1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የዓለም አበይት ፖለቲካዊ ክንዉኖች 2014

ሰኞ፣ ታኅሣሥ 20 2007

«ዓለም ከሁለተኛዉ ያዓለም ጦርነት ወዲሕ የዘንድሮን ያክል ሕዝብ ተሰዶ፤ተፈናቅሎባት አያዉቅም።የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ለበርካታ ሕዝብ አስቸኳይ እርዳታ እንዲያቀርብ የዘንድሮን ያክል ተጠይቆ አያዉቅም።»

https://p.dw.com/p/1EC75
ምስል Reuters/Eduardo Munoz

ያለፈዉ ሳምንት ዝግጅታችንን የተከታተላችሁ እንደምታስታዉሱት በጎርጎሮሳዉያኑ 2014 ከአፍሪቃ ዉጪ ባለዉ ዓለም የተከናወኑ አበይት ፖለቲካዊ አዉነቶችን በገሚስ ቃኝተን፤ ቀሪዉን ዛሬ ለመቃኘት ቀጠሮ ነበርን።

የቀድሞዎቹየዩናትድ ስቴትስ ፕሬዝዳንት ጆርጅ ደብሊዉ ቡሽ እና የብሪታንያዉ ጠቅላይ ሚንስትር ቶኒ ብሌር ኢራቅን የወረሩበት ሰበብ፤ሐሰትነቱ ከተጋለጠ ወዲሕ ስሕተታቸዉን መደበቂያሌላ ሰበበብ አላጡም ነበር።«ሳዳም ሁሴን የተወገዱባት ዓለም ሠላሟ ይበልጥ አስተማማኝ ነዉ» የሚል።የዓለምን ታላቅ የሠላም ሽልማት ኖቤልን የተሸለሙት ፕሬዝዳት ባራክ ኦባማ ቢን ላደንን፤ እራሳቸዉ ኦባማ፤ፕሬዝዳንት ኒኮላይ ሳርኮዚ፤ ጠቅላይ ሚንስትር ዴቪድ ካሜሩንና ተባባሪዎቻቸዉ ሙዓመር ቃዛፊን ሲያስገድሉምየቀዳሚዎቻቸዉንብሒል ደጋግመዉታል።

Bildergalerie Kinder der Welt Gaza
ምስል Mohammed Abed/AFP/Getty Images

የዓለም ዘዋሪዎች ዋሹም፤ እዉነት አሉ ደጋፊ፤ ተከታይ አድናቂ እንጂ ፤ ከሳሽ፤ ወቃሽ በርግጥ የለባቸዉም።የሚዘዉሩት ዓለም የጋራ ማሕበር ሰኔ ማብቂያ ይፋ ያደረገዉ ዘገባ ግን ሳዳም፤ቢን ላደን፤ቃዛፊ የተገደሉባት፤ አልቃኢዳ፤ ታሊባን፤ አልሸባብ እና ሌሎች አሸባሪ ቡድናት የጠፉ ወይም የተዳከሙባት ዓለም ሠላም ዘንድሮ ክፉኛ ታዉኳል።ግጭት-ጦርነቱ ከሁለተኛዉ የዓለም ጦርነት ወዲሕ ታይቶ የማይታወቅ የዓለም ሕዝብ አስድዷል ወይም አፈናቅሏል።ከሐምሳ ሚሊዮን በላይ።

«ዓለም ከሁለተኛዉ ያዓለም ጦርነት ወዲሕ የዘንድሮን ያክል ሕዝብ ተሰዶ፤ተፈናቅሎባት አያዉቅም።የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ለበርካታ ሕዝብ አስቸኳይ እርዳታ እንዲያቀርብ የዘንድሮን ያክል ተጠይቆ አያዉቅም።»

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ ፓን ጊ ሙን።የድርጅቱ ዘገባ የሠላም ወዳዶችን ሐዘን፤ ስጋት ማናሩ፤ ሐማኖተኞችን ለፆም ፀሎት፤ ለጋሾችን ለርዳታ ማሳደሙ ተነግሮ ሳበያቃ፤ እስራኤል-ፍልስጤሞች የዓለምን ሟች፤ቁስለኛ ስደተኛ ቁጥርንለመጨመር እንደኖሩበት ይገዳደሉ ገቡ።

Großbritannien Schottland Unabhängigkeitsreferendum Reaktionen No Alistair Darling
ምስል P. Macdiarmid/AFP/Getty Images

