምንገኘው። ሆኖም 90 በመቶው የአካባቢው አጠቃላይ ብሄራዊ ምርቶች ወደ መዋዕለ-ነዋይ ደረጃ ደርሰዋል። ይህ ተመሳሳይ አይገኝለትም። የምናገረው ስለ ብራዚል፣ ሜክሢኮ፣ ኮሉምቢያ፣ ፔሩና ቺሌ ነው። የነዚህ ሃገራት የባንክ ስርዓት ከምዕራቡ አገሮች ይበልጥ ካፒታላዊ የሆነ ነው። ገበዮቻቸው ዕድገት ይታይባቸዋል። ይህ ደግሞ ቀውሱ ያስከተለውን የውጭ ንግድ መቀነስ ለማካካስ ጥሩ መሣሪያ ነው የሚሆነው”

የሆነው ሆኖ መፍትሄ ለማግኘት የተለያየው የላቲን አሜሪካ ገጽታና የቀውሱም ባሕርይ ተያይዞ በመልክ በመልኩ መጤን የሚኖርት ነው የሚመስለው። ለምሳሌ ብራዚልን የመሰለች አገር በአብዛኛው በእርሻ ምርቶች ላይ ጥገኛ ስትሆን ቀውሱ የሚጫናት ንግዷ በአሜሪካ ላይ ጥገኛ ከሆነው ከሜክሢኮ በተለየ ሁኔታ ነው። በሌላ በኩል የላቲን አሜሪካ አገሮች ከራሳቸው ሃብት ተጠቃሚ ለመሆን ይችላሉ። ይህ ሁሉ በመድረኩ ላይ ትኩረት የሚሰጠው ሲሆን የግሉ ኤኮኖሚው ዘርፍ በአካባቢው ዕድገት ላይ የሚኖረው ሚናም ሰፊ ውይይት የሚደረግበት ዓቢይ ጉዳይ ነው። ድርሻው እየጨመረ ሄዷል፤ ትልቅ ክብደት አለው።
የብራዚሉ የውጭ ንግድ ድርጅት ወኪል የአፔክ ሃላፊ አሌሣንድሮ ቴክሢየራ እንደሚያስረዱት በአጠቃላይ በመንግሥትና በግሉ ዘርፍ መካከል የሚደረገው ውይይት ዕርምጃ እያሳየ ነው የመጣው።

“ከአሥር ዓመታት በፊት ላቲን አሜሪካ የነበሯትን ዓለምአቀፍ ኩባንያዎች በእጣት መቁጠር ይቻል ነበር። ዛሬ በብራዚል፣ ሜክሢኮ፣ ኮሉምቢያ፣ አርጄንቲና ቺሌና ሌሎች አገሮች ቁጥር ስፍር የላቸውም። በመሆኑም መድረኩ ላቲን አሜሪካ ለኤኮኖሚና ማሕበራዊ ዕርምጃ ጠቃሚ ስፍራ ለመሆኗ ምልክት ነው”

ብራዚል መድረኩን እንድታስተናግድ መመረጧም የስብሰባው ሃላፊ ኤሚሊዮ ሎዞዮ እንዳሉት ያለ ምክንያት አይደለም። አገሪቱ በተፋጠነ ዕድገት ላይ ከሚገኙት አገሮች መካከል አንዷ ስትሆን እንደ ቻይና ወይም እንደ ሕንድ በዓለም ንግድ ላይ ክብደቷ እየጨመረ መምጣቱም የተሰወረ አይደለም። በመሆኑም በላቲን አሜሪካ በኤኮኖሚ ዕርምጃ ረገድ ግናር ቀደም ናት።

“ብራዚል የተሥፋ ነጸብራቃችን ናት። የአገሪቱ የፊናንስ ዘርፍ በጥሩ ሁኔታ ላይ ነው የሚገኘው። እርግጥ አምራቹ የኤኮኖሚ ዘርፍ እንደሌላው ሁሉ በቀውሱ ተነክቷል። ይሁንና ውስጣዊው ገበያ ባለፉት ጊዜያት በጣሙን እያደገ ነው የመጣው። አገሪቱ ከዚሁ ሌላ የምርት ፍጆትን የሚያራምድ ወጣት ሕብረተሰብ አላት። ይህ ደግሞ ትልቅ ምንጭ ነው”

