1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የወሲብ ጥቃቶችና የፍትህ አሰራር

ዓርብ፣ ጥር 9 2006

ሰሞኑን በሕንድ አንዲት ጀርመናዊት ወጣት እና ዴንማርካዊት እዛው ህንድ ውስጥ ተደፍረው ጉዳያቸው እያነጋገረ ይገኛል። በሕንድ ስለደረሱት የአስገድዶ መድፈር እና በኢትዮጵያ የሚደርሱ የወሲብ ጥቃቶች እንዲሁም ያለውን የፍትህ አሰራር በዛሬው የወጣቶች ዓለም እንቃኛለን።

https://p.dw.com/p/1Asbi
Symbolbild Vergewaltigung sexuelle Gewalt Afrika
ምስል picture-alliance/dpa

የሕንድ ፖሊስ ይፋ እንዳደረገው አንዲት ጀርመናዊት እና ዴንማርካዊት በጥቂት ቀናት ልዩነት ወሲባዊ ጥቃት ደርሶባቸዋል። የ18 ዓመቷ ጀርመናዊት ደቡብ ህንድ ውስጥ በአንድ የማደሪያ የባቡር ፉርጎ ውስጥ ሳለች ነበር አንድ ወንድ ወሲባዊ ጥቃት እንደደረሰባት ፖሊስ ባለፈው ዕሮብ ዕለት የገለፀው። የደፈራትም በቁጥጥር ስር መዋሉ ተገልጿል። እንዲሁ ባለፈው ማክሰኞ በሀገር ጉብኝት ላይ የነበሩ የ51 ዓመት ዴንማርካዊት ደግሞ ወደ ሆቴላቸው በጉዞ ላይ ሳሉ መንገድ ተሳስተው መንገድ ሲጠይቁ የተወሰኑ ወንዶች በጩቤ አስፈራርተው ጭር ወደ አለ ስፍራ እንደወሰዷቸው እና ኋላም በቡድን እንደደፈሯቸው ተናግረዋል። ፖሊስ በመጀመሪያ 15 ወንዶችን ቃል እንዲሰጡ ካደረገ በኋላ 8ንቱን በቁጥጥር ስር አውሏል። አገር ጎብኚዋ ወዲያው ክስ መስርተዋል። ወይዘሮዋ በሀገራቸው ኤምባሲ ትብብር አግኝተውም ወዲያው ወደ ሀገራቸው መመለሳቸው ተገልጿል። የደረሰባቸውን በደል በግልፅ አውጥተው የከሰሱት የውጭ ሀገር ዜጎች ጉዳይ ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ይፋ ይሁኑ እንጂ ህንድ ውስጥ በየቀኑ በርካታ ሰዎች ወሲባዊ ጥቃት ይደርስባቸዋል።

Indien dänische Touristin in New Delhi vergewaltigt Tatort
ዴንማርካዊቷ ወሲብ ጥቃት የተፈመባቸው ቦታምስል Reuters

በሕንድ አንድ ሰው አስገድዶ መድፈሩ ከተረጋገጠ ከተወነጀለ እስከ የሞት ፍርድ ድረስ ሊበየንበት ይችላል። ይህ በኢትዮጵያስ ምን ይመስላል? በአራት የአቃቢ ህግ መስሪያ ቤቶች በተለይ በወንጀል ጉዳዮች ላይ ከ15 ዓመት በላይ ያገለገሉት አቶ ዮሀንስ ወልደገብርኤል በህግ ድንጋጌዎች ውስጥ አስገድዶ መድፈር ከፍተኛ ቅጣት የሚያስበይን ነው ይላሉ። እንደእየሁኔታው እና ክብደቱም ፍርዱ እስከ 25 ዓመት ፅኑ እስራት ሊያስበይን እንደሚችል አቶ ዮሀንስ ገልፀውልናል። ወሲባዊ ጥቃት ከምን ይጀምራል? በግብረ ሶዶማውያን የሚደፈሩ ወጣት ወንዶች ጉዳይስ ምን ይመስላል? ለዚህ እና ሌሎች ጥያቄዎች መልስ ሰጥተውናል።

Symbolbild beratung Frau Jungfräulichkeitstest oder Vergewaltigung
ተጎጂዎች የምህር አገልግሎት የሚያገኙበት ስፍራ በጀርመንምስል picture-alliance/dpa

ሌላው ያነጋገርናቸው የኢትዮጵያ ሕግ ባለሙያ ሴቶች ማህበር የሥራ አስፈፃሚ ዳሬክተር የሆኑት ወ/ሮ ዜናዬ ታደሰን ነው። ወይዘሮዋ ወደ ማህበራቸው በርካታ ጥቃት የደረሰባቸው ሴቶች እንደሚመጡ እና ከዚህም ውስጥ የወሲብ ጥቃት የደረሰባቸው እንደሚገኙ ገልፀውልናል። ወደ ማህበሩም የሚመጡት ሴቶች በተለያዩ የእድሜ ክልል የሚገኙ ናቸው ። ማህበሩም የግንዛቤ ማስጨበጥ አገልግሎት በመስጠት ይተባበሯቸዋል።

ወሲባዊ ጥቃትን በተመለከተ አብዛኛውን ጊዜ ሴቶች ከማያውቁት ሰው ይልቅ በሚያውቋቸው ሰዎች ጥቃት እንደሚደርስባቸው መዘርዝሮች ያመላክታሉ። አዳጊ ወጣቶች የወሲባዊ ጥቃት ሙከራን በጊዜ ተረድተው ርምጃ እንዲወስዱ ወ/ሮ ዜናዬ የሚመክሩት አለ።

በኢትዮጵያ የሚደርሱ የወሲብ ጥቃቶችና ያለውን የፍትህ አሰራር አስመልክቶ ያደረግነውን ሙሉ ዝግጅት ከድምፅ ዘገባው ያገኙታል።

ልደት አበበ

ነጋሽ መሐመድ