ሰኔ 30 እስራኤል በሐይል በያዘችዉ የፍልስጤም ግዛት ምዕራባዊ ዮርዳኖስ ወንዝ ዳርቻ ዉስጥ ከሳምንት በፊት ታግተዉ የነበሩ የ3 እስራኤላዊ ወጣቶች አስከሬንን ማግኘቱን የእስራኤል ጦር አስታወቀ።የእስራኤል ባለስልጣናት አጋች ገዳዮች የፍልስጤም ደፈጣ ተዋጊዎች መሆናቸዉን ለማስታወቅ-መመርመር፤መረጃ መሰብሰብአላስፈለጋቸዉም።ለብቀላ ለመዛትምየሟቾቹ አስከሬን እስኪገኝ አልጠበቁም።

የወትሮ ጥላቻቸዉ በመሪዎቻቸዉ ቅስቀሳ የናረባቸዉ የእየሩሳሌም አክራሪ የሁዲዎች ለብቃላ መሪዎቹን አልጠበቁም።የሰወስቱ እስራኤላዉያን ወጣቶች አስከሬን መገኘቱ በተነገረ በማግስቱ አንድ ፍልስጤማዊ ወጣት ገድለዉ አስከሬኑን አነደዱት።

የየሁዲ፤የክርስትና የሙስሊሟ ቅድስት ከተማ በየሁዲ-አረቦች ጠብ ግጭት ስትተራመስ፤ ጋዛ በእስራኤል ጦር ቦምብ፤ሚሳዬል፤ ታንክ መድፍ አረር ትንፈቀፈቅ ያዘች፤ ደቡባዊ እስራኤል በሐማስ ሮኬት ትቦጫጨር ገባች።ሐምሌ ስምንት።

የዓለም ምርጥ ጦር ለበርካታ ዓመታት የከበባትን ጋዛን ማዉደም፤ማጥፋቱን ነዋሪዋን መፍጀት፤ማቁሰል፤ ማፈናቀሉ ያስቆጣቸዉ ፍልስጤሞችና ደጋፊዎቻቸዉ ከረመላሕ እስከ ቤይሩት፤ ከብራስልስ እስከ ኒዮርክ አደባባይ ወጥተዉ የእስራኤልን እርምጃ ሲያወግዙ፤ አሜሪካና አዉሮጳ የሚኖሩ የሁዲዎች ባንፃሩ አዉጋዢዉን ሠልፈኛ በሠልፍ አዉግዘዋል።

አንዳድ ደካማ መንግሥታትና ድርጅቶች የእስኤልን ጦር ጥቃት «ያልተመጣጠነ» በማለት ሲያወግዙት፤ ሐማስን እንደ እስራኤል ሁሉ በአሸባሪነት የሚወነጅሉት የዩናይትድ ስቴትስና የምዕራብ አዉሮጳ መንግሥታትን ጨምሮ በርካታ መንግስታት ጦርነቱ እንዲቆም ጠይቀዉ ነበር።የእስራኤል መሪዎች የሐያላኑ ጥያቄ ካንገት እንጂ ካንጀት እንዳልሆነ፤ የደካሞቹ ዉግዘት የሚያመጣዉ ለዉጥ እንደሌለ ያዉቁታል።እና ጦርነቱ ይቀጥላል አሉ፤ ጠቅላይ ሚንስትር ቤንያሚን ኔታንያሁሐምሌ 28።

Malecon von Havanna, Kuba
ምስል Fotolia/kmiragaya

«ጋዛ ዉስጥ ለረጅም ጊዜ ለሚደረግ ወታደራዊ ዘመቻ መዘጋጀት አለብን።ተልዕኳችንን እስክናጠናቅቅ ድረስ ሐላፊነት በተሞላበት መንገድ ጠንከርን እርምጃ መዉሰዳችንን እንቀጥላለን።ከፊታችን አስቸጋሪ ቀናት እንደሚጠብቁን እናዉቃለን።ይሕ አስቸጋሪና አሳማሚ ቀን ነዉ።እኛን ማጥፋት በሚሻዉ በገዳይ አሸባሪ ድርጅት ላይ የጀመርነዉን እርምጃ ለመቀጠል ትዕግስትና ቁርጠኝነት ሊኖረን ይገባል።»