እርግጥ የላቲን አሜሪካይቱ ግዙፍ አገር ኤኮኖሚም የቅርብ መረጃዎችን ለተመለከተ ከስድሥት ዓመታት ተከታታይ ዕድገት በኋላ አሁን ቀላል ችግር ላይ አይገኝም። የኢንዱስትሪው ንግድ አሥር ከመቶ ሲያቆለቁል እስካለፈው ዓመት መጨረሻ የታየው አምሥት ከመቶ ዕድገት ለጊዜው የማይደረስበት ነገር ሆኗል። የኤኮኖሚው ቀውስ የላቲን አሜሪካዋን ዝሆን ክፉኛ ሲፈታተን በዓመቱ የመጨረሻ ሩብ አጠቃላዩ ብሄራዊ ምርት አራት በመቶ ቀንሶ ነበር። ይህም መንግሥት የዚህ ዓመት የዕድገት ግምቱን ወደ ሁለት ከመቶ ዝቅ እንዲያደርግ አስገድዷል። ብሄራዊው የኢንዱስትሪ ማሕበር እንዲያውም አንዳች ዕድገት አይኖርም ባይ ነው።

ሁኔታው በብዙዎች የአካባቢው ሃገራት ቢያንስ ተመሳሳይ አለያም የባሰ ሆኖ ነው የሚገኘው። በተለይም የታናናሾቹ የላቲን አሜሪካ አገሮች ሁኔታ ሲበዛ ያሳስባል። ምክንያቱም እነዚሁ አብዛኛውን መዋዕለ-ነዋይ እያጡና በአንጻሩም የበለጠ ተበዳሪ እየሆኑ የሚሄዱ መሆናቸው ነው። የንግዱ ሚዛን ዝቤትም ችግሩን የባሰ ያደርገዋል። የሰሜን ደቡቡ የንግድ ልውውጥ በኤኮዋዶር-ኪኢቶ የላቲን አሜሪካ የማሕበራዊ ሣይንስ ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪ ዶር ፌርናንዶ ማርቲን እንደሚሉት ሚዛን የጠበቀ አይደለም።

“ከላቲን አሜሪካ ጋር የሚደረገው ንግድ ከሁሉም በላይ ከሰሜን በደቡብ አቅጣጫ የሚራመድ ነው። የበለጸገው ሰሜን ያለቁ ምርቶችን ለደቡቡ የዓለም ክፍል የሚሸጥ ሲሆን ደቡቡ ደግሞ ጥሬ ሃብትና ሰፊ የሥፋ ጉልበት የሚጠይቁ ምርቶችን ነው የሚያቀርበው። ይህ ነው እንግዲህ በአጠቃላይ በላቲን አሜሪካ የማየው የሥራ ክፍልል! ለየት ብለው የሚታዩ ካሉ ሜክሢኮና ብራዚል ብቻ ናቸው”

ሃቁ ይህ ሲሆን የንግዱን ሚዛን መለወጥ አጣዳፊ ጉዳይ ያደርገዋል። በመሠረቱ ንግድ ዕድገትን ለማራመድ የሚረዳ ጥሩ መሣሪያ እንደሆነ ዓለም በሙሉ ያውቀዋል። ሆኖም የሚያሳዝነው ሁሉም አገሮች ተጠቃሚ ሊሆኑ አለመቻላቸው ነው። በአብዛኛው ተጠቃሚዎቹ ሃብታሞቹ አገሮች ሆነው ይቀጥላሉ። ፌርናንዶ ማርቲን እንዳሉት በዓለምአቀፉ ንግድ ፊልም ላይ ዋነኞቹ ተዋንያን ሃብታሞቹ ሲሆኑ ድሆች አገሮች ቁም አድማቂ ብቻ ናቸው”

ለማጠቃለል በላቲን አሜሪካም ሆነ በተቀረው ዓለም የፊናንሱ ቀውስ ካስከተለው ድቀት ሁነኛ በሆነ መንገድ ለመላቀቅ ፍትሃዊ ንግድ መስፈኑ ግድ ነው። በቡድን-ሃያ ጉባዔ የዓለም ንግድን ለማጠናከር ቃል ተገብቷል። ግን የቆየውን ስርዓት ፍትሃዊ አድርጎ በመለወጡ ረገድ ጭብጥ ነገር አለመታየቱ ነው ችግሩ!

መሥፍን መኮንን, DW, AP, AFP