1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የዓለም ባንክና አመራሩ

ረቡዕ፣ ሚያዝያ 10 2004

ዋሺንግተን ላይ ተቀማጭ የሆነው የዓለም ባንክ እንደተጠበቀው የአሜሪካን ዕጩ ጂም-ዮንግ-ኪምን አዲስ ፕሬዚደንቱ አድርጎ ስይሟል።

https://p.dw.com/p/14fRI
ምስል picture-alliance/dpa

ዋሺንግተን ላይ ተቀማጭ የሆነው የዓለም ባንክ እንደተጠበቀው የአሜሪካን ዕጩ ጂም-ዮንግ-ኪምን አዲስ ፕሬዚደንቱ አድርጎ ስይሟል። የደቡብ ኮሪያው ተወላጅ አሜሪካዊ ዜጋ በባንኩ አመራር ሥልጣን የሚተኩት በፊታችን ሐምሌ ወር ከአምሥት ዓመት የሥራ ዘመን በኋላ በቃኝ ብለው ስንብት የሚያርጉትን ሮበርት ዞሊክን ነው።

ኪም 25 ዓባላትን ያቀፈው የባንኩ ሥራ አስፈጻሚ አካል ባለፈው ሰኞ ባካሄደው ድምጽ አሰጣጥ በቸኛ ተፎካካሪያቸውን የናይጄሪያይቱን ፊናንስ ሚኒስትር እንጎዚ-ኦኮኞ-ልዌአላን ሲያሸንፉ ሌላው ዕጩ የቀድሞው የኮሉምቢያ ፊናንስ ሚኒስትር ሆሴ-አንቶኒዮ-ኦካምፖ ምርጫው ጥቂት ቀናት ሲቀረው ቀደም ብለው ወደኋላ ማለታቸው አይዘነም።

የዓለም ባንክ ሁለቱ የዋሺንግተን ዓለምአቀፍ የገንዘብ ተቋማት ባንኩና የምንዛሪው ተቋም በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ማብቂያ ገደማ አሜሪካ ውስጥ ብሬቶን ዉድስ ላይ ከተፈጠሩ አንስቶ በአሜሪካዊ ባለሥልጣናት ብቻ ሲመራ ነው የቆየው። በሌላ አነጋገር የዓለም ባንክ ለአሜሪካ፤ ዓለምአቀፉ የምንዛሪ ተቋም IMF ደግሞ ለአውሮፓ ተመድቦ ነው የኖረው። በመሆኑም በወቅቱ ምርጫ ለመጀመሪያ ጊዜ ከሌላው የዓለም ክፍል ተፎካካሪ ዕጩ መቅረቡ ራሱ እንደ አንድ ጠቃሚ ለውጥ መታየቱ አልቀረም። ይህም እርግጥ ያለ ምክንያት አይደለም።

ከ 1930ዎቹ ዓመታት ወዲህ ሃያሉ የሆነው በተለይም በኢንዱስትሪ ልማት የበለጸጉትን ሃገራት ኤኮኖሚ ብርቱ ቀውስ ላይ የጣለው በ 2008 የተከሰተ ዓለምአቀፍ የፊናንስ ቀውስ የዓለም ገጽታ በጣሙን እየተቀየረ መምጣቱን በጉልህ አሳይቷል። የአሜሪካ ኤኮኖሚ እጅጉን ሲዳከምና በአውሮፓም የኤውሮ ምንዛሪ ተገልጋይ ሃገራት ክልል በበጀት ቀውስ መናጡን ሲቀጥል ጊዜው በሌላ በኩል በቻይናና መሰል በተፋጠነ ዕድገት ላይ በሚገኙ ሃገራት መጠናከር በፖለቲካም ሆነ በኤኮኖሚ ዓለምአቀፉን የሃይል አሰላለፍ እየለወጠ የመጣበትም ነው።