ጦርነቱን ጋዛ፣በነዋሪዎችዋ ደም አጥንትየቦካ ድንጋይ ጭቃ ከምርነት እስክትቀየር፤ ደቡባዊ እስራኤል በማስጠንቂያ ድምፅ እስኪተራመስ ድረስ ሰባት ሳምንት አሉት፤ አሉትና ሲደክማቸዉ አቆሙት።ነሐሴ-ማብቂያ።ፍልስጤም 2200 ተገደለ።በብዙ ሺሕ የሚቆጠሩ አካላቸዉ ጎደለ።አብዛኞቹ ሰላማዊ ሰዎች ናቸዉ።በቢሊዮን ዶላር የሚገመት ሐብት ንብረት ወደመ።እስራኤል ከሰባ በላይ ተገደለባት።ብዙ ቆሰለባት።አብዛኛዉ ወታደር ነዉ።

ጋዛ ላይ አስከሬን ሲቆጥር ከወደ ምስራቅ ዩክሬን ሌላ መርዶ ሰማ።298 ሰዎችን አሳፍሮ ከአምስተርዳም-ኔዘርላንድ ወደ ኳላ ላፑር -ማሌዢያ ይበር የነበረዉ የማሌዢያ የመንገደኞች አዉሮፕላንን አየር ላይ ጋየ።ሐምሌ 17።

Friedensnobelpreis Verleihung Malala und Satyarthi 10.12.2014 Oslo
ምስል Reuters/NTB Scanpix/C. Poppe

«እቤቴ ነበርኩ።ድንገትእስገምጋቢ ድምፅ ሰማሁ።ወዲያዉ ሁለት ፍንዳታዎች።ስወጣ ጥቁር ጢስ፤ ጠለስ ሲትጎለጎል አየሁ።» ይላሉ- ጥፋት እልቂቱን ያዩ ።የተረፈ ተሳፋሪ የለም።ሌዢያ፣ መጋቢት ላይ ከነመንገደኞቹ ደብዛዉ የጠፋዉ አዉሮፕላንዋ-ሳይገኝ ሁለተኛዉ ጋየባት።በርካታ ሐገራት ዜጎቻቸዉን ባንድ አየር መንገድ አዉሮፕላን አደጋ ለሁለተኛ ጊዜ አጡ።ዓመቱ ለትንሺቱ፤ ለፈጣን እድገት አብነቲቱ ሐገር በርግጥ ፈሪሰኛ ነዉ።ሰሞኑን ደግሞ ጎርፍ በአስር የሚቆጠሩ ዜጎቿን ገድሎ፤ በመቶ ሺሕ የሚቆጠሩ አፈናቅሎባትል።ዓመቱን ልትገላገለዉ-መሆኑ በጀ።

የአዉሮፕላኑመጋየት ግን ወትሮም ቅጥ ያጣዉን የዩክሬንና በዩክሬን ሰበብ የሚወዛገቡትን ሐያላን ጠብ ለማቀጣጠል ተጨማሪ ቤንዚን ሆናል።አዉሮፕላኑን የዩክሬን መንግሥት ጦር አለያም አማፂያኑ መትተዉታል መባሉ የኪየቭ-አማፂኑን ዉጊያ-መወነጃጀል አጋግሞ፤ የሞስኮ እና የዋሽግተን ብራስልስ ሐያላንን ዉዝግብ፤የማዕቀብ እርምጃዉ እንዳጦዘዉ፤ 2014 ዉጊያ መወነጃጀሉን ለ2015 ሊያስረክብ ነዉ።

የዓለም ብቸኛ ልዕለ ሐያል ሐገር ዩናይትድ ስቴትስ የጥቁር-ነጭ ክልስ ፖለቲከኛ ለፕሬዝዳትነት ከተመረጠባት ወዲሕ ለዘመናት የኖረችበት የዘር፤ ቀለም ልዩነት የሚነዳዉ ጠብ ቁርቁስ የማሳረጉ አብይ አብነት ተደርጎ ሲነገር-ሲተረክባት ነበር።ነሐሴ 9 የፈርግሰን-ሚዙሪዉ ነጭ ፖሊስ ያልታጠቀ ጥቁር ወጣትንበጥይት ደብድቦ የመግደሉ ግፍ እና መዘዙ፤የመዘዘዉ ሐቅ ግን የተነገረ-የተተረከዉ ሁሉ ሐሰት፤ ዉሸትነቱን አስመሰከረ።

Bergung der Wrackteile von Flug MH17 in der Ostukraine 16.11.2014
ምስል Reuters/Maxim Zmeyev

