1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኮንጎ ኢንጋ 3 ግድብ

ዓርብ፣ የካቲት 28 2006

ኤሌክትሪክ የዴሞክራቲክ ኮንጎ ዜጎች የሚመኙት ግን እንደልብ ያላገኙት ኃይል ነዉ። ኢንጋ አንድ እና ሁለት የሃይድሮ ኤሌክትሪክ ማመንጫዎች ከ200 ሜጋ ዋት በላይ እንደሚያመነጩ ቢገለፅም የሕዝቡን የኃይል ፍላጎት ገና አላረኩም።

https://p.dw.com/p/1BLzg
DR Kongo Inga Staudamm
ምስል DW
DR Kongo Inga Staudamm
ምስል DW

የሀገሪቱ መንግስት በኮንጎ ወንዝ ላይ 4,800 ሜጋ ዋት ያመነጫል የተባለለትን ኢንጋ ሶስት ግድብ ለመገንባት ተዘጋጅቷል። እንዲያም ሆኖ ለግንባታዉ እስከ 12 ቢሊዮን ዶላር እንደሚያወጣ የተገመተዉ ማመንጫ ዉጤት ለኅብረተሰቡ ሳይሆን ለግዙፍ የኤኮኖሚ ተቋማት የኃይል ጥማት ማርኪያ ይሆናል የሚል ትችት እየቀረበ ነዉ።

በጎርጎሪዮሳዊዉ 1972ዓ,ም ተግባሩን የጀመረዉ የኢንጋ 1 ግድብ 52 ሜጋ ዋት፤ እሱ ሥራ በጀመረ በአስረኛዉ ዓመት ሥራዉ የተጠናቀቀዉ ኢንጋ 2 ደግሞ 178 ሜጋ ዋት ኤሌክትሪክ ያመነጫሉ። ከአፍሪቃም ግዙፍ የዉሃ ኃይል ማመንጫ በመሆናቸዉ ይታወቃሉ። እንዲያም ሆኖ ግን የዴሞክራቲክ ሪፑብሊክ ኮንጎን ሰፊ ግዛት አካልሎ ለሕዝቡ ኃይላ መዳረስ አልቻሉም። ለዚህም ነዉ እኝህ የኪንሻሳ ኗሪ ተቸግረናል የሚሉት፤

«ኪንሻሳ ዉስጥ በኤሌክትሪክ እጥረት እየተቸገርን ነዉ። ማቀዝቀዣ መጠቀም ስላልቻልንም ምግብ እየተበላሸብን ተቸግረናል።»

Kongo Staudamm Inga
ምስል picture-alliance/dpa

ከዚህም ሌላ ሌቦችም ጨለማን ተገን በማድረግም በየጎዳናዉና በየቤቱ ችግር ማስከተላቸዉ አልቀረም። እንደሚባለዉም ከአስሩ አንዱ ዜጋ የኤሌክትሪክ አገልግሎት አያገኝም። የኢንጋ 3 የግንባታ ዜና ለብዙዎች ተስፋ ጭሯል። ከኪንሻሳ በስተምዕራብ በ400 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በኮንጎ ወንዝ አጠገብ ነዉ 12 ቢሊዮን ዶላር እንደሚያወጣ የተገመተዉ ግድብ የሚገነባዉ። የወጪዉን አንድ ሶስተኛ የኮንጎ መንግስት ራሱ የመሸፈን እቅድ እንዳለዉ ሲነገር ለቀሪዉ የሀገር ዉስጥና ዓለም ዓቀፍ ኩባንያዎች እንደሚሳተፉ ተገልጿል። ከዉሃ 4,800 ሜጋ ዋት የኤልክትሪክ ኃይል እንዲያመነጭ የታሰበዉ ይህ ግድብም በልማት ወደኋላ ለቀረችዉ የመካከለኛዉ አፍሪቃ ሀገር መለያ እንደሚሆን ተገምቷል። ከኮንጎ የፈጠራ ቴክኒዎሎጂና የዘላቂ ልማት ማዕከል ናኒ ማይንዛና ኢንጋ ሶስት ለዜጎች አስተማማኝ የኤልክትሪክ ኃይል ከማስገኘት በተጨማሪ ለአካባቢ ተፈጥሮዉም ጠቃሚ ነዉ ባይ ናቸዉ፤

