1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የዓለም ኤኮኖሚ መድረክ ለአፍሪቃ

ረቡዕ፣ ግንቦት 7 2005

የዘንድሮው ዓመታዊ የአፍሪቃ የዓለም ኤኮኖሚ መድረክ ጉባዔ ባለፈው ሣምንት ኬፕታውን ላይ ተካሂዷል።

https://p.dw.com/p/18Xgh
ምስል picture-alliance/dpa

ከዕለተ-ረቡዕ አንስቶ እስከ አርብ የዘለቀው የሶሥት ቀናት ጉባዔ የተካሄደው «የአፍሪቃን ቃልኪዳን ዕውን ማድረግ» በሚል መርሆ ነበር። በመድረኩ በርካታ የአካባቢውና የውጭ መንግሥታት ተጠሪዎች፣ እንዲሁም የኤኮኖሚው ዘርፍና የሲቪል ሕብረተሰብ ወኪሎች ሲሳተፉ የአፍሪቃን አንድነት አጀንዳ ከግብ ማድረሱ፣ እንዲሁም የኤኮኖሚ ዕድገትንና ልማትን ወደፊት የማራመዱ አስፈላጊነት ሰፊ ትኩረት ተሰጥቶታል።

አፍሪካ ከጥቂት ዓመታት ወዲህ መጪዋ! አዳጊዋ ክፍለ-ዓለም፣ የቻይናን ፈለግ ተከትላ የምትራመድ አህጉር ወዘተ- እየተባለች ትልቅ የኤኮኖሚ ዕርምጃ ሲተነበይላት ነው የቆየችው። እርግጥ በርካታ ከሣሃራ በስተደቡብ የሚገኙ ሃገራት ባለፈው አሠርተ-ዓመት በተከታታይ  የኤኮኖሚ ዕድገት ማድረጋቸው አልቀረም። ይሁንና በዕድገቱ መጠን ማሕበራዊ ልማት የሚገባውን ያህል ታይቷል ለማለት አይቻልም።                             

አፍሪቃ እርግጥ በተፈጥሮ ሃብት የታደለች ክፍለ-ዓለም ናት። ይህም በአግባብ ጥቅም ላይ ቢውል ብዙዎቹን በጸጋው የታደሉትን ሃገራት ከድህነት ሊያላቅቅና ለብልጽግና ጥርጊያ ሊከፍት እንደሚችል ጨርሶ አያጠራጥርም። ግን ያሳዝናል በወቅቱ ሙስና፣ ምዝበራና የበጎ አስተዳደር እጦት ጎላ ያለው የክፍለ-ዓለሚቱ መለያ ሆኖ ነው የሚገኘው። በተከታታይ ከአሥር በመቶ በላይ የኤኮኖሚ ዕድገት አሣየን ሲሉ በቆዩት ሃገራት እንኳ የብዙሃኑን የኑሮ ሁኔታ  በማሻሻሉ ረገድ ይህ ነው የሚባል የረባ ዕርምጃ ጎልቶ አይታይም።

ለአፍሪቃ ኋላ ቀርነት ዋናው ምክንያት ገዢዎቹ አገርና ሕዝብን ለማሳደግ በቂ የፖለቲካ ፍላጎት አለማሣየታቸው ነው። ገዢው መደብ ራሱን ያላግባብ ለማካባት እንጂ ለብዙሃኑ ደህንነትም ሆነ ለበጎ አስተዳደር ጨርሶ ደንታ የለውም። አፍሪቃ ውስጥ የፖለቲካው ስርዓት የሚዘወረው በአብዛኛው በመሪዎቹ የግልና የቡድን ፍላጎት ነው። መንግሥትን እነዚህ ለገዢው መደብ ወይም ለገዢ ቤተሰብ እንደ ገንዘብ ምንጭ አድርገው እንጂ እንደ አስተዳደር አካል አይመለከቱም።  

በዚሁ ሳቢያ በተፈጠረው ኋላ ቀርነት የተነሣ ታዲያ አፍሪቃ ለአያሌ ዓመታት በዓለም ኤኮኖሚ መድረክ ላይ አንዳች ሚና አልነበራትም። ከአምባገነን አገዛዝ ባሻገር የዕዳ ሸክምና የቀዝቃዛው ጦርነት ዘመን ተጽዕኖም በየመልኩ ብርቱ ተጽዕኖ ነበራቸው። ዓለምአቀፉ የኤኮኖሚ ማሕበረሰብም አፍሪቃን ምናልባትም እስከ አዲሱ ሚሌኒየም መግቢያ ድረስ ጨርሶ ችላ ሲል ይህም አፍሪቃ በማቆልቆል ሂደቷ እንድትቀጥል ማድረጉ አልቀረም።                                                                            