የ18 ዓመቱ ጥቁር ወጣት ማይክል ብራዉን በነጭ ፖሊስ መገደሉ አልበቃ ያለ ይመስል ገዳይ አለመያዙ የቆየ በደሉን የቀሰቀሰበት ጥቁር አሜሪካዊ ድፍን አሜሪካን በአደባባይ ሰልፍ ሲነዉጣት፤ ፈርግሰንን ሲያነድ፤ሲያወድም፤ ሲመዘብራት አስር ቀን አስቆጠረ።

የፍትሕ ጥያቄ፤ ሠልፍ፤ጩኸት፤ዉድመቱ የልዕለ ሐያሊቱን ነባር የዘር መርሕ ለመለወጥ አቅም አልነበረዉም።የግድያዉን ምክንያት ሲመረምር የከረመዉ ነጮች የበዙበት ፍርድ ሸንጎ ሕዳር ማብቂያ ገዳዩን በነፃ አሰናበተ።ሌላ አድልዎ፤ ሌላ ቁጣ፤ ሌላ አመፅ-«ፍትሕ ከሌለ ሠላም የለም» ይል ገባ አሜሪካዊዉ ጥቁር።

Amsterdam Gedenken an Opfer der MH 17 10.11.2014
ምስል Reuters/Frank van Beek/Pool

ከእስያ-እስከ አፍሪቃ፤ከአዉሮጳ እስከ አሜሪካ የዓለምን ባሕል፤ፖለቲካዊ ሥርዓት፤የሐገራትን ድንበር ስታፈርስ- ስትገነባ ምዕተ-ዓመታት ያስቆጠረችዉ ታላቅዋ ብሪታንያ የራስዋን ፖለቲካዊ አስተዳደር፤ መልዕከ ምድራዊ ድንበር የማወነካከሯ ጣጣ በይፋ የፈጋዉ ዘንድሮ ነበር።

ዉስጥ ዉስጡን ሲብላላ ሰወስት መቶ ዓመታት ያስቆጠረዉ የስኮትላንዶች የነፃነት ጥያቄ ጣራ ነክቶ መስከረም 18 በተደረገዉ ሕዝበ ዉሳኔ-ከብሪታንያ ጋር አንድነትን የሚመርጠዉ ሕዝብ በ55 ከመቶ አብላጫ ድምፅ የበላይነትን አግኝቶ የመገንጠል ጥያቄዉ ለጊዜዉም ቢሆን ተዳፈነ።ለጥቅላይ ሚኒስትር ዴቪድ ካምሩን በርግጥ ደስታ- እፎታም ነበር።

«የስኮትላንድ ሕዝብ ተናገረ።መልክቱም ግልፅ ዉጤት ነዉ።አራት ብሔሮች ያሏት ሐገራችንን አንድነት አስጠብቀዋል።እንደ ሌሎች ሚሊዮኖች ሰዎች ሁሉ ተደስቻለሁ።በሕዝበ-ዉሳኔዉ ዘመቻ ወቅት እንዳልኩት ታላቅዋ ብሪታኒያ ስትፈፀም ማየት ልቤን በሰበረዉ ነበር።»

ኢትዮጵያዉያን አዲስ ዓመት ባሉ በሳምንቱ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት 69ኛ ጠቅላላ ጉባኤ ኒዮርክ ተሰየመ።ዋና ፀሐፊ ፓን ጊሙን ለጉባኤተኞች ያስተላለፉት መልዕክት የዓለምን እዉነታ ገላጭ ነበር።

«በየዓመቱ በዚሕ ወቅት ይሕ አዳራሽ በተስፋ ይሞላል።በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መተዳደሪያ ደንብ በተካተተዉ ተስፋ፤ከዚሕ መድረክ በሚናገሩ መሪዎች ተስፋ፤ እና መሪዎቹ የሚገቡትን ቃል በሚሰማዉ የዓለም ሕዝብ ተስፋ።ዘንድሮ የተስፋ አድማፅ በጨለማ ተዉጧል።በንፁሐን ሞት ልባችን ቃላት በማይገልፀዉ ሐዘን ተሞልቷል።የቀዝቃዛዉ ጦርነት ጣረ-መንፈስ ዘመናችንን እያነፈነፈዉ ነዉ።»

ጉባኤተኞች፤ የሐያላኑ መንግሥታትን ዉዝግብ፤ አሸባሪ ዎችን የመዉጋት ዛቻ፤ የእስራኤል ፍልስጤም መሪዎችን እስጥ አገባ፤የኢቦላን አደገኝነትን የሚገልፁ ንግግሮችን አሰሙና ወደየመጡበት ተመለሱ።

