1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የዓለም ንግድ ድርጅት ስብሰባ በጀኔቫ

ማክሰኞ፣ ጥቅምት 15 1998

ጀኔቫ ላይ የሚካሄደው የዓለም ንግድ ድርጅት ስብሰባ የአውሮፓው ሕብረት፣ አሜሪካና G-20 በመባል የሚጠሩት በመልማት ላይ የሚገኙ አገሮች አሁን ንግግሩን በመቀላቀላቸው ድርድሩ ወሣኝ ወደሆነ አዲስ ደረጃ መሸጋገሩ ተነግሯል።

https://p.dw.com/p/E0eG
በመልማት ላይ ያሉት አገሮች አከራካሪ የሆኑትን የእርሻ ነክ ድርድር ችግሮች ለማቃለል በዚህ ሣምንት የራሳቸውን ጭብጥ መረጃዎች እንደሚያቀርቡ ትናንት አስታውቀው ነበር። ይህ ችግር የዓለም ንግድ ድርጅት የንግድ ደምቦችን ለማለዘብ ከዶሃ ጀምሮ ለአራት ዓመታት ሲያካሂድ ለቆየው ድርድር መሰናክል ሆኖ ነው የኖረው።

G-20 በመባል የሚጠራው ቡድን ቻይናን፣ ሕንድን፣ ብራዚልን፣ ናይጄሪያንና ደቡብ አፍሪቃን የመሳሰሉትን ቀደምት የታዳጊውን ዓለም አገሮች ጭምር የሚጠቀልል የመንግሥታት ስብስብ ነው። ከሕንድ የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትር ካማል ናት ጋር በመሆን ተግባሩን የሚያቀናብሩት የብራዚል ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሤሌሶ አሞሪም ቡድኑ የሚያቀርባቸው አሃዝ-አዘል መረጃዎች በሣምንቱ ከአሜሪካና ከአውሮፓ ሕብረት በኩል ለተሰነዘሩት ሃሣቦች ምላሽ እንደሚሆን ገልጸዋል። አሞሪም እንደተናገሩት ውይይ እስካሁን በመዋቅራዊ ጉዳዮች ላይ አተኩሮ ነው የቆየው። አሁን ግን የዓለምአቀፉ ንግድ ዋነኛ ተሳታፊዎች በዚሁ ላይ በመመስረት ጭብጥ አሃዞችን ወደማቅረቡ ደረጃ ለመሻገር ተስማምተዋል።

የዓለም ንግድ ድርጅትን የእርሻ ውል ለመጠገን በ 2000 ዓ.ም. ጥረት ከተጀመረ ወዲህና የዶሃ ድርድር ከተከፈተ ከሁለት ዓመታት ገደማ በኋላ የንግድ ድርጅቱ 148 ዓባል መንግሥታት ጭብጥ አሃዞች ላይ ሲደራደሩ የአሁኑ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው። አሜሪካ በትናንትናው ዕለት ወደ አገር በምታስገባቸው ምርቶች ላይ የምታስከፍለውን ቀረጥ በ 55 እና በ 90 በመቶ መካከል በሚንሸራሸር መጠን ለመቀነስ ፈቃደኛ ነኝ ብላለች። ለገበሬዎቿ የምትሰጠውን ድጎማም 80 በመቶ ለመቆረጥ እንዲሁ! ግን ይህን የምታደርገው የአውሮፓ ሕብረትና ጃፓን በወቅቱ ከፍተኛ ነው ብላ የምትገምተውን የየራሳቸውን ድርሻ ከቀነሱ ብቻ ነው።

