1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የዓለም ንግድ ድርጅት ድርድርና የድሆች አገሮች ዕጣ

ረቡዕ፣ ጥቅምት 30 1998
https://p.dw.com/p/E0eA

በሆንግኮንጉ የድርድር ዙር ዕርምጃ የመታየቱ ተሥፋ እስከምን ነው? የድርጅቱ ጥረት ከሁለት ዓመታት በፊት ሜክሢኮ-ካንኩን ላይ እንደታየው ዕጣው ምናልባት መክሸፍ ይሆን? በወቅቱ በመካሄድ ላይ የሚገኙት የዓለም ንግድ ድርጅት ድርድሮች ድሃውን ሕዝብ ይበልጥ ድሃ ሊያደርጉ ይችላሉ የሚል ስጋት ያደረባቸው ጥቂቶች አይደሉም።

በጥምረት የሚታገሉ በርካታ ከመንግሥት ነጻ የሆኑ ድርጅቶች የአውሮፓ ሕብረት እስካሁን ያቀረበውን የመፍትሄ ሃሣብ በቂ አይደለም ሲሉ ተችተዋል። በኢንዱስትሪ ልማት የበለጸጉት ሃብታም መንግሥታት የዓለም ንግድ ደምቦችን በማለዘብ ድህነትንም መታገል ይቻላል፤ እንደታቀደው የቀረጥ መሰናክሎችን በሁሉም ወገን ማስወገድ ከተቻለም የድሃ-ድሃ ለሚባሉት አገሮች ጭምር ይበልጥ ዕድል ከፋች ነው የሚሆነው ሲሉ ለሚሰነዝሩት አቋም ጨርሶ አመኔታ የላቸውም።

ሰሞኑን በብራስልስ ተሰብስበው የሚገኙት ከመንግሥት ነጻ የሆኑት ድርጅቶች ተጠሪዎች በዚህ ዓይነት አመለካከት ፍትሃዊ የዓለም ንግድን ለማስፈን አይቻልም ባዮች ናቸው። ከተጠሪዎቹ ልዑካን አንዱ ደቡብ አፍሪቃዊው ኩሚ ናይዱ አውሮፓውያንም ፍትሃዊ ለሆነች ዓለም የጠነከረ ፍላጎት የላቸውም ሲሉ ነው የወቀሱት። ናይዱ እንዳሉት የአውሮፓ ሕብረት በየቀኑ ለእያንዳንዷ ላም ሁለት ኤውሮ ወጪ ያደርጋል። በሌላ በኩል ግን ከግማሽ የሚበልጠው የዓለም ሕዝብ ኑሮውን ከዚያ ባነሰ ዕለታዊ ገቢ መግፋት ግድ እንደሆነበት ሊታሰብ ይገባዋል።

ኩሚ ናይዱ “ዓለምአቀፍ ድህነትን የመታገል ጥሪ” የተሰኘ ቡድን አፈ-ቀላጤ ሲሆኑ ኦክስፋምንና “Friends of the Earth” የተሰኘውን ከመሳሰሉት ከሌሎች ከመንግሥት ነጻ የሆኑ ድርጅቶች ጋር በወቅቱ በዓለም የንግድ ድርድር አኳያ የተያዘውን ጥረት በዓይነ-ቁራኛ የሚከታተሉ ናቸው። የድርድሩ ዙር ብርቱ የጊዜ ግፊት በሰፈነበት ሁኔታ ለዓለም ንግድ ድርጅት አንድ ስምምነት ለማርቀቅ በመጣር ላይ ይገኛል። ይሄው ረቂቅ በፊታችን ታሕሣስ ወር የመጀመሪያ አጋማሽ ሆንግ ኮንግ ላይ በሚካሄደው የዓለም ንግድ ድርጅት የሚኒስትሮች ስብሰባ እንዲጸድቅ የታቀደ ሲሆን ዛሬና በሚቀጥሉት ቀናት የሚካሄዱት ንግግሮች ወሣኝነት እንደሚኖራችው ነው የሚጠበቀው።

ድርድሩ በጥቅሉ የቀረጥ መሰናክሎችን በማስወገዱና የውጭ ንግድ ድጎማን በማስቀረቱ ጉዳይ፤ እንዲሁም ለኢንዱስትሪ ምርቶችና አገልግሎቶች የገበዮችን መከፈት የሚመለከት ነው። በወቅቱ ዋና አከራካሪ ጉዳይ ሆኖ የሚገኘው አውሮፓና አሜሪካ የቀረጥ ተመናቸውን ዝቅ በማድረግ የእርሻ ገበዮቻቸውን የሚከፍቱበት መጠንና ሂደት ሁኔታ ነው። እርግጥ በአንጻሩ ታዳጊ አገሮችም በኢንዱስትሪ ልማት ለበለጸጉት መንግሥታት ምርቶችና አገልግሎቶች ገበዮቻቸውን መክፈታቸው ቅድመ-ግዴታ ሆኖ ነው የተቀመጠው።

ይሁንና የኦክስፋም ባልደረባ ሉዊስ ሞራጎ ለውጭ ንግድ የሚደረገው ድጎማ በታዳጊው ዓለም የእርሻ ምርቶች ላይ የዋጋ መጣጣልን እንደሚያስከትል በማመልከት አሜሪካና የአውሮፓ ሕብረት አስፈላጊውን ፍትሃዊ መፍትሄ ለማስፈን ቁርጠኛ አለመሆናቸውን ተናግረዋል። ሞራጎ እንደሚሉት እስካሁን በጉዳዩ አንዳች ዕርምጃ አልተደረገም፤ ምዕራባውያኑ መንግሥታት የውጭ የእርሻ ንግድ ድጎማቸውን ለማቆም ያስቀመጡት ቀነ ቀጠሮም የለም። ከዚህ በተጨማሪ ፈረንሣይ በአውሮፓ ሕብረት ውስጥ መሰናክል መፍጠሯን እንደቀጠለች ነው። በአጭር ጊዜ የጋራ መፍትሄ መስፈን መቻሉ በጣሙን ያጠያይቃል።

ከመንግሥት ነጻ በሆኑት ድርጅቶች አመለካከት ሃብታሞቹ አምራች አገሮች በእርሻው ዘርፍ አንዳች ነገር አሳልፈው ለመስጠት ፍላጎት የላቸውም። በሌላ በኩል ግን የታዳጊውን ዓለም ገበዮች የምርቶቻቸው ማራገፊያ ማድረጉን ይሻሉ። ይህ ደግሞ ጥገኝነትን የሚያጠነክር ከመሆኑ የተነሣ ድሆች አገሮች የራሳቸውን መዋቅራዊ ዕድገት እንዳያደርጉ መሰናክል ነው የሚሆነው። ከመንግሥት ነጻ የሆኑት ድርጅቶች ስብስብ በወቅቱ ለአቋም ለውጥ ግፊት ለማድረግ በብራስልስ በመጣር ላይ ይገኛል። ጥሪው በፊታችን ታሕሣስ ከሚገኝ ጎጂ ስምምነት ስምምነት አለመስፈኑ ይመረጣል የሚል ነው።