New York Gedenkplakat Eric Garner Michael Brown
ምስል Spencer Platt/Getty Images

መስከረም 26 አደንዛዥ ነጋዴዎች ያገቷቸዉን 43 የሜክሲኮ ተማሪዎች በጅምላ መረሸናቸዉ ተሰማ።ወንጀሉ የተማሪዎችን ወላጅ፤ወዳጅ፤ ዘመድ-አስተማሪዎችን በሐዘን እራሮት ሲያንገበግብ፤ የሜክሲኮ አደባባዮችን በተቃዉሞ ሰልፍ አጥለቅልቆ ነበር።ዉሎ ሲያድር የፖሊስ ባልደረቦች ከአጋች፤ ገዳዮች ጋር ተባብረዋል መባሉ እና የሐገሪቱ መንግሥት ፈጣን እርምጃ አለምወሰዱ የማዕከላዊ አሜሪካዊቱን ሐገር ፖለቲካ አመሰቃሎት ዓመቱ አበቃ።

መስከረም 29፤ በአፍቃኒስታኑ ሁለተኛ ዙር ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ አሜሪካ የተማሩ፤ አሜሪካ ይሰሩ የነበሩት ፖለቲከኛ አሽረፍ ጋኒ ማሸነፋቸዉ ታወጀ።የአዲሱ ፕሬዝዳንት የመጀመሪያ ሥራ የቀድሞ አለቃቸዉ ፕሬዝዳንት ሐሚድ ካርዛይ እንቢኝ ያሉትን ዉል ከአሜሪካኖች ጋር፤ አሜሪካኖች በፈለጉት መንገድ መፈራረም ነበር።

ዉሉ የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃል ኪዳን ድርጅት ጦር ከአፍቃኒስታን በይፋ ለቅቆ ከወጣ በኋላ 12 500 የዉጪ ወታደሮች እዚያዉ አፍቃኒስታን እንደሰፈሩ እንዲቆዩ፤ ወታደሮቹ ቢያጠፉ አፍቃኒስታን ዉስጥ በአፍቃኒስታን ሕግ እንዳይዳኙ የሚያስገድድ ነዉ።አዲሱ ፕሬዝዳንት መመረጣቸዉ የተነገረ ዕለት ፈረሙ።

ከዋና ተቀናቃኛቸዉ ከአብዱላሕ አብዱላሕ ጋር የገጠሙት እስጥ አገባ ግን በአሜሪካኖች ጫና፤ ሥልጣን በማጋራት ሥምምነት እስኪቋጭ ድረስ በተከታታይ መደራደር፤መነጋገር፤ አንዳዴም መዘላለፍ፤ መመሳጠርም ነበረባቸዉ።

አፍቃኒስታን ዉስጥ ላለፉት አስራ-ሰወስት ዓመት ከታሊባን እና ከአልቃኢዳ ጋር የተዋጋዉ አሜሪካ መራሽ ጦር በአመቱ የመጨረሻ ቀን ተጠቃልሎ ይወጣል።ከነገ-ወዲያ ሮብ።ጦሩ በአስራ-ሰወስት ዓመቱ ዉጊያ የማሸነፍ-መሸነፉ ዉዝግብ ግን የፖለቲካ ተንታኞች ርዕስ-እንደሆነ ይቀጥላል።የአፍቃኒስታን ጦርነት-ግጭትም እንዲሁም።

ጥቅምት 10።ታሊባኖችን በመቃወሟ-በጥይት የተደበደበችዉ ፓኪስታናዊት ወጣት ማላላ ዩሳፍዛይ፤ ከሕንዳዊዉ የልጆች መብት ተሟጋች ከካይላሽ ሳትያርቲ ጋር የዘንድሮዉን ኖቤል የሠላም ሽልማት ማሸነፋቸዉ ታወጀ።በወሩ ሽልማቱን ተቀበሉ።