Kapstadt Weltwirtschaftsforum
ምስል picture-alliance/dpa

እርግጥ አፍሪቃ ውስጥ ከአያሌ ዓመታት በኋላ ባለፈው አሠርተ-ዓመት ለመጀመሪያ ጊዜ  ያልተቋረጠ የኤኮኖሚ ዕድገት ሲከሰት አፍሪቃ ልትነሣ ነው በሚል የተጠነሰሰው ተሥፋ ጥቂት አልነበረም። ግን ተሥፋው የታለመውን ያህል ፍሬ አልሰጠም። የአፍሪቃ ኤኮኖሚ ባለፈው ዓመት በአማካይ በ 4,5 ከመቶ ሲያድግ ዘንድሮ አምሥት በመቶ እንደሚሆን ነው የሚገመተው። ይህ ደግሞ ድህነትን ለመቀነስ የሚፈለገውን ያህል ድርሻ ይኖረዋል ማለት አይቻልም። ሂደቱ ምናልባትን ለረጅም ጊዜ መቀጠሉ የሚቀር አይመስልም።                                                                                     

ዓለምአቀፉ የምንዛሪ ተቋም IMF የያዝነው አሠርተ-ዓመት እስከሚያበቃ እስከ 2020 ድረስ ዕድገቱ ስድሥት ከመቶ እንደሚሆን ይተነብያል። መለስ ብሎ ለማስታወስ ክፍለ-ዓለሚቱ በቻይና የተፋጠነ ዕድገትና ከዚሁ በተያያዘው የጥሬ ሃብት ፍላጎት ማደግ የተነሣ ነው ከ 2000 ዓ-ም ወዲህ የዕድገት ባለ ተሥፋ መሆን የጀመረችው። ዛሬ አንዳንድ ታዛቢዎች አፍሪቃ ለተዳከመው የምዕራቡ ዓለም ኤኮኖሚ ሣይቀር መድህን ልትሆን ትችላለች እስከማለት ደርሰዋል።                                                                                        

እርግጥ አፍሪቃ በኤኮኖሚ በአግባብ በማደግ ዓለምአቀፍ ሚና እንዲኖራት ከተፈለገ የግሉ ዘርፍ ተሳትፎና የውጭ መዋዕለ-ነዋይ አቅርቦት መስፋፋት ይኖርበታል። ግን በኬፕታውን ሃንደልስብላት የተሰኘው የጀርመን የንግድ ጋዜጣ ወኪል ቮልፍጋንግ ድሬክስለር እንደሚሉት በዚህ ረገድ እስካሁን የታየው ዕርምጃ የመነመነ ነው።

Wolfgang Drechsler Afrika Korrespondent des Handelsblatts
ምስል Iris Ritter/Finanz und Wirtschaft, Zürich

«እነዚህ ለዓመታት የጎን አድማጮች፤ ተመልካቾች ሆነው ነው የኖሩት። የዝግጅቱ ዋና ችግርም ይሄ ይመስለኛል። በየስብሰባው በክፍለ-ዓለሚቱ የግል መዋዕለ-ነዋይ  በሰፊው ሊፈስ ነው የሚል ተሥፋ እንዲጠነሰስ ይደረጋል። ግን የገንዘቡ ፍሰት እስካሁን ይበልጡን በልማት ዕርዳታ ተወስኖ ነው የቆየው። የጉባዔው መፈክር ዘንድሮ «የአፍሪቃን ቃልኪዳን ዕውን ማድረግ» የሚል ነው። ግን አፍሪቃ ጸጋዋን አውጥታ መጠቀም መቻሏ በውጩ የግል ኤኮኖሚ ዘርፍ ላይ ጥገኛ ይሆናል»                                                                            

ማለት የነዚህ የውጭ ኩባንያዎች ካፒታል ያስፈልጋል።

«እነዚሁ አፍሪቃውያንን በአገራቸው በሙያ ማሰልጠናቸው፣ መንገዶችን መዘርጋታቸውና ትምሕርትቤቶችን ማቆማቸውም ግድ ነው። ለኔ የአፍሪቃ መፍትሄ ይሄ ይመስለኛል። የግሉ ዘርፍ በአፍሪቃም በእሢያና በላቲን አሜሪካ እንዳደረገው በሰፊው መዋዕለ-ነዋይ ማድረግ አለበት። ግን ሁኔታው ይህን አይመስልም። ወደ አፍሪቃ የሚሻገረው በዓለም አቀፍ ደረጃ ከሚንቀሳቀሰው መዋዕለ ነዋይ አምሥት ከመቶው ቢሆን ነው። ይህ ደግሞ የዓመኔታ እጦት የፈጠረው ነገር ነው። የግሉ የኤኮኖሚ ዘርፍ ገንዘቡን በአፍሪቃ በስራ ላይ ለማዋል ይፈራል»

