1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የዓለም ባንክና ድህነት-ቅነሳ

ሐሙስ፣ ሰኔ 10 1996

ከቅርብ ጊዜ በፊት የቀረበ አንድ የዓለም ባንክ ጥናት እንደሚጠቁመው፣ ባለፉት ሃያ ዓመታት ውስጥ ጠቅላላው የዓለም ድህነት እየተቀነሰ ነው የተገኘው፣ ግን ይኸው አዎንታዊ ለውጥ የተከናወነው፣ የዓለም ባንክና የዚሁ ተባባሪ የሆነው ዓለምአቀፉ ገንዘብ መርሕ ተቋም/ኣይኤምኤፍ የሰጧቸውን ምክርና መመሪያ ተቀብለው በተገበሩት ሀገሮች ውስጥ ኣይደለም።

https://p.dw.com/p/E0fa

የባንኩ ጥናት እንደሚለው ከሆነ፣ በሚደረጁት ሀገሮች ውስጥ በቀን ከአንድ ዶላር ባነሰ ወጭ የሚኖሩት ሰዎች አሃዝ እጎአ በ፲፱፻፹፩ እና ፪ሺ፩ መካከል ወደ ግማሽ በተጠጋ ደረጃ ነው የተቀነሰው። በመላው የሚደረጁ ሀገሮች ውስጥ በቀን ከአንድ ዶላር በታች በሆነ ወጭ የሚኖሩት ድሆች አሃዝ በዚያው በተጠቀሰው የሃያ ዓመታት ጊዜ ውስጥ ከ1.5 ሚሊያርድ ወደ1.1 ሚሊያርድ ወርዶ ነበር የተገኘው። ይህም በዓለም ሕዝብ አኳያ ሲታይ ከ፵ ወደ ፳፩ በመቶ የተቀነሰ ሆኖ ነው የሚታየው።

ግን ጥናቱ እንደሚለው፣ ድህነትን በመታገል ረገድ ብዙው አዎንታዊ ለውጥ የተገኘው በእስያ ሀገሮች--በተለይም ደግሞ በሕንድና በቻይና ነው። የሁለቱ ሀገሮች ጥረት ተጠቃልሎ ሲታይ፣ ፭፻ ሚሊዮን የሚደርስ ሕዝብ ነው ከድህነቱ ሰንሰለት እንዲላቀቅ ለማድረግ ያስቻለው። በዚህ አንፃር ደግሞ፥ የዓለም ባንክና የዓለምአቀፉ ገንዘብመርሕ ድርጅት መርሐግብር በተዘረጋባቸው የአፍሪቃ፣ የላቲን አሜሪካ፣ የምሥራቅ አውሮጳ እና የማዕከላይ እስያ ሀገሮች ውስጥ ውጤቱ መንማና ሆኖ ነበር የተገኘው።

እጎአ ከ፲፱፻፹፩ ወዲህ ጠቅላላው ብሔራዊ ውጤት በነፍስወከፍ ሲታሰብ በአምስት እጅ በጨመረባት ቻይና፣ የፍፁም ድሆቹ አሃዝ ከ፮፻ ሚሊዮን ወደ ፪፻ ሚሊዮን/ወይም ከ64 በመቶ ወደ 17 በመቶ ነበር የተቀነሰው። በሕንድ ደግሞ፥ ለምሳሌ እጎአ በ፲፱፻፹፩ ከ፫፻፹ ሚሊዮን በላይ ወይም ፶፭ በመቶ የነበረው በፍፁሙ ድህነት ተይዘው የነበሩት ሰዎች አሃዝ ከሃያ ዓመታት በኋላ፣ በ፪ሺ፩፣ ወደ ፫፻፶፱ ሚሊዮን ወይም ወደ ፴፭ በመቶ ነበር የተቀነሰው። በዚህ አንፃር ደግሞ፣ የዓለም ባንክና ዓለምአቀፉ ገንዘብመርሕ ድርጅት/ኣይኤምኤፍ የሚዘረጉትን የብድር መውሰጃ--ማለት የመዋቅር ማስተካከያ--መርሐግብር በቅርብ የሚከታተሉ ብዙ ሀገሮች ባሉበት በሰሐራ ደቡቡ የአፍሪቃ ከፊል ድህነት በመቀነስ ፈንታ፣ ጭራሹን እየተባባሰ መሄዱን ጥናቱ ያመለክታል።