የኖርዌዉ የኖቤል ኮሚቴ ሊቀመንበር ቶርቢዮርት ያግላንድ።ማላላ በኖቤል ሽልማት ታሪክ ወጣትዋ ተሸላሚ ናት።17 ዓመቷ።ዓመቱም ዝናዋ እንደናኝበት-አበቃ።ለትዉልድ ሐገሯ ፓኪስታን ግን ከቀዳሚዎቹ ዓመታት የከፋ እንጂ የተሻለ አልነበረም።በተላይ ታሕሳስ 16 ለፓኪስታን በጣሙን ለፔሻወር ነዋሪዎች የሐዘን-ሰቀቀን ዕለት ነበር።የታሊባን ታጣቂዎች የወታደሮች ልጆች የሚማሩበትን ትምሕርት ቤት ወርረዉ ተማሪ አስተማሪዎችን ረሸኑ።132-ተማሪዎች፤ ዘጠኝ አስተማሪና ሠራተኞች እንደወጡ ቀሩ።

BdT Deutschland Demonstration vor US-amerikanischer Botschaft
ምስል picture-alliance/dpa/R. Jensen

ከፓኪስታን ጋር ሕንድ ለምትለያቸዉ ለብርድ፤በረዶ፤ የተራራማይቱ ሐገር ኔፓልም ዘንድሮ-ጥሩ ብዙም አልታየባትም።በበረዶ ማዕበል እንደቆረፈደች-ጥቅምት 14 ታላቁን እልቂት አስተናገደች።በረዶ ባንድ ቀን ብቻ 43 ሰወስት ገደለባት።

ለኩባ-አሜሪካኖች ግን ዓመቱ በርግጥ የሠላም፤መልካም ግንኙነት ተስፋ የፈነጠቀበት፤ ሥልሳ-ዘመን የዘለቀዉ ጠብ፤ ቁርቁስ የመወገዱ ምልክት የተንፀባረቀበት ነዉ።ታሕሳስ 17።ፕሬዝዳንት ባራክ ኦቦማ በኩባ (ስጳኞቹ) ቋንቋ አበሰሩ።«ሁላችንም አሜሪካኖች ነን» ብለዉ።

የዩናይትድ ስቴትስን በተለይም የፕሬዝዳንት ኦባማን ዉሳኔ-አንዳድ የአሜሪካ ፖለቲከኞች በጣሙን የኩባ ዝርያ ያላቸዉ ተቃዋሚ ፖለቲከኞች ማዉገዛቸዉ አልቀረም።

ይሁን እንጂ የግንኙነቱን መሻሻል ከሐቫና እስከ ዋሽግተን፤ ከቦኒስ አይሪስ እስከ ሜክሲኮ የሚኖረዉ ሕዝብ፤ በፌስታ ተቀብሎታል።ከቤጂንግ እስከ ብራስል ያሉ ፖለቲከኞች፤ የቫቲክ የሐይማኖት መሪዎች አድንቀዉ-ደግፈዉታል።

ለግንኙነቱ መሻሻል የሮማ ካቶሊካዊት ርዕሠ ሊቃነጳጳሳት ፍራንሲስ ሽምግልና የካናዳና የአዉሮጳ ሕብረት ጥረት ትልቅ አስተዋፅኦ ማበርከቱ ተመስክሯል።

ከተመሰከረለት ሽምግልና፤ ጥረት ፍላጎት ጀርባ ዩናይትድ ስቴትስና የአዉሮጳ ተባባሪዎችዋ ከሩሲያ ጋር የገጠሙት እስጥ አገባ፤ ሁለቱንም የጠላቶቻቸዉን ቁጥር ለመቀነስ፤ ወይም ወዳጆቻቸዉን ለማብዛት የገጠሙት ሽሚያ ዉጤት መሆኑ ለፖለቲካ አነፍናፊዎች አልተሰወረም።

መጋቢት መጀመሪያ በአዉሮፕላን መሰወር የጀመረዉ 2014 በአዉሮፕላን አደጋ ለማሳረግ ያደባ ይመስላል።ትናንት። ኤር ኤዥያ የተሰኘዉ የኢንዶኔዢያ አየር መንገድ ንብረት የሆነዉ ኤር ባስ 320-200 አዉሮፕላን ከነመንገደኞቹ የገባበት ጠፋ።162 ሰዎችን አሳፍሮ ነበር።ግሪክ ባሕር ጠረፍ የጋየችዉ መርከብ ግን ከአምስቱ በስተቀር አብዛኛ ተሳፋሪዎቿ ከሞት አምልጠዋል።2014 ስልሳ ጋዜጠኞች የተገደሉበትም ነዉ። አምና ሊሆን -ሁለት ቀን ቀረዉ።

በቀመሩ ለምታሰሉ መልካም አዲስ ዓመት።

ነጋሽ መሐመድ

አዜብ ታደሰ