የአውሮፓ ሕብረት በበኩሉ ከውጭ፤ ማለት ከታዳጊው ዓለም በሚገቡ የምግብ ምርቶች ላይ የጣለውን ቀረጥ በግማሽ ለመቀነስና የገበሬዎቹን ድጎማ ደግሞ 70 በመቶ ለመቁረጥ ነው ዝግጁ የሆነው። G-20 አገሮች በፊናቸው ቀረጥ ቅነሣውን በተለያዩ ደረጃዎች፤ መለስተኛና ዓቢይ ጉዳዮች ብለው በመከፋፈል የራሳቸውን ሃሣብ ያቀረቡት ገና ባለፈው ሐምሌ ወር ነበር። የተለያዩት ሃሣቦች በያዝነውና በተከታዩ ሣምንት በንግድ ድርጅቱ መቀመጫ በጀኔቫ በተያዘው ንግግር ዓቢይ ማተኮሪያዎች ናቸው።

በእርሻው ንግድ ጉዳይ ከአንድ ስምምነት ለመድረስ የተጣለው የጊዜ ገደብ የሚያበቃው በፊታችን ታሕሳስ ወር የሚካሄደው የንግድ ድርጅቱ የሚኒስትሮች ጉባዔ በሚጠቃለልበት ጊዜ ቢሆንም በመጪዎቹ ሁለት ሣምንታት አንዳንድ ጭብጥ ውጤቶች ሊከሰቱ እንደሚችሉ የብራዚሉ ባለሥልጣን የሤልሶ አሞሪም ዕምነት ነው። በሌላ በኩል የዓለም ንግድ ድርጅት ዓባል ሃገራት በዶሃው የድርድር ዙር ሁለንተናዊ ዓለምአቀፍ ውል ለማስፈን ገና እስከሚቀጥለው ዓመት መጨረሻ ጊዜ አላቸው። ካታር ርዕሰ-ከተማ ዶሃ ላይ በ 2001 ዓ.ም. የጀመረው የድርድር ዙር ከእርሻ ባሻገር የገልግሎቱን ዘርፍ፣ የኢንዱስትሪ ቀረጥንና ሌሎች ልማት ነክ ጉዳዮችን ጭምር የሚጠቀልል መሆኑ ይታወቃል።

በወቅቱ የጀኔቫ ድርድር አሜሪካ ያቀረበችውን ሃሣብ ሃያው ታዳጊ አገሮች ጠቃሚ ዕርምጃ ቢሆንም በቂ አይደለም ብለውታል። ቻይናንና ሕንድን የመሳሰሉትን የተፋጠነ ዕድገት በማድረግ ላይ የሚገኙ መንግሥታትን የጠቀለለው የብዙ አገሮችን ጥቅም የሚያራምድ ስብስብ ከተቋቋመ ከሁለት ዓመታት ወዲህ ክብደት እያገኛ መምጣቱ አልቀረም። ስለዚህም ግፊቱ የአውሮፓ ሕብረት ገበዮቹን በመክፈቱ በኩል ያቀረበውን ሃሣብ እንዲያሻሽል ማስገደዱ እንደማይቀር ሚኒስትሮቹ ተሥፋ ጥለዋል።
ዓለምአቀፉ የልማት ድርጅት ኦክስፋም እንደሚለው አሁን የአውሮፓ ሕብረት አስታራቂ ብሎ ያቀረበው ሃሣብ ለድሆች አገሮች አንዳች ጥቅምን የሚያስከትል አይደለም። ሕብረቱ ሚዛናዊ ዕርምጃ ያስፈልጋል ባይ ቢሆንም ታዳጊ አገሮችን ብዙ የሚጋፋ ሆኖ ነው በድርጅቱ የታየው። የዓለምአቀፉን ድርጅት “ንግድ ፍትሃዊ ይሁን” የሚል ዘመቻ በሚመሩት በሤሊን ቻርቬሪዬ አመለካከት የአውሮፓ ሕብረትም ሆነ አሜሪካ የሚያቀርቡት ሃሣብ ክፍያን ከአንዱ ወደላሌው በማሸጋሸግ ብቻ የተወሰነ ነው። ስለዚህም የዚሁ ድርጊት ተጎጂዎች የድሆች አገሮች አርሶ-አደሮች እንዳይሆኑ ነው የሚሰጉት።