1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ጉባኤዉ በታዳጊ ሀገራት ተስፋ ተጥሎበታል

ዓርብ፣ ግንቦት 11 2009

በጎርጎሮሳዊዉ ከ ግንቦት 8 እስከ 18 ለ10 ቀናት በጀርመኗ ቦን ከተማ ዉስጥ  በዓለም አቀፍ በአየር ንብረት ለዉጥ ላይ ሲመክር የቆየዉ ጉባኤ በትናትናዉ እለት ተጠናቋል። ጉባኤዉ  በማደግ ላይ ያሉ ሀገራት የአየር ንብረት ተፅእኖን ለመቋቋም ለሚያደርጉት ጥረት ድጋፍ ማግኘት እዲችሉ መንገድ የሚጠርግ ነዉ ተብሏል።

https://p.dw.com/p/2dGg9
Bonn UN Climate Change Conference 2015
ምስል CC-BY-J. Golinski

World Climate Change conference in Bonn - MP3-Stereo


የአየር ንብረት ለዉጥ ጉባኤወች በተለያዩ  ቅርጽና ይዘቶች   ከ ጎርጎሮሳዊዉ 1992 ጀምሮ ለበርካታ  ጊዚያት የተካሄዱ ቢሆንም  ችግሩን በመቀነስ ረገድ አመርቂ ስራ ሳይሰራ መቆየቱን መረጃወች ያመለክታሉ። በተለይ  የአየር ንብረት ለዉጥ ተጽኖ  ምንጭ ሳይሆኑ የችግሩ ገፈት ቀማሽ ለሆኑት  ታዳጊ ሀገራት ትርጉም ያለዉ ድጋፍ ሳይደረግ መቆየቱ ይነገራል። በጎርጎሮሳዉያኑ 2015 በፈረንሳይ ፓሪስ የተካሄደዉ 21ኛዉ የተባበሩት መንግስታት የአየር ንብረት ለዉጥ ጉባኤ  ግን ተጽኖዉን ለመቀነስ የዓለም ሀገራት የተሻለ ዉሳኔ የወሰኑበት  ተደርጎ ሲወሰድ ቆይቷል። በቦን ከተማ  ትናንት ፍጻሜዉን ባገኘዉ ጉባኤ ላይ የተሳተፉት በኢትዮጵያ የደንና የአካባቢ ጥበቃ ሚንስቴር የአየር ንብረት ለዉጥ ትግበራ ዳይሬክተር ጄኔራል አቶ ደባሱ ባይለየኝ በሀሳቡ ይስማማሉ።

«የፓሪስ ስምምነት በተሊy መልኩ በተለይም በማደግ ላይ ላሉና ደሴቶች ላይ ለሚኖሩ ሀገራት የተለዬ ድጋፍ በፋይናንስ በቴክኖሎጅ ና በአቅም ግንባታ እንዲደረግ በግልጽ አስቀምጧል።ስለዚህ ስምምነቱ ከአሁን በፊት ከነበረዉ ዕድል ሰጥቷል።»

ለታዳጊ ሃራት ትኩረት ሰጥቷል የተባለዉ የፓሪሱ ስምምነት ተግባራዊ የሚደረገዉ በገርጎሮሳዊዉ 2020 በመሆኑ ለዚህ የሚያግዙ የትግበራ  ሰነዶች  ለማዘጋጀትም ተደራዳሪ ሀገራት በየ ጊዜዉ እየተገናኙ በመምከር ለይ ይገኛሉ።የሰሞኑ ጉባኤ ዓላማም ይህንኑ የተመለከተ መሆኑን አቶ ደባሱ ገልጸዋል።

የአየር ንብረት ለዉጥ የሚያመጣዉን ተጽዕኖ ለመቋቋም  በማደግ ላይ ያሉ ሀገራት ተጨማሪ የገንዘብ ፣የቴክኖለጂ፣ የቁሳቁስ ድጋፍና የአቅም ግንባታ ስራ  የሚያስፈልጋቸዉ  ቢሆንም በፓሪሱ ስምምነት ዋነኛዋ ተደራዳሪ የነበረችዉ የዩስ አሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በጉዳዩ ላይ ያላቸዉ አቋም የተለየ በመሆኑ በብዙወች ዘንድ  የታሰበዉን ያህል ድጋፍ ላይገኝ ይችላል የሚል ጥርጣሬ አስከትሏል።አቶ ደባሱ ግን እስካሁን የተለዬ ነገር አላጋጠመም ባይ ናቸዉ። 

Deutschland World Conference Center Bonn WCCB
ምስል Getty Images/AFP/P. Stollarz

 «በስብሰባዉ አሜሪካዉያን በፓሪሱ ስምምነት ሙሉ ተሳትፎ እያደረጉ ነዉ ።በፓሪሱ ስምምነት ላለመቀበል ሳይሆን እንዴት ነዉ ተግባራዊ የምናደርገዉ በሚለዉ ላይ ንቁ ተሳትፎ እያደረጉ ነዉ።ከዚያ ባለፈ እንደ ሀገር ፕሬዝዳንቱ የሚወኗቸዉ ዉሳኔወች ይኖራሉ።እነዚህ ዉሳኔወች በፓሪሱ ስምምነት ላይ በአሉታዊ መልኩ አስተዋጽኦ ሊኖራቸዉ ይችላል።እኛ ግን ተስፈኛ ነን  እንደ ሀገርም እንደ ተደራዳሪም ጥሩ ነገር ይመጣል ብለን እንገምታለን።»
እስከ 2018 ድረስ በማደግ ላይ ያሉ ተደራዳሪ ሀገራትን በሊቀመንበርነት የምትመራዉ ኢትዮጵያም የነዚህን ሀገራት ፍላጎት መሰረት ያደረገ ሰነድ እንዲዘጋጅ በሙሉ አቅም በመንቀሳቀስ ላይ እንደምትገኝ ሀላፊዉ አመልክተዋል።

ፀሐይ ጫኔ

ነጋሽ መሀመድ