እጎአ ከ፲፱፻፹፩ ወዲህ፣ ጥናቱ እንደሚለው፣ በሰሐራ ደቡቡ የአፍሪቃ ከፊል ያሉት ሀገሮች ጠቅላላ ብሔራዊ ውጤት በ፲፫ በመቶ ሟሽሾ የተገኘበት ሁኔታ በቀን ከአንድ ዶላር ባነሰ ወጭ የሚኖሩት ሰዎች አሃዝ ወደ እጥፍ በተጠጋ ደረጃ እንዲጨምር ነው ያደረገው--ይኸውም ከ164 ሚሊዮን ወደ 314 ሚሊዮን።
በምሥራቅ አውሮጳና በማዕከላይ እስያም፣ በኮሙኒዝሙ ክራንቻ ተይዘው በነበሩት በብዙዎቹ ሀገሮች ውስጥ፣ ከፍተኛው ሥራአጥነትና የምርት ድክመት የከባዱን ድህነት ይዘት ወደ ስድስት በመቶ ነበር ያወጣጣው። በምሥራቅ አውሮጳና በማዕከላይ እስያ በቀን ከሁለት ዶላር ባነሰ ወጭ የሚኖሩት ሰዎች አሃዝ በ፲፰ ዓመታት ውስጥ ከስምንት ሚሊዮን(ወይም ከሁለት በመቶ) ወደ ፩፻ ሚሊዮን(ወይም ወደ ፳፭ በመቶ) ነበር ያሻቀበው።

በማዕከላይ ምሥራቅም፣ ዓለምአቀፍ የፊናንስ ተቋማት የሚሰጧቸውን የልማት መመሪያ በሚከተሉትም ግብጽንና ዮርዳኖስን በመሳሰሉት ሀገሮች ውስጥ፣ በቀን ከሁለት ዶላር ባነሰ ወጭ የሚኖሩት ሰዎች አሃዝ ከ፶፪ ሚሊዮን ወደ ፸ ሚሊዮን የተወጣጣ ሆኖ ነበር የተገኘው።

በላቲን አሜሪካ፤ ያው የዓለም ባንክ ጥናት እንደሚያሳየው፣ በቀን ከአንድ ዶላር ባነሰ ወጭ የሚኖሩት ችግረኞች አሃዝ ከ፴፮ ሚሊዮን ወደ ፶ ሚሊዮን ነበር የተወጣጣው።

ይህም ሆኖ፣ የዓለም ባንክ ድህነት በተባባሰባቸውም ሀገሮች ውስጥ የመዋቅር ማስተካከያው መርሐግብር መከናወን እንዳለበት ሲያስገነዝብ ነው የቆየው። ይኸው፣ ለብድር አወሳሰድ ቀዳሚ ግዴታ የሆነው መርሐግብር፣ የመንግሥት ንብረት ወደ ግል ይዞታ እንዲዛወር ከሚደረግበት ርምጃ አንስቶ፣ ለሀገር ውስጥ እንዱስትሪዎች የሚሰጠው ከለላና ድጎማ እስከሚወገድበት እና ለማኅበራዊው ኑሮ የሚመደበው ርዳታ እስከሚቀነስበት ተግባር የሚዘልቅ ነው። ግን ሃያስያን ይህንኑ ግዴታ ለሚደቅኑት የዓለም ባንክና ለዓለምአቀፉ ገንዘብመርሕ ድርጅት የሚያጎሉት ማስገንዘቢያ፥ ቻይናንና ሕንድን የመሳሰሉት ሀገሮች በድህነት አንፃር በሚደረገው ትግል ረገድ ትልቅ እመርታ ለማግኘት የበቁት የተቋማቱን መመሪያ ተከትለው አይደለም ይላል። ርግጥ፣ ሕንድና ቻይና ንግድን ነፃ በማድረግ ረገድ አስፈላጊውን ርምጃ አንቀሳቅሰው ይሆናል፣ ግን፣ በዚሁ ርምጃቸው ረገድ እስከምን ነው የሄዱት ነው ጥያቄው--በሃያስያኑ አመለካከት። ሁለቱ ሀገሮች የተሐድሶውን ለውጥ ያመጡት ቀስበቀስ፣ እርከን በእርከን መሆኑ ነው። ኦክስፋምን የመሳሰሉት ግብረሠናይ ድርጅቶችም በበኩላቸው፣ ሕንድና ቻይና የሁለቱን ተቋማት መመሪያ በመከተል አይደለም በድህነት ቅነሳ ረገድ ጉልህ ለውጥ ለማምጣት የበቁት በማለት ያስገነዝባሉ።