«ታዳሽ የኃይል ምንጭን በማስገኘት በኩል ለኮንጎ ዜጎች ኢንጋ ምላሽ ይሆናል። ለሁሉም ኮንጓዉያን ኤሌክትሪክ ማዳረስ፤ እንዲሁም ለተራቆተዉ የኮንጎ ደን አንዳች ነገር ማድረግም እንችላለን።»

ግድቡ ሲጠናቀቅ ለዜጎች በሙሉ የኤልክትሪክ ኃይል ይዳረሳል የሚለዉ ተስፋ ቢደጋገምም ፕሮጀክቱን በቅርብ የሚከታተሉ አንዳንድ ወገኖች ይን አያምኑም። ደቡብ አፍሪቃ ፕሪቶሪያ የሚገኘዉ ዓለም ዓቀፍ ወንዞች የተሰኘዉ መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት ባልደረባ ሩዶ ሳንያንጋ የአፍሪቃ መንግስታት እንዲህ ያሉ ግዙፍ የመሠረተ ልማት ፕሮጀክቶችን የሚተልሙት ከምንም በላይ ለዝናና ብሄራዊ ስሜትን ለመቀስቀሻ እንደሆነ ነዉ የሚያመለክቱት። እርግጥም መረጃዎች እንደሚያሳዩት ከኢንጋ ሶስት ግድብ ይመነጫል ተብሎ ከሚጠበቀዉ ኤሌክትሪክ አብዛኛዉ ለኮንጎ ሕዝብ ሳይሆን ወደሌሎች ሊሻገር ከወዲሁ ታቅዷል። ባለፈዉ ዓመት የደቡብ አፍሪቃ መንግስት 2,500 ሜጋ ዋት ለመግዛት ተስማምቷል። ያ ደግሞ ግድቡ ከሚያመነጨዉ ግማሹን ማለት ነዉ። 1,300 ሜጋ ዋት ደግሞ በኮንጎ ካታንጋ ግዛት ለሚካሄደዉ የማዕድን ማዉጫ የሚዉል ነዉ። የሀገሪቱ መንግስት ግን ይህ ለልማቱ ወሳኝ እንደሆነ ያምናል። ጠቅላይ ሚኒስትር ማታታ ፖንዮ፤ ለሀገሪቱ የእድገት መንገድ እና ለአፍሪቃም የሚበጅ እንደሆነ ይናገራሉ። ሩዶ ሳንያንጋ ግን እንዲህ ያሉ ፕሮጀክቶች ለሙስና የተጋለጡና ተጠቃሚዎቹን ጥቂቶች መሆናቸዉን ያመለክታሉ።

DR Kongo Inga Staudamm
ምስል DW

«በተደጋጋሚ እንደተረጋገጠዉ ደካማ አስተዳደር ባላቸዉ በአብዛኛዎቹ የአፍሪቃ ሃገራት እንዲህ ያሉ ግዙፍ ፕሮጀክቶች ሙስናን በማባባስ ይታወቃሉ። ወደማኅበረሰቡና ዜጎች መዳረስ የሚኖርባቸዉ አገልግሎቶችም እነሱን እምብዛም ሲጠቅሙ አይታይም፤ ጥሩ ግንኙነት ላላቸዉ ለጥቂት ልሂቃን መጠቀሚያ ነዉ የሚሆኑት።»

ኢንጋ አንድና ሁለት ግድቦች በፕሬዝደንት ሞቡቱ ሴሴ ሴኮ ዘመነ ስልጣን የታቀዱና የተገነቡ ናቸዉ። በወቅቱ 1,7000 ሜጋ ዋት እንዲያመነጩ ነበር የታሰበዉ። አፈጻጸሙ ላይ የተጓደሉ ፕሮጀክቶች በመኖራቸዉ ያ አልተሳካም። ሳንያንጋ ለልማት ፕሮጀክቶቹ ተብሎ ከዓለም ባንክ የተሰጠዉ ገንዘብም ከነፕሮጀክቶቹ የገባበት እንደማይታወቅ ጠቁመዋል። ያም ሆኖ ለኢንጋ ሶስትም የዓለም ባንክ መቼ እንደሆነ ባይገልፅም የገንዘብ ድጋፍ እንደሚሰጥ ትናንት አስታዉቋል።

ፊሊፕ ዛንደነር/ ሸዋዬ ለገሠ

ኂሩት መለሰ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