ለምሳሌ ያህል ዛሬ አብዛኛው የዓለም የገንዘብ ክምችት የሚገኘው በቻይና ዕጅ ሲሆን ብሪክ በመባል የሚታወቁት በተፋጠነ ዕድገት የሚራመዱ ሃገራት በአንድ ላይ በዓለም ንግድ በኤኮኖሚ አቅም ሰፊውን ድርሻ ይይዛሉ። እነዚሁ ቻይና፣ ብራዚል፣ ሕንድና ሩሢያ ዛሬ የዓለም ኤኮኖሚ አንቀሳቃሽ መንኮራኩር ሆነው ሲታዩ በሚቀጥሉት ሶሥት ዓመታት ውስጥ የኤኮኖሚ ይዞታቸው ድርሻ በዓለም አቀፍ ንጽጽር 30 በመቶ እንደሚደርስ ነው የዋሺንግተኑ የምንዛሪ ተቋም የሚገምተው።

ለተጨማሪ ንጽጽር ዓለምአቀፉ የውጭ ንግድ ከ 2005 እስከ 2010 በኢንዱስትሪ ልማት በበለጸገው ዓለም በዓመት በአማካይ 2,9 በመቶ ሲያድግ በተራመዱትና በመልማት ላይ በሚገኙት ሃገራት በአንጻሩ በ 5,5 ከመቶ ከፍ ሲል ታይቷል። ሂደቱ በዚሁ አቅጣጫ የቀጠለ ሲሆን ይህ ሁሉ የሚጠቁመው ዓለምአቀፉ የኤኮኖሚ ስርዓት መሠረታዊ ለውጥ እንደሚያሻውና ከተጨባጩ ሁኔታ መጣጣም እንደሚገባው ነው። ሃያላን መንግሥታት በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ማግሥት የፈጠሩት የኤኮኖሚ ስርዓት ዛሬ ጊዜው አልፎበታል።

Internationaler Währungsfond in Washington DC
ምስል picture alliance/dpa

ከዚህ አንጻር እንግዲህ በውቅቱ የዓለም ባንክ ፕሬዚደንት ምርጫ ምንም እንኳ አርኪ ለውጥ ባይታይም ሌላው ዓለም ለመጀመሪያ ጊዜ የይገባናል ጥያቄ ማንሳቱ ራሱ ጥሩ የተሃድሶ ጅማሮ ነው። ለነገሩ የጊዜውን መለወጥ ራሷ አሜሪካም ሳትገነዘበው አልቀረችም። ዋሺንግተን የኤኮኖሚ ባለሙያ ያልሆኑትን ከሶውል የመነጩ ዜጋ ጂም-ዮንግ-ኪምን ዕጩ አድርጋ ማቅረቧ ምናልባትም አዳጊውን ዓለም፤ በተለይም እሢያን ለማግባባት የተወጠነ ሣይሆን እንዳልቀረ ነው አንዳንድ ታዛቢዎች የሚያምኑት።

ያም ሆነ ይህ ባለፈው ሣምንት ዕጩነታቸውን ቀድመው የሳቡት የኮሉምቢያው ተወላጅ ሆሴ-አንቶኒዮ-ኦካምፖ ሁኔታዎች መለወጥ መያዛቸውን በገለጹም የምርጫውን ዘይቤ ግን መጤን የሚገባው ነው ሲሉ ነው የተቹት።

«እርግጥ ባለፉት ጊዜያት ጠቃሚ መሻሻል ነው የተደረገው። ባለፈው ዓመት በዓለምአቀፉ ምንዛሪ ተቋም በ IMF አስተዳዳሪ አመራረጥ ሂደት ላይም መሻሻል ታይቷል። ይሁን እንጂ ሁኔታው በውል መጤን አለበት። ምክንያቱም ምርጫው በሃቅ ግልጽና በብቃት ላይ የተመሠረተ ነበር ብዬ አላስብም»