በሌላ በኩል በዚህ ረገድ ከአፍሪቃ መልካም ዜና መሰማቱም አልቀረም። ወደ ክፍለ-ዓለሚቱ የሚፈሰው ቀጥተኛ የውጭ መዋዕለ-ነዋይ ባለፉት ዓመታት በሰፊው መጨመሩ ነው የሚነገረው።

«ይህን እርግጥ ማስተባበል አይቻልም። በአፍሪቃ አዝጋሚም ቢሆን ጥቂት ዕርምጃ እየታየ ነው ያለው። ከሣሃራ በስተደቡብ ባለው የአፍሪቃ ክፍል በዚህ ዓመት የ 5,6 ከመቶ ዕድገት ይጠበቃል። ይህ ቢቀር የኤኮኖሚው ዕድገት አራት በመቶና በከፊልም ከዚያ በታች ከነበረበት ከ 90ኛዎቹ ዓመታት የበለጠ መሆኑ  ነው። ግን አፍሪቃ ገና ብዙ ይቀራታል። ሰላሣ ዓመታት በከንቱ መባከኑ መዘንጋት የለበትም። በሌሎች ክፍለ-ዓለማት የኑሮው ደረጃ በ 1975 እና በ 2005 መካከል እያደገ ሲሄድ በአፍሪቃ አቆልቋይ ነበር። እንግዲህ አሃዙ ከዝቅተኛ መሠረት የሚነሣ ነው»

Kapstadt Weltwirtschaftsforum
ምስል picture-alliance/dpa

በአፍሪቃ ዋናው የዕድገት መንኮራኩር በመሠረቱ ጥሬ ሃብት ነው። ግን ይህ ጠቃሜታው የጎላ እንዲሆን አሁን በጥሬ መልኩ ወደ ውጭ ከመላክ ባሻገር የራስን ኢንዱስትሪ በማቆም ሊመረት መቻል አለበት። ይሁን እንጂ ይህ እስካሁን በከፊል በኤነርጂ ጉድለትም ጭምር ሲሳካ አልታየም፤ በቀላሉ ገቢር መሆኑም ሊያምኑት የሚያዳግት ነው። በሌላ በኩል የጀርመኑ የንግድ ጋዜጣ ወኪል ቮልፍጋንግ ድሬክስለር እንደሚሉት አፍሪቃ በዓለምአቀፍ ደረጃ የቀራትን ለማሟላት ከዚህ ቀደም ያልነበረ አዲስ ነገር መፍጠር የለባትም።

«ዕርምጃ ለማድረግ ጎማን በአዲስ መልክ መልሶ መፍጠር አያስፈልግም። በሌሎች ክፍለ-ዓለማት የበጁ ዘዴዎችን ብቻ መጠቀም ነው የሚያሻው። ተቋማትን ማነጽ፣ ግብር ሰብሳቢ ቢሮዎችን መፍጠርና በአግባብ የሚያቅዱ አካላትን ማቋቋም፣ የከተሞች ዕቅድን ዕውን ማድረግ፣ በፍርድቤቶች ለፖለቲከኞች ታዛዥ ያልሆኑ ዳኞችን ማስቀመጥ ወዘተ-! ኬንያ ለምሳሌ ከነጻነት ወዲህ ባለፉት 50 ዓመታት አንዲት ኪሎሜትር የባቡር ሃዲድ እንኳ አልዘረጋችም። በሌላ በኩል በጥሬ ዕቃ ላይ ያለው ጥገኝነት ሲለዝብና ሙስና ሲቀንስ የዕርሻ ልማትም በመንግሥት እንዲራመድ ተደርጓል። በዙ ነገር ማድረጉ የሚቻል ነው። ግን ይህ እንዲሳካ ከሁሉም በላይ ለጋራ ጥቅም ግንባር ቀደም ሆነው የሚቆሙ መሪዎች ያስፈልጋሉ»                          

        

አፍሪቃ ውስጥ እርግጥ ለስኬት አርአያ የሚሆኑ በእጣት የሚቆጠሩ አገሮች አይታጡም። እንደ ምሳሌ ቦትሱዋናን ብንወስድ አገሪቱ ነጻነቷን ስትጎናጸፍ  ከ 15 ኪሎሜትር የሚበልጥ ለዚያውም ኮረኮንች መንገድ አልነበራትም። ሆኖም ግን በኤኮኖሚ አያያዙ ጥሩ በሆነ መንግሥት አማካይነት አገሪቱ ግሩም መዋቅራዊ ግንባታ ለማካሄድ በቅታለች። በዚሁ በብዙ መቶና ምናልባትም በሺህ ኪሎሜትሮች የረዘሙ መንገዶች ሲሰሩ የባንክና የጤና ጥበቃ መዋቅራትም ሕያው ሆነዋል። ለመሆኑ ይሄ እንዴት ሊሆን ቻለ?                                                          

