1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የዓለም ንግድ አዝማሚያ ከዶሃው ዙር ክሽፈት በኋላ

ሐሙስ፣ ሐምሌ 20 1998

የዓለም ንግድ ድርጅት የዶሃ የድርድር ዙር ጨርሶ መክሸፉ ይሁን ወይም ለረጅም ጊዜ መቋረጡ ለጊዜው በውል የለየለት ነገር አይደለም። ይህ ከሰሞኑ የጀኔቫ ንግግር ክሽፈት በኋላ የሚታየው የወቅቱ ሃቅ ሲሆን በሌላ በኩል ታላላቆቹ መንግሥታት ወደፊት በሁለት ወገን፤ ማለት ባይላተራል የንግድ ውሎች ላይ ይበልጥ እንደሚያተኩሩ ከአሁኑ እርግጠኛ ሆኗል።

https://p.dw.com/p/E0df
የዓለም ንግድ ድርጅት መሰብሰቢያ በጀኔቫ
የዓለም ንግድ ድርጅት መሰብሰቢያ በጀኔቫምስል AP

የዶሃው ዙር ተቋርጦ የሚቆይበት ጊዜ በረዘመ ቁጥር እንደገና መቀጠሉ ከናካቴው ግልጽ እስካልሆነ ድረስ የበለጸጉት መንግሥታት ይበልጡን በሁለት ወገን ወይም በአካባቢ የነጻ ንግድ ውል ፍለጋ መድህናቸውን እንደሚሹ ግልጽ ነው። የዚህ አዝማሚያ ተጎጂዎች ደግሞ ድሆች አገሮች ይሆናሉ። በወቅቱ በዚህ መልክ ሁለት መንግሥታት ወይም የተሳሰሩ የመንግሥታት ቡድኖች እርስበርሳቸው ገበዮች የሚጋሩባቸውና የቀረጥ ቅነሣ አስተያየት የሚያደርጉባቸው የጸኑ ውሎች ከሁለት መቶ ይበልጣሉ። ተጨማሪ ዘጠና የነጻ ንግድ ውሎች ደግሞ ተፈርመዋል ወይም በቅንጅት ላይ ናቸው።

ጊዜው በጣም ነው የተለወጠው። በዘጠናናዎቹ ዓመታት መጀመሪያ በዓለም ንግድ ድርጅት ቀደምት በአሕጽሮት GATT በመባል በሚታወቀው አጠቃላይ የቀረጥና የንግድ ውል የተፈረሙት የሁለት ወገን ወይም የአካባቢ ስምምነቶች ከ 31አይበልጡም ነበር። በሰባኛዎቹ ዓመታት እንዲያውም ስድሥት ብቻ ነበሩ። በዓለም ላይ በተለይ በቀደምትነት ከተናጠል መንግሥታትና አካባቢዎች ጋር የነጻ ንግድ ግንኙነቷን ለማጠናከር የምትጥረው ዩ.ኤስ.አሜሪካ ናት። ይህን መሰሉ ዘዴ ለአሜሪካ በዓለም ንግድ ድርጅት አኳያ እንደ አማራጭና እንደ ተጽዕኖ መሣሪያነትም እያደገ መምጣቱ አልቀረም።

ዩ.ኤስ.አሜሪካ በዓለም ንግድ ድርጅት ውስጥ ከምትፈልገው ግብ መድረስ ካልቻለች ወደ ሁለት ወገኑ ውል ገሰሽ ማለቱን ትመርጣለች። ዋሺንግተን ለምሳሌ ባለፉት ዓመታት ከ 11 የላቲን አሜሪካ አገሮች ጋር የሁለት ወገን ውሎች አድርጋለች። የአውሮፓ ሕብረትም ቢሆን እርግጥ ዳር ቆሞ መመልከቱን አልመረጠም። ከሜክሢኮና ከቺሌ ጋር የሁለት ወገን የነጻ ንግድ ውል አስፍኗል። የጀርመን የአገርና የውጭ ንግድ ማሕበር ፕሬዚደንት አንቶን በርነር በመሠረቱ በዓለም ንግድ ድርጅት ውስጥ የሚደረግ ለሁሉም 149 ዓባል አገሮች የሚሠራ የብዙሃን መንግሥታት ስምምነት የበለጠ ጥቅም እንደሚሰጥ ነው የሚያምኑት።

ግን የዓለም ንግድ ድርጅት ድርድር ሲሰናከል የሁለት ወገኑ ባይላተራል ውል አማራጭ መሆኑ የማይቀር ነው ባይ ናቸው። ይሁንና በርነር አያይዘው እንደሚያስረዱት አማራጩ ሁሉንም ወገኖች አይጠቅምም። “በጣሙን ተጎጂዎቹ ንግዱን ይበልጥ የሚፈልጉት ታዳጊ አገሮች ናቸው። በተለይም የድሃ ድሃ የሆኑት” ብለዋል። ይህም ማለት ብዙዎች በተለይ በጥሬ ሃብት ብዙ ያልታደሉ ትናንሽ የአፍሪቃ አገሮች በታላላቆቹ የንግድ ተጓዳኞች ማተኮሪያ ዝርዝር ውስጥ ዝቅ ብሎ መቀመጡ ግድ ይሆንባቸዋል ማለት ነው። የሌሎች ታናናሽ-ድሃ የእሢያና የላቲን አሜሪካ አገሮች ዕጣም ከዚህ የተለየ አይሆንም።

የተጠቀሱት አገሮች ከዚሁ ሌላ ከራሳቸው ተነስተው የሁለት ወገን የንግድ ውል ለመሻት በቂ አቅም የላቸውም አንቶን በርነር እንደሚሉት። “በቀላሉ በሰው ሃይልና አቅም ማነስ የተነሣ ከታላላቆቹ የኤኮኖሚ አካባቢዎች፤ ከጃፓንም ይሁን ከአሜሪካ ወይም ከአውሮፓ ሕብረት ጋር ለራሳቸው የሚጠቅም ውጤት ለማግኘት የሚያበቃ ድርድር ማካሄድ አይችሉም። ይህ ብቻ አይደለም። ለምሳሌ ጀርመንን የመሰለች በውጭ ንግዷ ቀደምት የሆነች አገር ከረጅም ጊዜ አንጻር ከኮስታሪካ ይልቅ ቻይናን ወይም ሕንድን መምረጧ ግልጽ ነው። እንግዲህ ታናናሾቹ አገሮች ማራኪነትም ይጎላቸዋል”

በዓለም ንግድ ድርጅት ውስጥ የሚደረጉ ስምምነቶች መላውን ዓባል መንግሥታት የሚጠቀልሉ ሲሆኑ ባይላተራል የንግድ ውሎች የተለየ ጥቅም የሚሰጡት ግን ለታሳታፊዎቹ አገሮች ወይም ሁለት ወገኖች ብቻ ነው። እርግጥ ጠንካሮቹ አገሮች በቀላሉ ጥቅማቸውን ሊያራምዱባቸው ይችላሉ። ለዚህም ነው በኤኮኖሚ የበለጸጉት መንግሥታት የአውሮፓ ሕብረት አገሮች፣ አሜሪካና ጃፓን በሁለት ወገኑ ውል ከመለስተኞቹ ይልቅ የበለጠ የሚጠቀሙት። የታዳጊ አገሮችን የከፋ ሁኔታ ለማሻሻል የዓለም ንግድ ድርድር መልሶ መንቀሳቀሱና ፍትሃዊ ከሆነ ግብ መድረሱ ግድ ነው።