በምርጫው የተሸነፉት የናይጄሪያ የፊናንስ ሚኒስትር እንጎዚም ኪምን እንኳን ደስ ያለዎት ቢሉም አቡጃ ላይ በጉዳዩ በሰጡት መግለጫ አንድ ምርጫ ነጻ የሚሆነው በዕጩው ተጨባጭ ብቃት ላይ ሲመሠረት ብቻ መሆኑን አጥብቀው አስገንዝበዋል። በሙያ ብቃታቸው ክብደት የሚሰጣቸው እንጎዚ ቢመረጡ ታዳጊው ዓለም ምንኛ በተደሰተ ነበር። ግን ምኞቱ ለጊዜው ፍሬ አልሰጠም። በሌላ በኩል ግን ለወደፊቱ ጥርጊያ ከፋች ጠቃሚ ጅማሮ ሆኖ ሊታይ ይችላል። ይሁንና የጀርመን የሣይንስና የፖለቲካ ምርምር ተቋም ባልደረባ ሄሪበርት ዲተር በበኩላቸው ከአሜሪካ ሌላ ዕጩ መቅረቡ ብቻ በቂ አይደለም ባይ ናቸው።

Schweiz Weltwirtschaftsforum in Davos Ngozi Okonjo-Iweala aus Nigeria
ምስል dapd

«ኪዚህ ድርጊት ባሻገር መራመዱ ወደፊት ግድ የሚሆን ይመስለኛል። ተፎካካሪ ዕጩዎች መቅረባቸው መልካም ነው። ነገር ግን ትራንስ-አትላንቲኩ መንግሥታት በዓለምአቀፉ ምንዛሪ ተቋምና በዓለም ባንክ ላይ የነበራቸው የበላይነት አሁን ቀስ በቀስ ወደ መጨረሻው ማዝመም ይኖርበታል። በተፋጠነ ዕድገት ላይ የሚገኙት መንግሥታት፤ በተለይም የብሪክ ሃገራት መነሣት አንዴ ከፍተኛ የአመራር ቦታን ለመያዝ ማብቃቱ ግድ ነው። ታዲያ አሜሪካና አውሮፓውያንም በሚቀጥሉት ዓመታት አዲስ ጽንሰ-ሃሣብ ማቅረብ አለባቸው»

እርግጥ በውዴታ ሥልጣኑን አሳልፎ የሚሰጥ መኖሩ ሲበዛ ያጠያይቃል። እናም ከዚህ አንጻር ብሪክም ሆነ በጥቅሉ አዳጊው ዓለም የበለጠ ሥልጣን ማግኘቱ በቀላሉ የሚሳካ ነገር አይመስልም። ሄሪበርት ዲተር እንደሚሉትም የበለጸጉት መንግሥታት በውዴታ ሥልጣን ማካፈላቸው ጨርሶ የማይታሰብ ነገር ነው።

«በውዴታ አያደርጉትም። የውጭ ፖሊሲን ለማራመድ ጠቃሚ መሣሪያ በመሆኑ! ይህ ደግሞ የምንዛሪውን ተቋም ያህል የዓለም ባንክንም ይመለከታል። ይህም ማለት አዳጊዎቹና በተፋጠነ ዕድገት የሚራመዱት ሃገራት ተጽዕኖ ማድረግ ይኖርባቸዋል ማለት ነው። በሌላ በኩል እነዚሁ መንግሥታት ባለፈው ዓመት አንድ ጥሩ አጋጣሚ እንዳመለጣቸው ማስታወስም ያስፈልጋል። ይህም በክሪስቲን ላጋርድ አንጻር ለምንዛሪው ተቋም ሥልጣን ተፎካካሪ ዕጩ አለማቅረባቸው ነበር። ለማንኛውም በሚቀጥሉት ዓመታት ግን ተጽዕኗቸው እያደገ መሄዱ የማይቀር ነው»

በጎርጎሮሳውያኑ 1944 ከዓለምአቀፉ ምንዛሪ ተቋም ጋር ብሬተን ዉድስ ላይ የተመሠረተው ባንክ በመጀመሪያ የተወጠነው ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ጥፋት በኋላ መልሶ ግንባታን ለማራመድ ነበር። ባንኩ ዛሬ 187 ዓባል መንግሥታትና በዓለም ዙሪያ ዘጠን ሺህ ያህል ሠራተኞች ሲኖሩት ከ 1960 ወዲህ የልማት ዕርዳታንና ድህነት ቅነሣን ዓቢይ ተግባሩ አድርጎ ቆይቷል። ለአዳጊዎቹ ሃገራት የሰጠው ብድርና ዋስትናም ከ 50 ሚሊያርድ ዶላር በላይ እንደሚሆን ነው የሚገመተው።

