1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኮንጎው ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ

ሰኞ፣ ጥቅምት 20 1999

በኪንሻሳ የድምፅ መስጫ ጣቢያ አንድ መራጭ ድምፅ ሲሰጥ

https://p.dw.com/p/E0ho
ምስል AP
በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ የኮንጎ ዜጎች ከሁለቱ ተፎካካሪ ዕጩ ፕሬዝዳንቶች አንዱን ለመምረጥ ትናንት ድምፅ ሰጥተዋል ። አብዛኛዎቹ መራጮችም የትናንቱ የመለያ ምርጫ ለዘመናት በሀገሪቱ የተካሄደው ጦርነት ማሳረጊያና የኮንጎ አዲስ ምዕራፍ መጀመሪያ ይሆናል የሚል ተስፋ አላቸው ። ይኽው በርካታ ዜጎች ድምፅ የሰጡበት ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ በዓለም ዓቀፍ ታዛቢዎች ዓይን ያን ያህል የጎላ እንከን አልታየበትም ። የምርጫው ሂደት የተረጋጋና ሰላማዊ እንደነበር ነው ታዛቢዎች የተናገሩት ። የምርጫው ውጤትም ከጥቂት ሳምንታት በኃላ ይፋ ይሆናል ። ከወዲሁ የሚሰጡ ግምታዊ አስተያየቶች ግን የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ጆሴፍ ካቢላ እንደሚያሸንፉ እየጠቆሙ ነው ።
ከመለያ ምርጫው ተወዳዳሪዎች አንዱ የኮንጎ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ፕሬዝዳንት ጆሴፍ ካቢላ ከባለቤታቸው ጋር ድምፅ በሚሰጡበት ምርጫ ጣቢያ ሲደርሱ ደጋፊዎቻቸው ደማቅ አቀባበል አድርገውላቸዋል ። ካቢላ በአንድ ጎምቤ በተባለው አካባቢ በዲፕሎማቶች መኖሪያ ሰፈር ትምህርት ቤት ቅፅር ግቢ ውስጥ ቀትር ላይ ነበር ድምፃቸውን የሰጡት ። በዚሁ ምርጫ ጣቢያ እስከዚያን ሰዓት ድረስ ድምፅ ሊሰጥ የወጣው መራጭ ቁጥር አነስተኛ ነበር ። ቀኑ እየገፋ ሲሄድ ግን የመራጩ ቁጥር ተበራከተ ። ትናንት ከሰዓት በኃላ ድምፅ ከሰጡት መራጮች አንድ ጃክሰን ባርቤስ ነው ። ጃክሰን በአካባቢው ይጥል የነበረው ከባድ ዝናብ ሳያሳንፈው በዝናብ እንደራሰ ነበር ምርጫ ጣቢያው የደረሰው ። በመምረጡ የተሰማውንም እንዲህ ሲል ነበር የገለፀው ።
ድምፅ
“በመምረጤ ደስተኛ ነኝ ።”
ሌላ መራጭም ድምፅ መሰጠቱ በሀገሪቱ የተፈጠረውን ትርምስ ለማስወገድ አስፈላጊ ነው ። በእግዚአብሄር ዕርዳታ ይህ ይሳካል ብለን ተስፋ እናደርጋለን ብሏል ። ይህ መራጭ የከዚህ ቀደሙን ተሞክሮውን ሲያስታውስ አብዛኛውን ህይወቴን በአምባገነኑ ሞቡቱ ዘመን ነው ያሳለፍኩት ሞቡቱ እሺ ካሉ ሁላችንም የተባለውን ማድረግ ነበረብን ሞቡቱ ዕብቢ ካሉ ደግሞ ሁሉንም እናቆማለን ።አሁን ግን እሺም ዕምቢ ለማለት ወሳኞቹ እኛ ነን ብሏል ። ከዚህ በኃላ የሽግግሩ ጊዜ ያበቃል ተብሎ ነው የሚገመተው ። በፕሬዝዳንት ካቢላ የስልጣን ዘመን ምርጫው ገቢራዊ ሆኗል ። የተቀናቃኙ የጆን ፕየር ቤምባ ደጋፊዎችም ድምፃቸውን ሰጥተዋል ። ወቅቱ የለውጥ ነው ተብሎ ነው የሚታሰበው ። ለውጥ መምጣቱ ግን ከእስካሁን አካሄድ እንደሚታየው አጠራጣሪ ነው ። በቅድመ ምርጫው ትንበያ መሰረት ትናንት ከተሰጠው ድምፅ ካቢላ ሀምሳ ሰባት በመቶውን ተቀናቃኛቸው ጆን ፕየር ቤምባ ደግሞ አርባ ሶስት በመቶውን ድምፅ ያገኙ ይሆናል ። ውጤቱ እንግዲህ ከሶስት ሳምንት በኃላ ይታወቃል ። ለጊዜው የታወቀ ነገር ቢኖር ትናንት በአንድ ክፍለ ሀገር የሚገኝ የምርጫ ጣቢያ ለመዝረፍ ሞክረዋል የተባሉ ሁለት የቤምባ ደጋፊዎች መገደላቸውና በአንዳንድ ስፍራዎችም ረብሻዎች መነሳታቸው ነው ። ከዚህ ውጭ ግን የምርጫው ሂደት ሰላማዊ እንደነበር ታዛቢዎች መስክረዋል ።” ምርጫው ነፃና ግልፅ ነበር ። በትናንቱ መርጫ ድምፅ ሊሰጥ የወጣው ህዝብ ቁጥር እንዳለፈው ምርጫ ብዙ አልነበረም ። የመጀመሪያው ቆጠራ ውጤት ከአርባስምንት ሰዓት በኃላ ይፋ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል ። እናም እስካሁን እንደሆነው ሁሉ እስከዚያውም ሰላማዊ ይሆናል ብለን ተስፋ እናደርጋለን ።”
ታዛቢዎች ይህን ሲሉ አንዳንድ የኮንጎ ዜጎች ደግሞ የምርጫው ውጤት ይፋ ሲደረግ ይሆናል ብለው የሚገምቱት ያሰጋቸዋል ።
“የምርጫው ውጤት ይፋ ሲደረግ ሊሆን የሚችለው በመጠኑም ቢሆን ያስፈራናል። ምክንያቱም ያኔ ነው ግጭቱ በደጋፊዎች መካከል የሚቀሰቀሰው ። እነዚህ ግለሰቦች መሳሪያ አላቸው ።በዚህ የተነሳ መጥፎ ነገር ያጋጥማል ብለን እንጠብቃለን ። ጦርነት እንዲጀመር አንፈልግም ። በኮንጎም ተጨማሪ ደም እንዲፈስ አንዲሁ “
የነዋሪዎቹ ስጋት ይህ ቢሆንም የሁለቱ ተቀናቃኞች የጆሴፍ ካቢላና የቤምባ ደጋፊዎች ከምርጫ በኃላ ምንም ዓይነት ኃይል ላለመጠቀም ስምምነት ፈርመዋል ።ስምምነቱ ለተሸናፊው ወገን ደህንነት ዋስትና ይሰጣል ።