«ለዚህ ምክንያቱ አገሪቱ ጥሬ ሃብቷን ማለትም የአልማዝ ጸጋዋን ከደቡብ አፍሪቃው ዴ ቤር ኩባንያ ጋር በማውጣትና ለገበያ በማቅረብ ገቢዋን በአግባብ ማስቀመጧና መጠቀሟ ነው። አፍሪቃ ውስጥ ለማንኛውም ዕድሉ አለ። ግን የተፋጠነ የኤኮኖሚ ዕድገት በማስፈኑ ረገድ አንዳንድ አማካሪ ኩባንያዎች እንደሚተነብዩት በእሢያ እግር መተካቱ ቀላል የሚሆን አይመስለኝም»

የአፍሪቃው የዓለም ኤኮኖሚ መድረክ ጉባዔ አጀንዳ አንዱ ነጥብ አፍሪቃ በሚቀጥሉት 50 ዓመታት በሚኖራት ገጽታ ላይ የሚያተኩር ነበር። ሂደቱ ተሥፋም ስጋትም የተዋሃደው ሲሆን ጉዞው ቀላል የሚሆን አይመስልም። ቮልፍጋንግ ድሬክስለርም በዚህ ጉዳይ ቆጠብ ማለቱን ነው የሚመርጡት።

Kapstadt, Südafrika, Stadtansicht
ምስል picture alliance/dpa

«እዚህ ላይ በጣም ጥንቁቅ ነኝ። ክፍለ-ዓለሚቱ ያላንዳች ጥርጥር ትልቅ ዕድል አላት። ግን በዚያው መጠን አደጋም እንዲሁ! በወቅቱ አፍሪቃ ውስጥ አንድ ሚሊያርድ ሕዝብ ይኖራል። አሀዙ በ 2030 አንድ ሚሊያርድ ተኩልና ከዚያም በ 2050 ሁለት ሚሊያርድ እያለ የሚያድግ ነው። ይህ እርግጥ ለኩባንያዎች ትልቅ የገቢ ምንጭ ነው። ግን ይሄ ሁሉ ሕዝብ የስራ መስክ ካልተከፈተለት የነውጽ ምንጭ ሊሆን መቻሉም መዘንጋት የለበትም። አፍሪቃ እስካሁን በዚህ ረገድ፤ ማለትም ሕዝቡ ሰርቶ የዳቦው ባለቤት እንዲሆን ለማብቃት ያደረችው በጣሙን ጥቂት ነው። ይህ ደግሞ በወቅቱ ለኔ ከተሥፋ ይልቅ የስጋቴ ምንጭ ነው»

አፍሪቃ ከዚሁ ሌላ ውዝግቦችም ያዘወትሩባታል። በወቅቱ በምዕራብና በምሥራቃዊው አፍሪቃ የሰፈኑት ውዝግቦች በፍጥነት ዕልባት ሊያገኙ ካልቻሉ ለኤኮኖሚው ዕድገት ጎጂ መሰናክሎች እየሆኑ መቀጠላቸው ነው። እርግጥ አፍሪቃ ውስጥ የተያዘው ሁሉ መጥፎ ነው ማለት አይደለም። ሆኖም ተሥፋው የተጋነነ እንዳይሆን ሃቁን ማመልከቱ ተገቢ ይሆናል። በኬፕታውኑ የአፍሪቃ የዓለም ኤኮኖሚ መድረክ ጉባዔ እንዳለፉት ዓመታት ሁሉ የክፍለ-ዓለሚቱ የዕድገትና ድህነትን የማሸነፍ ተሥፋ ዓቢይ ጉዳይ ሆኖ ተነስቷል።                       

ይሁን እንጂ ዘንድሮም ለአፍሪቃ ዕርምጃ ጠንቅ የሆነውን ሙስናንና የተመጽዋችነት ባሕል በማስወገድ ሕብረተሰብን ባሳተፈ ዕድገት የክፍለ ዓለሚቱን ገጽታ ለማደስ አሁንም ገቢር የሚሆን ጭብጥ ዕቅድ አልተቀመጠም። መፍትሄው ከውጭ የሚጠበቅ ነው የሚመስለው። አፍሪቃ ለራሷ ችግር የራሷን መፍትሄ ለማስፈንና ለመተግበር እስካልበቃች ድረስ  መጪው ዘመን ዕውነትም ከተሥፋ ይልቅ የስጋት ነው የሚሆነው።

መሥፍን መኮንን