ከዚህ አንጻር የባንኩ የልማት ተግባር ካተኮረበት ከአዳጊው ዓለም የመነጨ ዕጩ ቢመረጥ ምናልባት የተሻለ በሆነ ነበር። እርግጥ ጂም-ዮንግ-ኪም በአዳጊው ዓለም የተወለዱ ናቸው። ቢሆንም የአሜሪካ ዜጋና የፕሬዚደንት ኦባማ ዕጩ እንደመሆናቸው መጠን ከዋሺንግተን ጥቅም የሌላውን ማስቀደማቸውን ለማመን በወቅቱ በጣሙን ያዳግታል። በሌላ በኩል የዋሺንግተን ወኪላችን አበበ ፈለቀ በአገሪቱ ቀደምት ፖለቲከኞች ዘንድ የሚባለውን ጠቅሶ እንደገጸልን አሜሪካ ዕጩዋን የሰየመችው ከዚህ ቀደሙ በተለየ መስፈርት ነው። ግን ምን ያህል አዲስ ፖሊሲ ያስፍኑ አያስፍኑ ለጊዜው በውል የሚታወቅ ነገር የለም።

የ 52 ዓመቱ የኒው ሃምፕሻየር ዩኒቨርሲቲ አስተዳዳሪ የሕክምና ዶክተር ሲሆኑ የፊናንስ ባለሙያ የነበሩበት አንድም ጊዜ የለም። በዚህ ረገድ እስካሁን የዓለም ባንክ ፕሬዚደንት ከነበሩት 11 ቀደምቶቻቸው ሁሉ የተለዩ ናቸው። እንግዲህ የኤኮኖሚና የፊናንስ ችሎታቸውን በሰፊው ለማዳበር መጣሩ የሚቀርላቸው አይመስልም። በሌላ በኩል በዓለም ጤና ጥብቃ ድርጅት ያገለገሉና በልማት ዕርዳታ ሥራ ልምድም ያላቸው ሲሆኑ እንደ ጀርመኑ የሣይንስና የፖለቲካ ምርምር ተቋም ባልደረባ እንደ ሄሪበርት ዲተር አባባል ከሆነ ድህነት በሰፈነበት ዓለም ለሚካሄደው ለባንኩ ተግባር የሕክምና ሙያቸው ጠቃሚ ሊሆን የሚችልም ነው።

Jim Yong Kim und Barack Obama
ምስል Reuters

«እንግዲህ የድሃ ድሃ በሚባሉት ሃገራት እጅግ አስፈላጊ የሆነውን የዓለም ባንክን ተግባር በቀጣይነት ማራመዱ ይጠበቃቸዋል። እና እዚህ ላይ እርግጥ እንደ ሃኪም ያላቸው ዕውቀት መጠፎ የሚሆን አይመስለንም። የዓለም ባንክ እንድ ምንዛሪው ተቋም ሣይሆን በተለይ እጅግ ድሃ በሆኑት ሃገራት እንደሚሰራ ይታወቃል። ከዚህ አንጻር አንድ የሕክምና ባለሙያ ሊሰጥ የሚችለውን ጥቅምም ማሰብ አስፈላጊ ነው»

ኪም ቀደም ባለው ጊዜ በኢንዱስትሪ ልማት የበለጸገውን ዓለም የልማት ዕርዳታ ፖሊሲ አነስተኛና በሁነኛ ግብ ላይ ያላተኮረ ሲሉ መተቸታቸው ተሰምቷል። በ 2002 በአሜሪካ ሤኔት ፊት ቀርበው ዋሺንግተን ኤይድስ ለመታገል የምታደርገውን ወጪም በስፊው እንድታሳድግ ጠይቀው ነበር። ሆኖም ለዓለም ባንክ ፕሬዚደንትነት ከታጩ በኋላ ግን ይህን ጥሪያቸውን ሲደግሙ አልተደመጡም። እንግዲህ በትክክል የሚሆነውን ለማወቅ ፖሊሲያቸው እያደር መታዘቡ ግድ ነው የሚሆነው።

መሥፍን መኮንን

ነጋሽ መሀመድ