በሃያስያኑ አመለካከት መሠረት፣ የዓለም ባንክና ዓለምአቀፉ ገንዘብመርሕ ድርጅት/ኣይኤምኤፍ የድህነትን ግዝፈት ምክንያት በማድረግ ጥጥሩ መመሪያቸው እንዲተገበር የሚያስገድዱበት አድራጎት ዓምና ስለሰብዓዊ ዕድገት የተባ መ የልማት መርሐግብር ያቀረበውን ዘገባ የሚቃረን ነው። ይኸው ዘገባ ሁለቱ ተቋማት ለብድራቸው አሰጣጥ የሚደቅኑት ቀዳሚ ግዴታ(ለምሳሌ ለትምህርትና ለጤና ጥበቃ አገልግሎት ግብር እንዲከፈል፣ የውሃ አቅርቦት ወደ ግል ይዞታ እንዲዛወር፣ የማኅበራዊ ኑሮ ድጎማ እንዲቀነስ የሚጠይቁበት ሁኔታ) ለኅብረተሰቡ በጣም ጎጂ ሆኖ ነው የሚታየው።

የሁለቱ አበዳሪ ተቋማት ቅን ታዛዦች የሆኑትና መመሪያቸውን የሚከተሉት የአፍሪቃ፤ የላቲን አሜሪካና የማዕከላይ ምሥራቅ ሀገሮች ድህነትን በመታገል ረገድ እምብዛም ያስገኙት ውጤት አለመኖሩ የዓለም ባንክን መመሪያ አተረጓጎም የሚቃረን መሆኑም ነው የሚመለከተው።

ሌላ ምሳሌ ለመስጠት ያህል፥ ግብጽም የምትገኝባቸው የማዕከላይ ምሥራቅ ሀገሮች፣ እንዲሁም አርጀንቲናንና ቦሊቪያን የመሳሰሉት የላቲን አሜሪካ መንግሥታት የፊናንስ ተቋማቱን መመሪያ በጥንቃቄ ቃልበቃል በመከተል፥ ለማኅበራዊው ኑሮ የሚመድቡትን ድጎማ ቀነሱ፣ ኤኮኖሚዎቻቸውን ለነፃው ንግድ ክፍት አደረጉ፣ የመንግሥትን ንብረት ወደ ግል ይዞታ በማዛወር ሸጡ---ግና በድህነት ቅነሳ ረገድ አንዳች ያስገኙት ፋይዳ የለም ይላል ጥናቱ።

የሆነ ሆኖ፣ የዓለም ባንክ ራሱ እንደሚለው፣ ፬፻፳ ሚሊዮን የሚደርሱ ፍፁም ችግረኞችን ከድህነት ሰንሰለት ለማላቀቅ የበቃችው ቻይና ለሌቹ ሀገሮች ዓይነተኛ አርአያ ሆና መታየት አለባት። የዓለም ባንክ ሊቀመንበር ዎልፈንዘን ከቅርብ ጊዜ በፊት በሻንግሃይ/ቻይና ተከፍቶ ለነበረው፣ በድህነት አንፃር የሚደረገውን ትግል ላስመለከተው ጉባኤ ያሰሙት ንግግር፥ ቻይና ዛሬ 1.3 ሚሊያርድ ደርሶ የሚገኘውን ሕዝቧን ሙሉ በሙሉ ከድህነት ቀንበር ለማላቀቅ ከፍተኛ ጥረት እያደረገችም ሳለች የማዕከላይ ዕቀዳ ኤኮኖሚዋን ለውጣ በቦታው የገበያ ኤኮኖሚውን ሥርዓት ለመተካት በወሰደችው ርምጃ ረገድ ያተረፈችው ተሞክሮ ለሌሎች ዓይነተኛ ትምህርት ነው የሚሆነው ይላል።